የትወና የበዓል ፕሮግራሞች

ጥሎብኝ ሚዲያ መከታተል በጣም እወዳለሁ። ከልጅነቴ ጀምሮ ሬዲዮ ተለይቶኝ አያውቅም፤ አሁን ደግሞ ዘመኑ ያመጣቸውን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና ቴሌቭዥን እከታተላለሁ። ይህን የምለው የኔን ታሪክ ለመናገር ሳይሆን ሚዲያ ለመከታተል የተገደድኩበትን ልማድ ለመናገር ነው፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ፕሮግራሞችን እያቀያየርኩ አያለሁ።

በተለይ የበዓል ሰሞን ገና ከማስተዋወቂያው ጀምሬ ነው የተጠቀሰበትን ሰዓት በጉጉት የምጠብቅ፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት ይሆኑና ይደራረቡብኛል። እኔ የምመርጠው የቴሌቭዥን ቻናል ሳይሆን የፕሮግራም ይዘት ነው። በሁለት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሁለት የወደድኳቸው ፕሮግራሞች በተመሳሳይ ሰዓት ከሆኑብኝ የአንደኛውን አይቼ የአንደኛውን ደግሞ የሚደገምበትን መጠበቅ ነው፤ ወይም በዩትዩብ ገጻቸው ላይ እስከሚጫን መጠበቅ ነው። የበዓል ቀን የወደድኩትን ፕሮግራም ለማየት ብየ የተጠራሁበት ቤት እንደማልሄድ ብናገር የሚያምን ይኖር ይሆን?

ጥሪው ጋ ብሄድ የምሄድበት ቤት የቴሌቭዥን ፕሮግራሙን በጽሞና መከታተል ስለማልችል ወይም እኔ የምፈልገው ቻናል ላይ አድርጉልኝ ማለት ስለማልችል ነው የማልሄደው። የሚያዝናናም ሆነ የሚያስተምር ብቻዬን ነው ማየት የምፈልግ፤ ይህ የእኔ የግል ልማድ ስለሆነ ልክ ላይሆን ይችላል።

በዚህ ሚዲያ የመከታተል ልማዴ ውስጥ ግን የተቸገርኩት ነገር ቢኖር እንደ ብዙ ጓደኞቼ ንቆ መተው አለመቻሌ ነው። ‹‹አሁንም ቴሌቭዥን ታያለህ?›› የሚሉኝ ብዙ ናቸው። አንድ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ጠቅሼ ‹‹ለምን እንዲህ ይደረጋል?›› ብየ ትዝብቴን ሳጋራ ‹‹ለምን ታያለህ?›› የሚል መልስ ነው የሚሰጠኝ። የሚያሳዝነው ነገር ይህን የሚሉት ራሳቸው የፕሮግራም አዘጋጆች ጭምር ናቸው። ስለፕሮግራሞቻቸው ከአድናቆት ውጭ የሆነ የግሳጼ አስተያየት ሲሰጣቸው ‹‹ለምን ታየዋለህ?›› የሚሉ አሉ። የሀገራችንን ሚዲያዎች ሕፀፅ ማስተካከል የሚቻለው ችግሩን በመንገር እንጂ ባለማየት አይደለም!

የበዓል ሰሞን በተለይም በቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ላይ የሚበዛው ከጣቢያው ይልቅ በተባባሪ አዘጋጆች የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ናቸው። እነዚህ ፕሮግራሞች የሚዘጋጁት በብዛት በታዋቂ ሰዎች ነው። ሰዎቹ ታዋቂ ስለሆኑ ስፖንሰር ያገኛሉ። የስፖንሰር አድራጊዎች መስፈርት ደግሞ ከፕሮግራሙ ጥራት ይልቅ የስፖንሰር ጠያቂዎቹ ታዋቂነት ይመስላል። እዚህ ግባ የሚባል ምንም ፍሬ ነገር ሳይታይ አንድ ሰዓት ወይም ሁለት ሰዓት ሙሉ ይባክናል። ይህን ስል ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ መሻሻሎች መኖራቸውን ሳልክድ ነው።

ከበዓል ፕሮግራሞች ሁሉ ሁሌ የሚገርመኝ ግን አድማጭና ተመልካችን የሚያጭበረብሩበት መንገድ ነው። በተባባሪ አዘጋጆች የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ከበዓሉ ከረጅም ቀናት (ምናልባትም ሳምንታትና ወራት) በፊት የሚቀረጹ ናቸው። የሚተላለፉት ግን የበዓሉ ዕለት ነው። በበዓሉ ዕለት በሚተላለፈው ፕሮግራም የሚያወሩት ስለባህሎቻችን አኩሪነት ነው። በበዓል ቀን ስለሚደረጉ ነገሮችና እነዚያ ነገሮች የሚደረጉት የበዓል ቀን ብቻ መሆኑን በኩራት ይናገራሉ። እነርሱ ግን ያደረጉት ከበዓሉ ከብዙ ቀን በፊት ነው።

