ትናንት ከወትሮው በተለየ ማለዳ ነበር ወደ ሥራ ገበታዬ ያቀናሁት። ቀድሞ በየጎዳናው መጥረጊያቸውን ይዘው የዘወትር ተግባራቸውን የሚከውኑት የጽዳት ሠራተኞች እምብዛም አይታዩም፤ ይልቁንም በየአካባቢው በርከት ያሉ ሰዎች መጥረጊያና አካፋ ይዘው በጽዳት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ነገሩ እንግዳ ባይሆንም በዚህ ልክ ማልዶ ይጀመራል የሚል ሀሳብ አልነበረኝም። በዚህ መልኩ የህዝቡን ህብረትና ትጋት ከቆሻሻው ክምር ጋር እያገናዘብኩ፤ የኤኖቬሽንና ቴክኖሊጂ ሚኒስቴር ደረስኩ። በስፍራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተገኝተው የጽዳት ተግባር እያከናወኑ ሲሆን፤ በአካባቢው ካለው ሠራተኛና ነዋሪ በተለየ መልኩ ታዳጊ ህጻናት ላይ የሚታየው ድባብ ልዩ ነው።
ከእነዚህ ታዳጊዎች መካከል የጠቅላይ ሚንስትሩ የጽዳት ተግባር ሳይሆን በስፍራው መገኘት ልዩ ስሜት የፈጠረባቸው የ11 እና 12 ዓመት ታዳጊዎቹ አለማየሁ መድህን እና ደሳለኝ ያዕቆብ ይገኙበታል። ታዳጊዎቹ በፈገግታ ታጅበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርጉትን ለማድረግ አካፋ ሲይዙ ወደ አካፋ፣ መጥረጊያ ሲይዙ ወደ መጥረጊያ፣ አረም መንቀያ ሲይዙም ያንኑ ለማድረግ ይታትራሉ። ይሄን ማግኘት ባይችሉ እንኳን እጃቸው የቻለውን ያክል ቆሻሻውን እያፈሱ ወደ ማጠራቀሚያ ያግዛሉ። ታዲያ እኚህ ታዳጊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦታው መገኘት ብሎም አካባቢያቸውን ማጽዳት ከእለታዊ ደስታ ያለፈ ነገን በተሻለ መንገድ ለመጓዝ እንዲመኙአድርጓቸዋል።
ታዳጊዎቹ እንደሚሉት፤ አካባቢ ያቸው እምብዛም ንጹህ ያልሆነ ይልቁንም ለታዳጊዎች ምቹ ያልሆነ ድባብ አለው። በዚህም መጫወትም ሆነ ደጅ ላይ ቁጭ ብሎ ጊዜን ማሳለፍ የሚችሉበት እድል አልነበራቸውም። ይሄን ቢያደርጉ እንኳን ለጉንፋንና ሌሎች በሽታዎች ሲጋለጡ ቆይተዋል። በእለቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ተገኝተው ማጽዳትም አካባቢያቸውን ንጹህ ማድረግና ደስተኛ መሆን እንደሚቻል አስገንዝቧቸዋል። ሌሎች አካባቢዎች ላይ ያሉ ጓደኞቻቸውም እንደነሱ ማጽዳት እንዲችሉ ለመንገርም ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህ ታዳጊዎች ባልተናነሰ ደስታ ውስጥ ሆነው የሚያጸዱት አቶ በድሩ አለዊ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አካባቢ ከሚገኙ የሸራ ቤቶች በአንዱ ውስጥ ነዋሪ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የጽዳት ጉድለትን አስከፊነት እንደነርሱ በተጎሳቆሉና በሸራ በተወጠሩ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በላይ የሚረዳው የለም። እርሳቸውም በቤታቸው ዙሪያ ያሉ ቆሻሻዎችን በየጊዜው የሚያጸዱ ቢሆንም፤ ጽዳት የአንድና ሁለት ሰው ትግል ሳይሆን የሁሉንም የጋራ ጥረት የሚጠይቅ እንደመሆኑ በሚፈልጉት መልኩ አካባቢያቸውን ንጹህ ማድረግ አልቻሉም። አሁን ላይ ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ በስፍራው ተገኝተው በዚህ መልኩ ማጽዳታቸው እርሳቸውም የበለጠ አካባቢያቸውን እንዲያጸዱ አነሳስቷቸዋል። አቶ በድሩ እንደሚሉት፤ ጽዳት ግለሰብን፣ አካባቢን፣ ህብረተሰብን ብሎም አገርን የሚገልጽ ነው። አካባቢን ከማጽዳትና በንጹህ አካባቢ ከመኖር በላይ የሚያስደስት ነገርም የለም።
ውስጥ ሲደሰት ደግሞ ሰዎች መልካም የማሰብ፣ ለሌሎች ፍቅር የመስጠትና ከክፋት የመራቅ ስሜትን ያሳድራሉ። በእለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ጭምር ራሳቸውን ሳይቆጥቡ አብሮ በመስራትና ልባዊ ሰላምታ በመስጠት በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ የሚገኝ ሰው ዝቅ ብሎ ህብረተሰቡን ማገልገል እንዳለበት የሚያሳይ ተግባር አከናውነዋል። ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ ተከትለው ቢያንስ በየደጃፋቸው ያለን ቆሻሻ በማጽዳት ንጹህ አካባቢን የሚፈጥሩበትንና ህሊናቸውንም ከክፉ ነገር የሚያርቁበትን መንገድም አሳይተዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቢሮ ጽዳት ሠራተኛ የሆነችው ወጣት ይመኙሻል ጩበሮ እንደምትለው፤ በመስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥም ሆነ በቢሮዎች ውስጥ ያለው የጽዳት ሁኔታ በጣም ጥሩ ነው። የጽዳት ሠራተኞችም በጥሩ ሁኔታ ነው የሚያጸዱት። ይህ ደግሞ ለጽዳት ሠራተኞቹም እርካታን፤ አጠቃላይ ለመስሪያ ቤቱ ሠራተኞችም ደስታ የሚፈጥር ድባብን አላብሷቸዋል። ሆኖም የተቋም ውስጥ ጽዳት ብቻውን የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን አይዘልም። እናም የተቋሙ ሠራተኞች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ መሰረት በማድረግ የሚኒስቴር መስሪያቤቱን አካባቢ የማጽዳት ዘመቻ ጀምረዋል።
