የተባባሪዎቹ ጉዞ እስከ የት?

ጊዜው ሳብ ቢልም አብዛኛው ሰው ያስታውሰዋል ብዬ አስባለሁ። በአንድ ወቅት ድንገት ደርሶ በተዛመተ ጭምጭምታ ጨው ከሀገር ሊጠፋ ነው የሚል ወሬ ተወለደ። ይህ እንደዋዛ ሽው ያለ መረጃ ታዲያ ውሎ አድሮ እየገዘፈ ከአብዛኞች ጆሮ ደረሰ።

በወቅቱ ወሬውን የሰሙ ሁሉ ጨው ፍለጋ በየቦታው ባዘኑ። ይህ የበዛ ፍላጎት የገባቸው ነጋዴዎች ታዲያ የተለመደ ሥራቸውን ለመጀመር አልዘገዩም። ከየቦታው የነበረን ጨው በጆንያ ደብቀው ለጠየቃቸው ሁሉ ‹‹የለም›› ማለትን ደጋገሙ።

ይህን አጋጣሚ ከእውነታ ያገናኙ አንዳንድ ሸማቾች ጉዳዩን ያባብሱት ያዙ ። ጨው ሲጠየቅ ‹‹የለም›› መባሉ ከምድረ ገጽ ለመጥፋቱ ማሳያ አድርገው ወሬውን አራገቡት። ባልተለመደ ሁኔታ ጨው ትኩረት ስቦ የገበያው ቅመም ሆኖ ሰነበተ። የሚገርመው እንዲህ መሆኑ ብቻ አልነበረም ። ጨው ፈልገው የጠየቁ አንዳንዶች በከባድ ኪሎ እያስመዘኑ የወሰዱትን ጥሬ ጨው በየቤታቸው ማከማቸታቸው አነጋጋሪ ሆነ።

ጉዳዩ ካለፈ በኋላ አብዛኛው ሰው በአግርሞት ሲወያይበት እንደሰነበተ አስታውሳለሁ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለቤታችን ከምንገዛው አቅርቦት ጥቂት ዋጋና ትንሽ ፍላጎት ያለው ጨው ነው ቢባል ውሽት ነው አያሰኝም። የዛኔ የሆነውን ጉዳይ መለስ ብለን ካሰብነውም ይህን የሚያገናዝብ አእምሮ ጠፍቶ አልነበረም።

በተለምዶ ገበያው ላይ የሚነሳው አጉል ወሬ ግን በአብዛኞቻችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህን ተለምዶ ተከትለን በተጓዝን ጊዜም ራሳችንን ለችግር አጋልጠን ለስግብግብ ነጋዴዎች ፍላጎት ጭዳ እንሆናለን። ወደዘንድሮ ጉዳይ መለስ ስንልም ይህ አይነቱ እውነታ ከእኛው ጋር መቀጠሉን አናጣውም።

ሁሉም እንደሚያውቀው ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ዕለታዊ የገበያ ዋጋ ሽቅብ ጉኗል። እንደሁኔታው ከሆነ ይህ ጉዳይ ከዛሬ ነገ ይሻላል የሚሉት አልሆነም። ዛሬ የተጠየቀው ዕቃ ነገ ይቀንሳል፣ የሚሉት አይደለም። እንደውም በተቃራኒው የጠዋቱ ለምሽት በእጥፍ ጨምሮ ይገኛል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ገበያውን የሚቆጣጠርና የሚያረጋጋ አካል አይኖርም። አንዳንድ ነጋዴዎች ያለ አንዳች ምክንያት እንዳሻቸው ዋጋ ሲጨምሩ የሚቃወማቸው አለመኖሩ ደግሞ የተጠቃሚውን አቅም እያዳከመው ነው።

በቅርቡ በጤፍ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ የብዙዎችን ጓዳ አንገዳግዷል። ይህ አጋጣሚ በተለይ ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል እየጎዳው ለመሆኑ የምናየው ሀቅ ነው። ትናንት በርካታው በአቅሙ መጠን የሚገዛውን የጤፍ ፍጆታ ዛሬ ላይ ማሰቡ ዘበት ሆኖበታል።

አሁን የተጠቃሚውን ፍላጎት ዝቅ አድርጎ የሚያወጣውን ገንዘብ ሰማይ የሰቀለው ሁሌም የምናነሳሳውና መላ ያጣንለት የኑሮ ውድነት ሆኗል ። ይህ አጋጣሚ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም እንደጥላ ሲከተለን ኖሯል። ነገም መፍትሄና መላው ካልተበጀ አቅማችን የማይገዘግዝበት አንዳች ምክንያት አይኖርም።

በገበያው ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ሸማቹን የሚንገላቱት ስግብግብ ነጋዴዎች ብቻ አይደሉም። ይህን የችግር መረብ አወሳስበው ተጠቃሚውን ጠልፈው የሚጥሉት የወቅቱ ደላሎች ጭምር ናቸው።

እነዚህ አካላት የሀገሪቱን ገበያ በእጃቸው ለማስገባት የሚያህላቸው የለም። የራሳቸው ጥቅም እስከሞላ ድረሰ የሌላው እስትንፋስ መኖር አለመኖር ጉዳያቸው ሆኖ አያውቅም። የእነሱ ችግር እንዳለ ሆኖ የአንዳንድ ሰዎች ድርጊት ደግሞ ችግሩን እያባባሰው ይገኛል።

እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ሁልጊዜም ከገበያው መሃል አይጠፉም። ኑሮ ተወደደ ፣ ዋጋ ጨመረ፣ ዕቃ ጠፋ በተባለ ቁጥር ቀድመው ለመግዛት ተሸቀዳዳሚዎች ናቸው። ችግሩ ይህን ማድረጋቸው አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ በተባሉት ዋጋ ለመግዛት ዓይናቸውን አለማሸታቸው እንጂ።

