አዲስ አበባ የክረምቱ ወቅት ጠንከር ከሚልባቸው የአገራችን ክፍሎች አንዷ ናት። በዚህ የተነሳ ክረምት በመጣ ቁጥር በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎችና የተጎሳቆሉ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ አዲስ አበቤዎች ስጋት ላይ መውደቃቸው አይቀሬ ነው። ከዚህም ባሻገር ክረምት በመጣ ቁጥር በአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች ትልቅ ፈተና ያጋጥማቸዋል። ምክንያም ወንዞቹ በክረምት በሚሞሉበት ወቅት ለህይወታቸውም አደጋ የሚስከትልበት ሁኔታ የተለመደ ነውና።
በሌላ በኩል እነዚህ አዲስ አበባን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች በአግባቡ ብንጠቀምባቸው ለከተማዋ የውበትና የሃብት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን እስካሁን በነበረው ሁኔታ ወንዞቹ በአንድ በኩል ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት በሌላ በኩል የቆሻሻ መጣያ በመሆን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዝኖ ኖሯል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም መንግሥት በአዲስ አበባ ወንዞችን በልዩ ሁኔታ ማልማት የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ትውልዱም ሆነ እድገቱ በአሮጌው ቄራ በኩል በሚያልፈው ወንዝ ዳር አካባቢ መሆኑን የነገረን ወጣት መስፍን ሳሙኤል አኗኗሩ ስለ ወንዝ ዳር ህይወት፣ ስለ ወንዝ ዳር ቤት፣ ስለ ወንዝ ዳር ጤና ሁኔታ፣ ስለ ወንዝ ዳር ንፅህና፣ ስለ ወንዝ ዳር ደህንነት እና ሌሎችም በሚገባ እንዲያውቅ እድል እንደፈጠረለት ይናገራል። የጤና ባለሙያው ወጣት መስፍን እንደሚለው የወንዝ ዳር አካባቢው በችግሮች የተሞላ ነው። እንኳን ለመኖር በዛ በኩል ለማለፍም ይከብዳል። በመሆኑም መንግሥት አካባቢውን ለማልማት መዘጋጀቱ ሊያስመሰግነው ይገባል።
በተለይም የነዋሪዎችን ጤንነት ከመጠበቅ፣ የከተማውን መሰረታዊ ችግር ከመፍታት አኳያ ርምጃው ሊበረታታ የሚገባው ነው። ነዋሪው በተለያዩ፤ በተለይም ባዮሎጂካልና ኬሚካል ለሆኑ በሽታዎች የተጋለጠ፣ በቆሻሻዎች የተበከሉ የፋብሪካ ፍሳሾች ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ከማስወገድና ፅዱ፣ ለኑሮ አመቺና ውብ ከተማ ከመፍጠር አኳያ ተገቢና መሆን ያለበት ተግባር ነው። የጤና ባለሙያው መስፍን እንደገለፀው በአካባቢው ነዋሪዎች በልማቱ ሊያምኑበትናፍላጎታቸውን ባገናዘበ ሁኔታ መሰራት አለበት።
ለዚህም መንግሥት ከሚዲያ ባለፈ እታች ድረስ ወርዶ ከነዋሪው በተለይም ጉዳዩ ቀጥታ ከሚመለከታቸው ጋር ግልፅ ውይይት በማድረግ ማስረዳትና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይገባዋል። ሌላው የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ነዋሪ ከሽሮ ሜዳ አፍንጮ በርን አቋርጦ፣ በራስ መኮንን የሚያልፈው ወንዝ ዳር ነዋሪ የሆኑት አቶ አየለ ተፈሪ ናቸው። እንደ አቶ አየለ አስተያየት በልማቱ በኩል ምንም አይነት ቅሬታም ሆነ ተቃውሞ የለም። ሆኖም እንዴት፣ መቼ እና ወዴት? የሚለው ነው ጭንቀታቸው። የምኖረው የገዛሁት መሬት ላይ በሰራሁት መኖሪያ ቤቴ ውስጥ ነው።
