አቶ አሽኔ አስቲን ተወልደው ያደጉት ጋምቤላ ክልል መዣንግ ዞን ሚንጌሺ ወረዳ ሶኔይ ቀበሌ ሲሆን በወቅቱ አካባቢው ላይ ትምህርት ቤት ስላልነበረ እድሜያቸው ለመማር ቢደርስም ትምህርትን ያገኙት ካደጉ በኋላ ነበር። ካደጉ በኋም አካባቢው ላይ ጄይን አንደኛ ደረጃ ትምህትርት ቤት በመከፈቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው አምስተኛ ክፍል ደረሱ። ስድስተኛ ክፍልን ለመማር ከአካባቢያቸውና ከቤተሰባቸው ራቅ ብለው መሄድ ነበረባቸውና ጉደር ወረዳ ሜጢ ከተማ በመሄድ የስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የጀመሩ ቢሆንም ከተማው ላይ አስጠግቶ ሊያስተምራቸው የሚችል ዘመድ ስላልነበራቸው በቀን 30 ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በወቅቱ መንግሥት በትምህርት ወደኋላ የቀሩ ክልሎችን ለመደገፍ በአዲስ አበባ ከተማ የጎልማሶች አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲከፈት አድርጎ የነበረ በመሆኑና አቶ አሽኔ በትምህርታቸው ጎበዝ ስለነበሩ በዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት የመማር እድልን አገኙ።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ ላይም ከአፋር ፤ቤኒሻንጉል፤ ጋምቤላ ከመጡ ጎበዝ ተማሪዎች ጋር በመሆን ከስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ቀጠሉ። 12 ክፍል ደርሰውም ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቃቸውንም ተከትሎ ረዳት መምህር (አሲስታንት ሌክቸረር ) በመሆን በዩኒቨርሲቲው አገለገሉ ፤ በመቀጠልም ወደክልላቸው በመሄድ የትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ በመሆን ሰሩ። በመቀጠልም የንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ሃላፊ ፣ የክልሉ አፈጉባኤ፣ የድርጅት ጽህፈት ቤት ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በድጋሚም የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሃላፊ በመሆን ተሹመው ሠርተዋል።
ኋላም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ገብተዋል። ከስራቸውና ከትምህርታቸው ጎን ለጎንም ለክልላቸው ልማት ለህዝቡ ተጠቃሚነት ብዙ የሠሩ ሲሆን አግባብ ያልሆኑ አስተዳደራዊ ሥራዎች ሲያጋጥማቸው መንግሥትን ይሞግቱም ነበር። ለውጡ ከመጣ በኋላ ሁሉም ፓርቲዎች አንድ ሲሆኑ አቶ አሽኔም አዲስ አበባ የፓርቲ ጽህፈት ቤት የሱፐርቪዝን ጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ሃላፊ ሆነው ተሾሙ።
ከዛም በምርጫ ወቅት ክልልቸውን ወክለው በመሳተፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተቀላቀሉ። በምክር ቤቱም የአማካሪዎች ኮሚቴ አባል በመሆንና ሀገራቸውን እንዲወክሉ በምክር ቤቱ ተመርጠውም የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባልና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊም ናቸው። እኛም በተለይም ወቅታዊ በሆነው ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ አቶ አሽኔ አስቲኒን የዘመን እንግዳ አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የፓን አፍሪካ ፓርላማ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆነው እንደማገልገልዎ የፓርላማ ዋና ዓላማና ሥራ ምንድን ነው ከሚለው እንጀምር?
አቶ አሽኔ ፦ የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላት ከየሀገራቱ የተመረጡ አምስት አምስት ሰዎች ሲሆኑ የሚመርጣቸውም የየአገራቸው ፓርላማ ነው። እነዚህ ሰዎች ጉባዔ ከመመሥረት ጀምሮ ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝደንታቸውን ይመርጣሉ። የሽግግር ሂደት ስላለውም ጉባዔው ያንን ተከትሎ በመሄድ የአፍሪካ ጉዳዮችን ዋና አጀንዳው አድርጎ ያያል።
በሌላ በኩልም ፓርላማው የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የተቋቋመ እንደመሆኑ ዋና ሥራውም አፍሪካን ማስተሳሰር ነው። ፓርላማውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕግ አውጪ አካልም በመሆን የሚያገለግል ነው። በዚህም እቅድ በጀት የሚያጸድቅ አፍሪካ ህብረት የሚሠራቸውን ሥራዎች አጀንዳ የሚቀርጽም ነው።
አዲስ ዘመን፦ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዘረኝነት ሳይሆን ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው ሲሉ ይደመጣሉና ይህ እንደው ምን ማለት ይሆን?