ይሄም ከግቢው ውጪ የነበረውን ያልጸዳ አካባቢ ንጹህ ለማድረግ ያስቻለ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም የዚሁ ተግባር ተሳታፊ በመሆናቸው ጽዳቱ እንደ ግቢው ሁሉ ያማረ እንደሚሆን እምነት አሳድራለች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አካባቢው ሄዶ ከእነርሱ ጋር ዝቅ ብሎ ማጽዳት ደግሞ ለስራቸው የበለጠ አቅምና መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል። “ጽዳት የውስጣዊ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ማንነት መገለጫ ነው” የምትለው ወጣት ይመኙሻል፤ አካባቢን ማጽዳትም ከራስ ባለፈ ለሌሎች ደህንነት መጨነቅን ስለሚያሳይ፣ በተቋማትም ሆነ በየመንደሩ የሚታየው የጽዳት ሁኔታ በዛ አካባቢ ያለን ሠራተኛ ወይም ነዋሪ ባህሪና ማንነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ትናገራለች። ጽዳት፣ የጽዳት ሠራተኞች ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው ተግባር መሆኑን በመገንዘብም ሰዎች በቢሮም ሆነ በሰፈር አካባቢ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ለጽዳት ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ትመክራለች።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠሩት አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ መሰረት በሰፈራችን የሚኒስቴሩ ሰራተኞችና ሁሉም የሥራ ሃላፊዎች ባሉበት፤ የአካባቢውን ነዋሪዎች ባሳተፈ መልኩ የፅዳት ዘመቻ ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የቀድሞ ተቋማቸውን አካባቢ ለማጽዳት በስፍራው መገኘታቸው በሠራተኛውም ሆነ በአካባቢው ነዋሪ ላይ ልዩ ስሜትን ፈጥሯል። መነሳሳትንም አሳድሯል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሾሙ ጀምሮ ሲናገሩ የነበረውን በተግባር የመቀየር ሂደት ውስጥ ናቸው። ይቅርታን፣ አንድ መሆንን፣ ህሊናን ማንጻትን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ማጠናከርን፣ ወዘተ እንደሚቻል እያሳዩ ናቸው። ከዚህ ባለፈም ሰው አካባቢውን ሲያጸዳና ንጹህ ነገር ሲያይ ውስጡ ይጸዳል፤ ንጹህ ይሆናል።
የጽዳት ንቅናቄው በዚህ መልኩ ተቃኝቶ ነው የሚካሄደው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠራው ይህ አካባቢንና ከተማን የማጽዳት ብሎም የሸገር ፕሮጀክት የሰው ህሊናን ንጹህና መልካም የሚያስብ የማድረግ ጅማሮ ነው። ምክንያቱም ሰው አካባቢው ንጹህ ሲሆን፤ ልብሱን ንጹህ ማድረግና ቆሻሻ ነገሮችም መጥላት ይጀምራል። የውስጥና የውጭ ነገር የተገናኘ እንደመሆኑም፤ ይሄው ስሜት ወደ ውስጡ ይገባና በጎ ያልሆነ አስተሳሰብና ተግባራትን መጠየፍ ይጀምራል። እናም የተጀመረውን ነገር የራስ ሥራ አድርጎ መውሰድ፤ ከቤት፣ ከቢሮዎችና ሰፈሮች ጀምሮ ንጹህ ማድረግ፤ ልብስና ሰውነትንም ንጹህ ማድረግ፤ በዚህ ሳይወሰኑም ንጹህነትን ወደ ውስጥ ማስረጽ ይገባል።
ቆሻሻ ሲከማች ጥሩ ያልሆነ ሽታ እንደሚፈጥር ሁሉ፤ መጥፎ ሀሳብም ሲጠራቀም መጥፎ ተግባርን ይወልዳል። በመሆኑም ቆሻሻን ሳይጠራቀም፤ መጥፎ ሀሳብም ሳይከማች መጽዳት ይኖርበታል። በዚህ መልኩ አካባቢ ሲጸዳ ውስጥ ይጸዳል፤ ውስጥን ሲጸዳ ደግሞ መልካም ሀሳብ ይመነጫል፤ መልካም ምግባርም ይወለዳል። ይህ ግን ስላሰቡትና ዝም ብሎ ስለተቀመጡ የሚመጣ ሳይሆን ከልብ ተነሳስቶ በመስራት የሚፈጠር ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውም የግቢውን ንጽህናም ወደ አካባቢው ለማውጣትና የተሻለ ለማድረግ የሚሠራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
ወንድወሰን ሽመልስ