በቤቱ ላይ ብዙ ገንዘብ አፍስሼበታለሁ። ሁሉም ነገር ለዘለቄታው በማሰብና እዚሁ ኑሮዬን ለመግፋት የመሰረትሁት ነው። አሁን ልማቱ ይህን እንዴት ነው የሚፈታው ነው ጥያቄዬ የሚሉት አቶ አየለ የባለቤትነታቸው መብት ሊከበር፣ ካሉበት አካባቢ ሳይርቁ ምትክ ሊሰጣቸው እንዲሁም ወጪያቸው ሊሸፈን እንደሚገባ ነው የሚናገሩት። ይህን በተመለከተም ግልፅ የሆነ መረጃ ስላልደረሳቸውም ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ መኖራቸውን ይገልፃሉ። ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት ከወዲሁ አንድ ነገር ሊለን ይገባል የሚሉትና በግል ስራ የሚተዳደሩት አቶ አየለ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር መምከርን አጥብቀው የሚሹ መሆናቸውንም ይገልፃሉ።
ኑሮዬ የተመሰረተውና ሥራዬን የማከናውነው በዚሁ አካባቢ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው የምንነሳ ከሆነ የመነሳቱንና እንደገና ጎጆ የመውጣቱን ጉዳይ ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን መንግሥትን አሳስበዋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የ“ለሸገር ገበታ” አስተባባሪ የሆኑትን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን አዲስ ዘመን አነጋግሯል። እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስተያየት ፕሮጀክቱ አሁን ያለው በሀሳብ ደረጃ ነው። እንዴት ይተግበር፣ የነዋሪዎች ሁኔታ ምን መሆን አለበት፣ መብትና ጥቅማቸውን በተመለከተ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፎ ምን መምሰል አለበት እና በመሳሰሉት ላይ እስካሁን ምንም የተደረገ ውይይትም ሆነ የተደረሰበት ውሳኔ የለም።
ወደፊት፣ ጊዜውን ጠብቆ በእያንዳንዱ የፕሮጀክቱ ዝርዝር ይዘት፣ ሂደትና አፈፃፀም ላይ ከህዝቡ፤ በተለይም በወንዙ ዳርና ዳር ከሚኖሩት ጋር ጥልቅ ውይይት ይደረጋል። ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳብራሩት ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች ካሉ መታረም አለባቸው። ምክንያቱም በመንግሥት በኩል እከሌ ይነሳል፤ ይህንን ያህል ሜትር (ግራና ቀኝ) ይሸፍናል፣ ጥልቀቱና ርዝመቱ የሚለው የመንግሥት መረጃ አይደለም። በመሆኑም ኅብረተሰቡ እነዚህንና ሌሎች የተሳሳቱ መረጃዎች ሲያጋጥሙት በጥንቃቄ ሊያይ፤ ምንጩንም ሊያጣራ ይገባል።
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ዋና ዋና የሚባሉትን የከተማዋን መሰረታዊ ችግሮች ይፈታል የሚሉት ዲያቆን ዳንኤል እነዚህ ችግሮችም የጤና፣ የአካባቢ ደህንነትና ስጋት፣ የከተማዋ የነዋሪዎችን ድህነትና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ሰፊ የስራ እድል፤ የዘመናዊ ሆቴሎች፣ መዝናኛዎች፣ ቤተ-መፃህፍቶች እና የመሳሰሉ ተቋማት እጥረቶችን ሙሉ ለሙሉ ይቀርፋል ይላሉ። ፕሮጀክቱ 56 ኪሎ ሜትር ርዝመትን የሚሸፍኑ ሁለት ወንዞች የሚኖሩት ሲሆን፤ የአንደኛው ወንዝ ርዝመት 27 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር፣ የሌላኛው ደግሞ 23 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር መሆኑ ታውቋል። 29 ቢሊዮን ብር ወጪን ይጠይቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሲሆን ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም የስራ እድል እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
ግርማ መንግሥቴ