እነዚህ ሰዎች ልምዳቸው በዚህ ብቻ አይገደብም። ገንዘቡ እስካላቸው ድረስ ከታሰበው በላይ እያጋበሱ ያከማቻሉ። ይህን ማድረጋቸው ለሌላው ጎረቤታቸው ተጽዕኖው የሰፋ ነው። ምንጊዜም ወቅቱን አሳበው ስለሚያከማቹ ለስግብግቦቹ ነጋዴዎች ተንጋለው የሚታረዱ ናቸው ። ነጋዴዎቹ ሁሌም እነሱን መሰል ገበያ ደፋሪዎች ስለማያጡ ሌላው ጠየቀ፣ ቀረ ደንታቸው አይሆንም። ያከማቹትን ቀን ቆጥረው እየመመዘዙ ለጠየቃቸው በእጥፍ ይሸጣሉ። እግረመንገዳቸውንም የነገን አስከፊነት እየሰበኩ ኪሳቸውን ያደልባሉ።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በዚህ አይነቱ እውነታ ላይ ዋናውን ጡብ እያኖሩ ያሉት ‹‹አቅሙ አለን›› የሚሉ አንዳንድ ሸማቾች መሆናቸውን ነው። እንዲህ አይነቶቹ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ‹‹ስለ ነገ አርቀን እናስብ ›› ባዮች ናቸው።

በቅርቡ የጤፍ ዋጋ ሽቅብ በወጣ ጊዜ አብዛኛው ሸማች ሲያስብ ፣ ሲጨነቅ ከርሟል። እንጀራ በልቶ ማደር ግድ ሆኖበትም ፍላጎቱን በአቅሙ እያጣፋ እንደነገሩ መሆኑን ልብ ይሏል። ይህን የሚያደርገው ለዛሬ እንጂ ስለነገ የሚለውን አቅም ገበያውና ነጋዴው ነጥቀውታል።

ከገበያው መሀል ቀድመው የሚገኙት እነ እንቶኔ ግን ሃሳባቸው ዛሬ ላይ ብቻ አይደለም ። ስለነገ ሕይወት አብዝተው መጨነቅ ልምዳቸው ነው። በእነሱ ቤት የሚያድጉ ልጆች፣ የሚኖሩ ቤተሰቦች ነገን ያለችግር እንዲሻገሩ ክምችታቸው ጣራ ነክቷል። ጎተራቸው ሞልቶ ፈሷል። አንዳንዴ እነዚህን ሰዎች ጠጋ ብሎ ለጠየቃቸው የሚሰጡት ምላሽ ተመሳሳይ ነው።

‹‹ነገ ጦርነት ቢኖር ፣ ችግር ቢመጣ፣ የሚገዛ፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ ቢጠፋ … ›› እያሉ ይቀጥላሉ። እነሱ ይህን ይበሉ እንጂ ለሕገወጦች ከመመቸት ባለፈ ነገ ይዞት የሚመጣውን ችግር የተረዱት አይመስልም።

አይበለውና እነሱ የሚያስቡት አይነት ጦርነት አልያም ሌላ ችግር ቢከሰት ካከማቹትን እህል አንዳች ቅንጣት ማንሳት አይችሉም ። እነሱ እየበሉና እየጠጡም ጎረቤታቸው በርሃብና በችግር አይሞትም ።

የሚነግራቸው ጠፍቶ እንጂ ችግር ሲመጣ ያለ ችግር አይደለም። ለነገው ጥጋብ ያከማቹት አህል፣ የሠሩት ጎተራ ደጀን አይሆናቸውም። የቤታቸው ማግኘት ብቻውን ሰላም ፈጥሮ ዕንቅልፍ አያስተኛቸውም።

ዛሬ ላይ ለደረስንበት የገበያ ቀውስ እንዲህ አይነቶቹ ‹‹አለን›› ብለው ባይቀድሙ ነገሮች ሊለወጡ በቻሉ ነበር። የአብዛኛው ሸማች ፍላጎት በአንድ ተጣምሮ የገበያውን ሜዳ መቆጣጠር ቢችል ሕገወጦች እንዳሻቸው አይናኙም። አንድ ተብላ የምትጨመረው ሳንቲም ውላ አድራ በብር ስትመነዘር ዝምታው ባያይል ኖሮ የዛሬው ችግር ባልመጣ፣ ባልባሰም ነበር።

ሸማቹ ለሕገወጦች ትከሻ ማበጥ ማገር እየሆነ መቀጠሉ ዋጋ እያስከፈለን ነው። ሁሌም ገበያው ላይ የማንሞክረው ‹‹እምቢ›› ባይነት የደላሎች መፈንጫ አድርጎናል። ገበያውን በይሁንታ ይዘው በገንዘባቸው የሚያዙ አንዳንዶች ደግሞ በአንድም በሌላም ለኑሮ ውድነቱ አባሪ፣ ተባባሪ ሆነዋል።

ይህ አይነቱ ጉራማይሌ ሕይወት በርካታውን ነዋሪ እየጎዳ ለችግር ዳርጎታል። እንዲህ አይነቱ የገበያ ልማድ መዳበሩም ከመፍትሄው ጥግ ሳያደርሰን ዘመን ወለድ ክፋት እያስፋፋብን ይገኛል ። ‹‹ጉዳዩ ሊታሰብበትና .መላ ሊባል ይገባል ›› ማለት ደግሞ መልዕክታችን ነው።

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You