አቶ አሽኔ፦ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዘረኝነት ሳይሆን ብሔርን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ብሔርና ሰፈርን ሽፋን ያደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ መሆኑን ማወቅ ይገባል ። ኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኝነትን (Racism) እና ብሔርተኝነትን (Ethnicity) አቀላቅሎ የማየት ችግር ይስተዋላል ። ነገር ግን ሁለቱ ጉዳዮች ፈጽሞ የተለያዩ ቢሆኑም በእኛ ደረጃ እየታየ ያለው ችግር አብዛኞቻችን ፖለቲከኛውም ሌላውም ሌላውም አንድ ሃሳብ ሲያዝ ጠለቅቆ ሳይመረምሩ እንዳለ መውሰድ ይታያል። ይህ መሆኑ ደግሞ አንድ ሰው አንድን ሃሳብ አነስቶ ስለተናገረ ብቻ ያንን ተከትሎ ማስተጋባት ይስተዋላል። ከስር መሠረቱ መመርመር ላይ ከባድ ክፍተት አለ። ይህ መሆኑ ደግሞ አሁን የገባንበት ችግር ውስጥ እየጨመረን ነው።
በሌላ በኩልም በእኛ ሀገር ዘረኝነትና ብሔርተኝነት በጣም ግራ የሚያጋቡ ሃሳቦች ሆነዋል፤ ዘረኝነት ምንድነው? የሚለው ነገር በአግባቡ ያልተጠና ከመሆኑም በላይ ሃሳቡን መሠረት ተደርጎም ለማህበረሰቡ ግልጽ የሚያደርጉ ሰዎች የሉም። በመሆኑም ይህ ሁኔታ ሰዎች የተለያዩ ችግሮች ሲደርስባቸው በዘሬ ተጠቃሁ ፤ በዘሬ የተነሳ ተገደልኩ ፤ ተገለልኩ የሚሉ ሃሳቦችን ያንጸባርቃሉ ። እነዚህ ግን እውነት ሳይሆኑ በፖለቲካ ቁማር የተቀቡ ሃሳቦች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል።
እነዚህን ሃሳቦች ግን በትኩረት ማየትን ይጠይቃል፤ ለምሳሌ ዘረኝነት ምንድን ነው? የሚለውን ብናይ፤ ዘረኝነት አሁን ላይ ቃሉ ፓለቲካዊ ቀለም ስለተቀባና የሆነ አንድ ነገር ጋር ስለተያያዘ ትንታኔው ብዙ ነው። ዘረኝነት ከዘር ጋር በተገናኘ የሚመጣ ሃሳብ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅት ሃሳቡ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል አካባቢ እየተቀነቀነ ያለ ሃሳብ ነው። ምንጩ ከአውሮፓውያኑ ሆኖ ሳለ እነሱም ይሉት የነበረው አንዳንድ ዘሮች ከሌሎች የተለዩ ናቸው በማለት የአንድን ማህበረሰብ የፊትና የዓይን ቀለምን መነሻ የሚያደርግ ቀጥሎም ወደጄኔቲክ በመግባትና በመለያየት የአንዳንድ ዘር ከሌላው ዘር የተሻለ ነው የሚል ሃሳብ ያንጸባርቁ ነበር። እነሱ ግን እንደዚህ ያደርጉ የነበረው የነጭን የበላይነት ለማሳየትና ጥቁሮችን ለመጫን ነበር።
በተመሳሳይ ብሔርተኝነትም ፖለቲካዊ ቃል ሆኖ ቃሉ ራሱ ሲጠራ የተፈረጀበት ነገር ትዝ የሚለው ሰው ብዙ ነው። በመሆኑም ብሔር በትርጉሙ አንድ ቋንቋ ባህልና የራሱ ማንነት ያለው ማህበረሰብ መጠሪያ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀነቀነ ያለው ዘረኝነት ልንለው አንችልም፤ ይልቁንም ተንሰራፍቶ ያለው ብሔርተኝነት ነው። በሌላ በኩልም እኛ እንደምናስበው ሀገራችን ውስጥ እየተቀነቀነ ያለው ነገር ዘረኝነት ቢሆን ኖሮ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር አይጋባም፤ አይዋለድም፤ አብሮ አይኖርም ፤ አንድ መስሥሪያ ቤትም አይሠራም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የዘረኝነት ጉዳይ እኛ እንደምናስበው ቀለል ያለ ባለመሆኑ።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በዘራቸው ምክንያት ጥቃት እየደረሰባቸው አይደለም ?