ለምሳሌ፤ ስለመስቀል የሚያወሩ ከሆነ በ 16 ደመራ እንደሚደመር፤ በ 16 ለምን መብራት እንደሚበራ ያብራራሉ። ከዚያም ደመራ እንደምር ብለው ወደተዘጋጀው ደመራ ችቦ እያበሩ ይሄዳሉ። ያ ፕሮግራም የቀጥታ ሥርጭት አይደለም። በተባባሪ አዘጋጆች ከቀናት በፊት የተቀረጸ ነው። ይሄ ትወና ነው። ከዚህ ይልቅ በ16 ደመራ እንደሚደመር፣ በ17 መስቀል መሆኑን እየጠቀሱ ስለመስቀልና ደመራ ሙያዊ ማብራሪያ መስጠት ወይም አዝናኝ ፕሮግራሞችን ማቅረብ ይሻል ነበር። የደመራ ሥነ ሥርዓቱን ራሱ ጣቢያው በቀጥታ ሥርጭት ያሳያል፤ ከዚያ በኋላ የተቀረጸውን ያሳያል።

ይህ ችግር የለውም እንበል። እንደ ፋሲካ ባሉ በዓላት ደግሞ ከተፈቀደው ቀን ውጭ እርድ የሚፈጸምባቸው ፕሮግራሞች ይታያሉ። አሁንም ያ ፕሮግራም የቀጥታ ሥርጭት እንዳልሆነ ይታወቅ! የፋሲካ በዓል የኦርቶዶክስ አማኞች ሁለት ወር የሁዳዴ ጾም ጾመው የሚፈስኩበት ነው። ፕሮግራሞቹ የተሚዘጋጁትም ይህንን በዓል ምክንያት በማድረግ ነው። ስለዚህ የዚህ በዓል ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ባህልና ሃይማኖታዊ ሕግጋት መጠበቅ አለበት ማለት ነው።

እንደ ግለሰብ አንድ የኦርቶዶክስ አማኝ በጾም ወቅት ሥጋ ሊበላ ይችላል፤ ሊያርድ ይችላል። ይህ ግን እንደ ግለሰብ ነው። በዓሉ የሚከበረው በእምነቱ ተከታይ ስለሆነ የእምነቱ ተከታዮችን ባህልና ሃይማኖታዊ ሕግጋት ማሳየት አለበት። በኦርቶዶክስ አማኞች በሁዳዴ ጾም ውስጥ አይታረድም። ለፋሲካ በዓል ፕሮግራም ቀርጸው የሚያስተላልፉ አካላት ግን የሚያርዱት በሁዳዴ ጾም ውስጥ ነው ማለት ነው። መቼም ቅዳሜ ሌሊት ከ9፡00 በኋላ ቀርጸው ለጠዋት አደረሱት ሊባል አይችልም።

አንዳንዱ ደግሞ ልብ ብለው ከሰሙት ፈገግታን ያጭራል። ከሳምንት በፊት በተቀረጸ ፕሮግራም ‹‹የዛሬውን በዓል እንዴት አየኸው?›› እየተባባሉ ያወራሉ። ጠያቂውም መላሹም ስለበዓሉ ድምቀት፣ በየመንገዱ ስላለው ድባብ ያወራሉ። አያደርገውና በበዓሉ ዕለት እንደታሰበው ባይሆንስ? እርግጥ ነው በዓላት ገና ከሳምንት ጀምሮ ድባባቸው ያምራል። የዕለቱን መናገር ግን በጣም የተጋነነ ትወና ይሆናል።

እንዳልኩት ይሄ ነገር በስፋት የሚታየው በተባባሪ አዘጋጆች ነው። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ እንደ ጣቢያው በፈለጉት ጊዜ የመቅረጽ ሙሉ ግብዓትና ቦታ ላይኖራቸው ስለሚችል ነው። ምናልባትም በግለሰቦች አቅም የሚሠራ ስለሚሆን ነው። ጣቢያው በዓሉ አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ብቻ ሲቀረው ሊቀርጽ ይችላል። በዕለቱም በጋዜጠኞች የዕለቱን ሁነት መናገር ስለሚችል ነው።

ሌላው የበዓል ሰሞን የፕሮግራሞች ማድመቂያ ደግሞ የምርትና አገልግሎቶች ማስታወቂያ ነው። እነዚህ የበዓል ሰሞን ማስታወቂያዎች የሚታጀቡት በበዓል ሰሞን ዘፈኖች ዜማ ነው። እዚህ ላይ ታዲያ የምንታዘበው በተለይም የሕዝብ የሆኑት የሥነ ቃል ግጥሞች ይቀየራሉ። በእርግጥ የሚቀየሩት አዝናኝ ለማድረግ ሲባል ነው። ዳሩ ግን አሁን ላይ ያለው ትውልድ ምናልባትም ትክክለኛው ይሄኛው (በማስታወቂያ የተነገረው) ሊመስለው ይችላል። ይህ ሆነ ማለት ትውፊቱ ተዛባ ማለት ነው። የሕዝብ የሥነ ጽሑፍ ሀብት በአንድ ተቋም ፍላጎት ተቀየረ ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ትክክለኛውን የሕዝብ ዜማ አስታውሰው ከዚያ በኋላ የራሳቸውን ተቋም ማስተዋወቅ ይሻል ነበር።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በአዝናኝነትም ሆነ በአስተማሪነት በጣም ተወዳጅ ፕሮግራሞች መኖራቸውን ሳልዘነጋ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ብዙ መነቃቃት እንደፈጠሩ በቅርቡ አድናቆታችንን አስነብበናል። እንደዚያ አይነቶቹ እንዲቀጥሉ፣ በተመልካች ዘንድ የተሰለቹት ደግሞ እንዲስተካከሉ አዘጋጆች አስተያየቶችን ልብ ሊሉ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መስከረም 19/2016

Recommended For You