ዛሬ ከትናንት እንዲሻል

የአይሁድ ዝርያና የደች ዜግነት ያለው ታዋቂው የፍልስፍልና ጠቢብ ባሩች ስፒኖዛ Baruch Spinoza ‹‹ If you want the present to be different from the past, study the past/ዛሬ ከትናንቱ የተሻለ እንዲሆን ከፈለግክ የትናንቱን በሚገባ አጢነው/››የሚል አባባል አለው፡፡ ይህን አባባል በተለይ አዲስ አመትን ስንጀምር ይበልጥ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ወደ አዲስ አመት ስንሸጋገር ካለፈው ልምድና ተግባራችን ትምህርት መቅሰም እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ይሁንና አንዳንዶች በአሮጌ አመት የሠሩትን ስህተት በአዲሱ አመትም ደግመው ሲሠሩ ራሳቸውን ያገኙታል። ይህም ያለፈውን ልምዳቸውን የመለየትና ለመፍትሔ የመራመድ ፍላጎትም ሆነ ልምድ ስለሌላቸው የሚከሰት ስለመሆኑ እርግጥ ነው፡፡

ዛሬ ላይ ሆኖ የትናንት ተግባር ምን ጠቀመን? ስህተቱስት ምን አስተማረን? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ትክክለኛውን መልስ ፈልጎ ማግኘት የቻለ ግን ከዚህ ቀደም የጨበጠውን እሳት ዳግም እንደማይጨብጠው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡፡

የዘመን በዘመን የጊዜ በጊዜ መተካት የማያቋርጥ ሂደት ቢሆንም አዲስ ዓመት ሰው ከራሱ ጋር ይታረቅ ዘንድ እቅዱ ከግቡ እንዲስማማ ውጫዊና ውስጣዊ ሕይወቱ እንዲጣጣም ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ አዲስ ዓመት የሰው ልጅ ራሱን የሚያሻሽልበት ያለፈውን ሕይወቱን ገምግሞ ደካማውን ሽሮ ጠንካራውን ይዞ እንዲቀጥልበት ለራሱ የፈጠረው የቀን ቀጠሮ ነው፡፡

አዲስ አመትም ራስን ለመለወጥ፣ አስተሳሰብን ለማደስ፣ አኗኗርን ለማስተካከል፣ ለማሰብና ለማሰላሰል ዕድል ይሰጣል፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሰው ባሰመረው የጊዜ ድንበር ለአዲስ አመት ሁሌም አዲስ ያስባል፡፡

ኢትዮጵያውያንም 2015 ዓ.ም አሮጌ ብለው ሸኝተው አዲሱን 2016 ዓ.ም ተቀብለዋል፡፡ አዲስ አመትም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዲስ ቃል የሚገቡበት ዕለት ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው መጪው ጊዜ መልካም እንዲሆን፤ ኑሮው እንዲሳካ ጎጆው እንዲሞላ፣ መንፈሱ እንዲረካ፣ አዕምሮው እንዲሰላ፣ ነፍስያው እንዲጠግብ፣ የውስጡም የውጭውም ሕይወቱ እንዲያምር ያቅዳል፡፡

ለአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያንም እውነተኛው የአዲስ ዓመት ትርጉሙም አዲስ ሰውነት፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ የሕይወት መንገድ የሚበጅበት፣ ለራሳችን ቀና አስተሳሰብ የምንቀይስበት በአጠቃላይ አዲስ የምንሆንበት የአዲስነት የጅማሮ ቀን ነው፡፡

አዲስነት የትናንቱን ድካም፤ ያለፈውን አጉል ልማድ መድገም ሳይሆን አዲሱን ኑሮ በአዲስ ሰውነት፣ በሰለጠነ አስተሳሰብና በቀናነት መጀመር ነው፡፡ አዲስነት በግንዛቤ መበልጸግ፣ በጥበብ መጎልመስ፣ ራስን በመቆጣጠር መርቀቅ ጭምር ነው፡፡

አመቱ አዲስ እንዲሆን ደግሞ አዲስ ሰው መሆንን የግድ ይላል፡፡ አዲስን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ እንደማይጨምሩት እና አዲሱና አሮጌው እንደማይስማሙ ሁሉ ሰው በአዲስነት ካልተቀበለው አዲስ አመትም የቁጥር ለውጥ ብቻ ይሆናል፡፡