አቶ አሽኔ፦ በዘረኝነት ምክንያት ጥቃት ደረሰብኝ የሚሉ ሃሳቦች እንደሚቀነቀኑ ይታወቃል። ይሁንና በዘሬ ምክንያት ጥቃት ደረሰብኝ የሚሉ ሰዎች በብሔር ምክንያት አሊያም በሃይማኖትና በጎሳ የተነሳ በተቧደኑ ሰዎች ችግር የደረሰባቸው ናቸው። ይህ የሚያሳየው ሀገራችን ውስጥ ዘረኝነት ሳይሆን ብሔርን ማዕከል ያደረገ ሽኩቻ መኖሩን ነው። ዘረኝነት ። አንተ ጥቁር ነህ፤ አንተ ነጭ ነህ። በሚል አሊያም እንደናዚዎች የእኛ ደም ከሌላው የተለየ በሚል እራስን የበላይ ለማድረግና ሌላውን ለማግለል የሚደረግ ጥፋት ነው።
ዘረኞች በአፓርታይድ ጊዜም ሆነ በተለያዩ ዓለማት በተነሱበት ወቅት እነሱ የሚጠቀሙበት የሃይማኖት ተቋም አሊያም የገበያ ስፍራቸው ውስጥ ሌላው እንዲገባ አይፈቅዱም ነበር። ብሔርተኝነት በአንጻሩ የፖለቲካ ፍላጎቴ አልተሟላም የሚል አካል ሃይማኖትን፣ ጎጠኝነትን፣ ቋንቋን ምክንያት በማድረግና ቡድን በመፍጠር ዓላማውን ለማሳካት የሚመርጠው አካሄድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ብሔርን መነሻ አድርጎ የሚቀነቀኑ የፖለቲካ ፍላጎቶች አሉ፤ እነዚህ ፍላጎቶች አንድ ወገንን መደበቂያ በማድረግ የሚፈጸሙ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል።
አዳዲስ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ እንኳን ብሔርን መሠረት አድርገው ነው፤ ይህ የሚሆነው ፖለቲከኞች በቀላሉ የሕዝብን ቀልብ ለመግዛት የሚመቻቸው ማንነትን ወይም ብሔርን መሠረት አድርገው በሚሰራጩ መረጃዎች መሆኑን በማወቃቸው የተነሳ ነው። በመሆኑም ችግሩ ከታወቀ ለመፍትሄው ብሔርተኝነትን መሠረት ያደረገውን ችግር ለመቀነስ ምን መሠራት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው ነገር የፖለቲካ ጉዳይ ነው። ይህም ማለት በተለይም በ19 ኛ ክፍለ ዘመን ዘመናዊው የኢትዮጵያ የአስተዳደር ሥርዓት ሲመሠረት ጀምሮ የኢትዮጵያን ብዝሃነት የመቀበልና ያለመቀበል ችግር ነው። በተለይም ቀደም ባሉት መንግሥታት የአካታችነት ችግር ነበር። አስተዳደሩም ወደአንድ መስመር ያጋደለ በመሆኑ በወቅቱ ብዙ ችግሮችን ፈጥሯል። እየቆየም ሲሄድ በተለይም አካታችነት ላይ በሚፈጠሩ ክፍተቶች ምክንያት የመደብ ትግል ነው የተጀመረው፤ ይህም ሲባል በሥልጣን ላይ ያለው አካል ራሱን ብቻ ይዞ ሌላውን ጭሰኛ በማድረግ ይገለጽ ስለነበር ትግሉም በእነዚህ መካከል ነበር።
