የ 25 ዓመቱ ወጣት ራጉኤል በላይ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ አንድ ዓመት ሆኖታል።ወጣቱ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልምድ የለውም። አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ፊልም በማየት ነው። አመጋገቡም ያገኘውን ነው። በሂደት ያጋጠመው የሰውነት ክብደት መጨመር ለእሱ ምቾት እንጂ ስጋት አልነበረም። ሆኖም ሰውነቱ እንደልብ አልታዘዝ ሲለው፤ ሆዱ አካባቢ ከፍተኛ ውጋት ሲሰማው የህክምና ተቋማትን በር ሊያንኳኳ ግድ ሆነ። ከጤና ባለሙያው የተነገረው « ከፍተኛ የስብ ክምችት በሰውነቱ መኖሩ ነው»። የሰውነቱ መወፈር የምቾት ቢመስለውም የዕድሜ ማሳጠሪያ መሆኑን የተገነዘበው ያኔ ነው። ዶክተር ሳልሃዲን መሃመድ በቢታንያ ልዩ ክሊኒክ የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት የስብ ክምችት «ትራንስ ፋቲ አሲድ» ፈሳሽ የሆነ የምግብ ዘይት ወይም ቅቤ በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋ ሲደረግ የሚፈጠር የስብ ዓይነት ነው።
እንደ ቅቤ የረጉና ጠጣር የምግብ ዘይቶችን መመገብ የደም መጓጎል በማስከተል ደም ወደ ልብ፣ አንጎል እንዲሁም ወደ የተለያዩ የውስጥ አካል ክፍሎቻችን በተፈለገው መጠን እንዳይደርስ በማድረግ ለድንገተኛ የልብ ህመም እንዲሁም በአንጎል ውስጥ ለደም መፍሰስ አደጋ ይዳርጋል፡፡
ትራንስ ፋቲ አሲድ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙትን ደህነኛ ኮሌስትሮሎች እንዲቀንሱ በማድረግ በምትኩ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ኮሌስትሮሎች እንዲበዙ ያደርጋል።ጤናማ ኮሌስትሮሎች ጠጣር የሆኑ ቅባታማ ምግቦችን ወደ ጉበት በማጓጓዝ እንዲፈጩና ከሰውነታችን በፈሳሽ መልክ እንዲወገዱ ያደርጋል።በአንጻሩ ጎጂ የኮሌስትሮል ዓይነቶች ያልተፈጨውን ቅባት በደማችን ውስጥ በማዝቀጥ ደም እንዲጓጉል ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
አርተሪዎች በኦክሲጅን በበለፀገ ደም የተሞሉ ከደም ስሮች የውስጠኛውን ክፍል በትራንስ ፋት አማካኝነት በሚፈጠር ኮሌስትሮል ከተሸፈነ ፣ ከጠበበ ወይንም ከተዘጋ ደማችን በአግባቡ መጓዝ ይሳነዋል።በዚህም ምክንያት ልብ በቂ የሆነ የደም አቅርቦትና ኦክስጂን ስለማያገኝ ለድንገተኛ የልብ ሥራ ማቆምና በአንጎል ላይ ለሚፈጠር የደም መፍሰስ አደጋ ያጋልጣል።ይህም የልብ ህመም የሚያስከትል መሆኑን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት የሥነምግብ ባለሙያ አቶ ክፍሌ ሀብቴ እንደሚገልጹት፣ የሰውነት ውፍረት በቀጥታ ከትራንስ ፋት ጋር የሚያያዝ ሲሆን በቀጥታ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣል።የሁለት በመቶ ጭማሪ ያለው የትራንስ ፋትነት ያለው ምግብ መውሰድ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች 23 በመቶ እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል።በተጨማሪም አላስፈላጊ ለሆነ ውፍረት፤ የክብደት መጨመር፤ ከፍተኛ ለሆነ የደም ግፊት፤ ለስኳር በሽታ እንዲሁም ለካንሰር ያጋልጣል፡፡
የሰው ልጅ ስጋንና ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎችን መመገብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ትራንስ ፋት ይዘት ያላቸውን ምግቦች ይወስድ ነበር ያሉት አቶ ክፍሌ እነዚህን ተፈጥሮአዊ የትራንስ ፋት አይነቶች በጮማና በሞራ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ በአግባቡ ለምግብነት መጠቀም ግን ጉዳት የለውም ብለዋል።
ባለሙያው እንዳሉት ሰው ሰራሽ ምግቦችና በፋብሪካ በተቀነባበሩ ዘይቶች 80 በመቶ ትራንስ ፋቲ አሲድ እንደሚገኝባቸው ይገመታል።ለምሳሌ በዘይት የተጠበሱ ድንችና ፈንዲሻ ፣ ጨዋማና ጣፋጭ ብስኩቶች፣ ኩኪስና ዶናቶች፣ ኬክ ውስጥ የሚጨመሩ ማጣፈጫዎች፣ የወተት ውጤት ያልሆኑ የቡና ማንጫ ክሬሞችና የዳቦ ቅቤዎች፣ በፋብሪካ ተቀነባብረው ያለፉ ወተት፣ እርጎና አይብ፣ የሚረጉ የአትክልት ዘይቶች፣ የአትክልትና ዳቦ ቅቤዎች በሰው ሰራሽ መንገድ ትራንስ ፋት ሊይዙ ይችላሉ።
በጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ተግኔ ረጋሳ እንደሚናገሩት፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አማካኝነት ነው።በተለይ በትራንስ ፋቲ አሲድ አማካኝነት ለችግር የሚጋለጡ ሰዎችን ለመታደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀገራዊ የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅቷል።ይህም እየተሰራ ያለውን ሥራ ለማጠናከርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ይረዳል ብለዋል፡፡
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለበርካታ በሽታዎች እና ያለጊዜ መሞት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
አብርሃም ተወልደ