ይሁንና በዘመን ሂደት በትውልድ ቅብብል የማይጠቅምን አስተሳሰብን ማራመድ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ጉዳቱ ግልፅ ነው፡፡ አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚነጣጥል፤ መሰብሰብን ትቶ የሚበትን፣ ከማዋሃድ ይልቅ የሚለያይ አስተሳሰብን ማራመድ ኪሳራ እንጂ ትርፍም የለውም።

እንማ መታወቅ ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ቢኖር ማሰብ መቻል ልዩ ፀጋ ነው። መልካምን ሃሳብን መርጦ መተግበር ደግሞ ሰው በራሱ ላይ የሚያመጣው በረከት ነው። ማንም ለሆዱ የሚስማማውን ምግብ እንደሚመርጠው ሁሉ ለአዕምሮውም የሚመጥን ሃሳብን መመገብ ራስን መጥቀም ነው።

ንፁህ ምግብ ሰውን ከበሽታ እንደሚከላከለው ሁሉ ንጹህና መልካም ሃሳብም ሰውን አፍራሽ ተልዕኮ ካለው ተግባር ያቅበዋል። ሰው ሃሳቡን እያበጠረ ገለባ ሃሳቡን የሚያስወጣበትና ጠቃሚውንና ፍሬ ሃሳቡን የሚያስቀርበት የሕሊና ወንፊት መሥራት ይገባዋል። ሃሳብ እንደስንዴ እንክርዳድ ካልተጣራ ንጹሁንም ሃሳብ ያበላሻል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ትናንት በሃሳብ ቀድመን ከፍ ከፍ እንዳላልን ዛሬ አዲስ ሃሳብ መሥራት፣ ሃሳቡን ማርቀቅ፣ ሃሳቡን ማጎልመስ፣ ሃሳቡን በተሻለ ሃሳብ መጣል፣ ሃሳቡን ማድመቅ የሚያስችል ባህል ጠፍቶብናል። ትናንትም ሆነ ዛሬ እየተመላለሰ የሚደቁሰንና አዙሪት ሆኖብን ወደፊት አላንቀሳቅስ ያለን ችግራችንን በአስተሳሰብ ልዕልና ተነጋግረንና ተወያይተን ፍቱን የሆነ መፍትሔ ማስቀመጥ አለመቻላችን ሆኖም ይታያል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ያለፈው ዓመት ደስታና ኀዘን ተስፋና ፍርሀት ድልና ትግል የተፈራረቁበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የምንሰማውና የምንናገረው የምንፈልገውን ብቻ ሆኖ በጥቂቱ አውቆ በብዛት መደምደም፣በከፊል ሰምቶ በሙሉ መፍረድ፣ መርጦ በመመልከትና በመስማት ሳይመርጡ ማውገዝ የሁላችንም መገለጫ ሆኖም ታይቷል፡፡

ይህን ታሪክ በአዲስ አመት መለወጥ ይኖርብናል። ኢትዮጵያውያን በአዲሱ አመት ካለፈው ተምረን መጪውን ለማሳመር በተለይም ሀገር ሠላም እንድትሆን ካሳለፍናቸውም መልካም ሆነ እኩይ ታሪኮች ተምረን መጪውን ለማሳመር ማድረግ ያለብን ብዙ ነው፡፡

ኢትዮጵያችን በአዲስ አመት አዲስ አስተሳሰብ ያለው ዜጋን ትፈልጋለች፡፡ የሚክሳት እንጂ የሚከሳት አያስፈልጋትም፡፡ ዘመን የሚዋጅ፣ ትውልድን እንደ አዲስ የሚቀርፅ ትውልድ ትባጃለች፡፡ ትንሳኤዋን የሚሻ፣ ወደ ኋላ የሚጎትትና የማይጠቅም አስተሳሰብ በአዲስና በተሻለ አስተሳሰብ መለወጥ የሚችል ዜጋን ትናፍቃለች፡፡ ሊገነባ፣ ትውልድ ከፍ ከፍ ሊያደርግ የሚችል አስተሳሰብ ትሻለች።