ከ1966 ዓ.ም አብዮት በኋላ ሌሎች ፍላጎቶች መጡ፤ እነዚህም የብሔር ጥያቄዎች ናቸው። እነ ኦነግ ሕወሓትና ሌሎችም ይህንን ጉዳየ ማቀንቀን ጀመሩ ፤ እነዚህም ቡድኖች እንደ ብሔር ታሪካዊ ጭቆና አለብን ብለው ተነሱ፤ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ፓርቲዎች በብሔር መደራጀት ጀመሩ፤ እንደዚህ እያሉም ደርግ ሥልጣኑን ተቆጣጠረ፤ በኋላም ደርግ ሥልጣኑን በሀይል ሲለቅ የመጣው አደረጃጀት በብሔር የተደራጀ ነበር። በመሆኑም እሱ ደርግን ለማስወገድ አንድ ብሔር ሆኖ ስለመጣ ሥልጣን ከያዘ በኋላም በተመሳሳይ ሌሎችን ማደራጀት እንዲደራጁም መፍቀድ ነበረበትና ይህንን የተጠቀሙም ሁሉም በራሱ ቋንቋና ብሔር ፓርቲ ሆኖ መመሥረት ጀመረ።
ይህ መሆኑ ደግሞ መፍትሄ ሳይሆን የመጣው ብሔርን መሠረት ተደርገው የሚቀነቀኑ የጥቅም ፍላጎቶች ናቸው የመጡት። በመሆኑም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመጣ የህዝብን ስሜት አገኛለሁ ብሎ ከሚራመድባቸው መንገዶች አንዱ ብሔርን መያዝ ሆነ።
አሁንም በየአካባቢው እያየናቸውና እየሰማናቸው ያሉ ችግሮች ዘርን ማዕከል ያደረጉ ናቸው ይባላል ፤ ይመስላሉም። ነገር ግን እንደዛ አይደለም። ዛሬ ችግሩን የዘር አስመስለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ነገ የሚፈልጉት ነገር ሲሟላላቸው ዘር ይሉት የነበረውን ነገር ሲተውት እናያለን።
በመሆኑም አሁን ላይ ሀገራችን ላይ ያለው ችግር ዘርን መሠረት ያደረገ ሳይሆን ዘር የሚለውን ነገር እንደመጠቀሚያ የመውሰድ አዝማሚያ ነው። ይህንን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ግለሰቦች ይጠቀሙበታል።
እንደው ይህ የዘር ጉዳይ አሁን አሁን እስከሚያስገርም ድረስ በሰው ውስጥ የተዛባ ትርጓሜ ስለተሰጠው ለሥራ ቅጥር ያመለከተ ሰው እንኳን ማሟላት የሚገባውን የመጨረሻ መስፈርት ሳያሟላ ቢወድቅ በዘሬ በብሔሬ ምክንያት ነው ፈተና ማለፍ ያልቻልኩት በማለት ቅሬታውን የሚያሰማበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። በጠቅላላው ግን ብሔርና ዘርን እንደ ፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሣሪያነት መጠቀም እየተለመደ መጥቷል እንጂ እንደ ሀገር ዘረኝነት የሚባለው ነገር የለም። በሚባለው ልክ ቢኖር ኖሮ ሰዎች እርስ በእርሳችን እንጨራረስ ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ ስለዚህ በሀገራችን ላይ ዘረኝነት የሚባለው ነገር የለም ማለት እንችላለን?
አቶ አሽኔ ፦ በሀገራችን ላይ የሌለውን ችግር አምጥተን ለመሰቃየት መፈለጋችን በራሱ አስገራሚ ነው። ምክንያቱም ዘረኝነት የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንም ልንረዳ የሚገባን ነገር የተወለድንበት ብሔር ወይንም ደግሞ እንደሚባለው ዘር የእኛ ፍላጎት ሳይሆን የተፈጥሮ ሕግ ያስገደደችን ነው፤ ማንም ስለፈለገ ኢትዮጵያዊ አልያም አሜሪካዊ ሆኖ ሊወለድ አይችልም፤ ይህንን ጠንቅቆ መረዳት ይገባል።
በመሆኑም ከችግራችን ልንወጣ የምንችለው ፈልገን መርጠን ያልተወለድንበትን ብሔርና ዘር መሰዳደቢያ እንዲሁም የችግር ምንጭ ከማድረግ ይልቅ በመከባበርና በአብሮነት በመኖር መቀጠሉ እንደ ሀገርም እንደ ህዝብም ብዙ ርቀት መሄድ እንችላለን።
አዲስ ዘመን ፦ አንዳንድ ሰዎች ይህ ብሔርና ዘር የሚባለው ነገር የችግራችን ሁሉ ምንጭ በመሆኑ በተለይም ብሔር ብሎ ነገር በመታወቂያ ላይ እንኳን እንዳይገለጽ ይታገድ የሚሉ አሉና እንደው ይህ ምን ያህል መፍትሔ ሊሆን ይችላል?
አቶ አሽኔ፦ አዎ አንዳንዶች እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያራምዳሉ፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር ወጥ ይሁን ብሎ መነሳት በራሱ ሌላ ችግር ነው፤ ብሔር የሚባለው ነገር በሕግ ይታገድ እንደሚሉት ዓይነት ርምጃ መውሰድ ኢትዮጵያ ውስጥ አይሰራም። ከዛ ይልቅ ግን ተፈጥሯዊ ማንነታችን አክብረንና ተከባብረን መኖሩ ነው የተሻለው አማራጭ።
ለመፍትሄውም ብሔርተኝነትን ማዕከል አድርገው የሚመጡ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን ማስቀረትና በብሔር ላይ ተመርኩዘው የሚመጡ የአካታችነት ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በስፋት መጠቀም ይገባል። የብሔር ማንነቶችና የቋንቋ ልዩነቶች ያሉና ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው ፤ ስለዚህ አካታችነትን በተለያዩ መስኮች ላይ ማስፋት ያስፈልጋል። በተለይ የወል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የብሔር ጥያቄ በማንሳት አሊያም የማንነትና የቋንቋ ሁኔታን በማንሳት ለሚመጡ ሰዎች የሚስተናገዱባቸውን የሕግ ማዕቀፎች ከወዲሁ በማዘጋጀት አካታችነትን ማጎልበት ይገባል ። አንዳንዶች ዘረኝነት ነው አካታች እንዳንሆን ያደረገን፤ ችግራችን እሱ ነው ይላሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋነኛ ችግር በዘረኝነት ስም ወይም በሰፈር ስም የሚቀነቀን የፖለቲካ ሽኩቻ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ይህ መከባበር እንዲመጣስ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ አሽኔ ፦ ትልቁ ነገር የሃሳብ አመንጪዎች ለነገሩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ፖለቲከኞች፤ የሃይማኖት አባቶች፤ ምሁራን ፤ሲቪክ ማህበረሰብና ህዝቡ የሚያመነጩትን ሃሳብ ገንቢ በሆነ መልኩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩል በሁሉም የእምነት ተቋማቶቻችን ላይ የመከባበርና የመቻቻል እሴታችን ትልቅ ሥራ ሊሰራበት የሚገባ ነው። ሌላው ፖለቲከኞች ምን ጊዜም ከአንደበታቸው የሚያወጡት ቃል ገንቢም አፍራሽም ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባቸዋል።
በመሆኑም እንደ አገር ፓርቲ ስንመሠርት ራሱ ነጻ አውጪ ንቅናቄ እያልን ታርጋ የምንሰጥ ፖለተከኞች መቆጠብ አለበን፤ አሁን ነጻ የሚወጣም ሆነ የሚነቃነቅ ማንነት ላይ አይደለም ያለነው፤ ከዛ ይልቅ ግን ከብሔርና ዘር ውጪ አስበን ሀገራችንን የጋራችን መሆኗን ተረድተን በዛ ማዕቀፍ ውስጥ የሚያስኬዳትና ለችግሮቿ መፍትሔ የሚሆን ሃሳብ ማመንጨት መቻል አለብን።
ነገር ግን ብሔሬን ነጻ አወጣለሁ ተብሎ የሚመሠረት የፖለቲካ ፓርቲ አስገራሚ ከመሆኑም በላይ ከማንስ ነው ነጻ የሚያወጣው የሚለውም ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካል ሥርዓት ለብሔር አደረጃጀት የሚመች አይደለም። በብሔር ተደራጅቶ የሚመጣ የፖለቲካ ፓርቲም በፍጹም አሸናፊ ሊሆን አይችልም።
እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር አደረጃጀት አያስፈልግም ሲባል ብሔሮች ተደፈጥጠው አንድ ይሆናሉ ማለት ሳይሆን የራሳቸውን ቋንቋ ይጠቀማሉ ፤ ይሠራሉ፤ ነገር ግን ፓርቲዎቻችን። ሁሉን ያቀፉ የሁሉንም ሃሳብ የሚቀበሉና እንደ ሀገር አሻጋሪ ሃሳቦችን የሚያፈልቁ ሊሆኑ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት ሃሳብ ካለ?