በአዲስ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ ፀጉር ከመንጨት፣ ሃሳብ ማመንጨት እናስቀድም፡፡ ከመቆላለፍ መተላለፍን፣ ከመተናነቅ፣ መደናነቅን እንምረጥ፡፡ የአምናውን ዕዳ አንውረስ። የአምናውን ክፋት አንጨርስ፡፡ አዲስ ጎዳና ይተለም። አዳዲስ ፈትል ይቀለም፡፡ ተከፋፍሎ መፍረስ ይብቃ፡፡ ለቆጡ ተንጠራርተን የብብቱ አያምልጠን፡፡

የእብደቱ መንገድ ቁልቁለቱ፣ በዘር ሀረግ መለቃቀም፣ በእምነት ጥላ መጠቃቀም ይብቃን፡፡ በሰውነት እንከባበር። ማድላት ማግለል እንቅበር፡፡ ቅን እናስብ። ቅን እንናገር፡፡ አፍና ልባችን አንድ ይሁን፡፡ ወጥመዱን ሁሉ እንበጥስ፡፡ ተንኮሉን ሁሉ እናፍርስ፡፡

በአዲሱ አመት በአስተሳሰብ ለውጥ ‹‹እኛ እነሱ››፣ ‹‹የእኛና የእነርሱ›› የሚል ዘረኛ ቀይ የጎጥ መስመር ከማጋደም እንቆጠብ፡፡ በብሔር መነፅር ተሸፍነን ‹‹እንዲህ ነን›› ስላልን ‹‹እንዲያ›› እንደማንሆን እንገንዘብ። የባንዲራ ክብር ይታየን፡፡ በጎጥና መንደር የጠበበ ሰው አስፍቶ ማሰብ ይሳነዋልና ከጎጥ አስተሳሰብ እንገንጠል፡፡

ምግባርና ተግባር የጎደለን፣ የሚጨበጥና የሚያዝ የሌለን አንሁን፡፡ ኅሊና ያድሰን፡፡ ሰውነት ይመልሰን። ሃይማኖት ይፈውሰን፡፡ የሀገር ፍቅር ድምጽ ይሠማን። ሁሉንም ወቃሽ ከመሆን እንቆጠብ፡፡ ‹‹ተበድያለሁ›› ከሚል በደል ቆጣሪነት እንፋታ፡፡ ከተገፊነት ተረክ እንላቀቅ፡፡ከሚያነቃቅፈን ይልቅ የሚያስተቃቅፈንን እንምረጥ፡፡ ቃልና ተግባራችን ይመጣጠን፡፡

በአዲስ አመት ባለፈውና ባሳለፍነው አጉል ጊዜ መቆጨትን ማቆም እና ለወደፊቱ መሻልን ማሰብ ልንጀምር ይገባል፡፡ ከማፍረስ ይልቅ መካብ ሊቀለን፣ ይገባል። ኋላቀርነት ሊማርከን፣ መጥፎ ታሪክ ሊጎትተን፣ ዘመን ሊያድሰን፣ ክፉ ትናንት ሊቀይረን አይገባም። ከመጥበብ መስፋትን እንምረጥ፡፡ ለሕዝብ የማይበጅ የሴራ ፖለቲካ መጎንጎን ማቆም አለብን፡፡

በአዲስ አመት በዚህ አስተሳሰብ ለመቃኘና አስተሳሰቡን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ለዚህ የሚመጥን ጭንቅላት መፍጠር ግድ ይለናል። አስተዋይ ጭንቅላት አንድም ከመጽሐፍ ማሕፀን በንባብ ምጥ የሚወለድ፤ አንድም ትናንትን በማስተዋልና የኋላ ታሪክን ተጠቅሞ በበጎ እሳቤ በመለወጥ እውን እንደሚሆን ልንረዳም ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ከቻልን የተሻለችና በሁሉም መስኮች የተሳካላት ኢትዮጵያን ማየት ህልም አይሆንብንም፡፡

አዲሱ አመት ምንም ልንለውጠው ከማንችለው ትናንት ይልቅ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ልናደርግበት በምንችልበት ነገ ላይ እንረባረብ፡፡ ስለትናንትና አበክረን ስንናገር ዛሬና ነገ እንዳያመልጡን እንንቃ፡፡ መጪው ዓመት ያለፈውን እያስታወስንና እያወሳን የምንጋጭበት ሳይሆን መጪውን እያለምንና እየተለምን በአንድነት በፍቅር ተደምረን የምንፈስበት ጨርሶ የመጀመር ዓመት ይሁንልን፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You