አቶ አሽኔ፦ ብሔርና ዘር ላይ ትኩረትን አደርጎ መኖር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፤ ምክንያቱም ሀገር የምትለማውና የምተቀጥለው የተለያዩ የሀገሪቱ ዜጎች በሚያዋጡት ሃሳብ እና በሚያደርጉት ተሳትፎ ነው።
አሁን ያለንበት የፖለቲካ ሁኔታም ይህ የተዛቡ ነገሮች ያመጡት ውጤት በመሆኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ እርስ በእርሳችን ተከባብረንና አንዱ አንዱን ተቀብሎ የሚኖርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፤ ይህ እንዲሆን ፖለቲከኞች ትልቅ ድርሻ ሊወጡም ይገባል።
ህዝብና ህዝብ ዘሬ ፤ብሔሬ ሳይባባል ለዘመናት አብሮ የኖረ ፣ የነገደ ፣ የሠራ ፣ የተጋባ ፣ የደገሰ፣ የበላ፤፣ የጠጣ ፣ የተዋለደ አሁንም ድረስ አብሮ ተቻችሎ እየኖረ ያለ ነው፤ ነገር ግን ፖለቲከኞች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ከእውነት የራቀ ነገርን በመፍጠር ህዝቡን ወዳልተገባ መንገድ እየመሩት ነው። ደጋግሜ እንደነገርኩሽ አሁን ለሀገራችን የሚያስፈልጋት ሁሉን አካታች የሆነ ሥርዓት ነው ፤ ይህ ሲባል ደግሞ ብሔረሰቦች ይጠፋሉ አህዳዊ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነም በደንብ ሊሰመርበት ይገባል፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ የህዝቦች ደህንነትና ሰላም የተጠበቀ ፍትሃዊ ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት አግባብም እየተፈጠረ ይሄዳል ማለት ነው።
እንደ ሀገር ገና ያልመለስናቸው በርካታ የመልማት ጥያቄዎች ቢኖሩም ፖለቲከኞች በተለያየ ጊዜ በሚያቀብሉን አጀንዳ እየተጠለፍን የልማትን ጉዳይ ችላ ያልነው ይመስላል። በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች አግባብነት ያለው ምላሽን ሊያገኝ ይገባል። እንደውም ሰዎች ወይም ህዝቦች የልማት ጥያቄያቸው በተመለሰ መጠን ብሎም መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ከተሟሉ እነዚህ ፖለቲከኞች የሚያቀብሏቸውንም አጀንዳዎች ማራገቡ ላይ ፍቃደኛ አይሆኑም ፤ አሁን ግን ፍላጎት ባልተሟላበት ሁኔታ ህዝቡ ብሔርህ፤ ዘርህ ተነካብህ ሲባል ሆ ብሎ ይነሳል።
እስከ አሁን በሀገራችን ላይ በትንሽ ደረጃም ይሁን በትልቅ ደረጃ የተነሱ ያለመግባባቶች ላይ ጥናት ቢደረግ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ብሔር ወይም ዘር ሳይሆን የተጠቃሚነትና የመልማት ጥያቄዎች ናቸው፤ እነዚህን ችግሮች ደግሞ ፖለቲከኞች በደንብ ስለሚመቻቸው ይጠቀሙበታል።
አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ አሽኔ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2016