ኢትዮጵያውያን የእኛ ከሚሏቸው እሴቶች መካከል በፍትህ ማመን አንዱ ነበር። ለዚህም «በፍትህ ከሄደ በሬዬ ያለፍትህ የሄደ ጭብጦዬ» የሚለው ብሂል እንደማሳያ ይጠቀሳል። ይህ በፍትህ ማመን አንድም የሕግ የበላይነትን ከመቀበል የመጣ ነው። ሙግት ከገጠሙት አልያም ቂም ከተያያዙት ሰው ጋር ያለገላጋይ የተገናኙ ጊዜም «በሕግ አምላክ» ተባብለው፤ ዳኝነቱን ለሕግ ትተው ይተላለፋሉ፤ ኢትዮጵያውያን።
ዘመናዊ የሕግ አሠራርና ስርዓት ባልነበረበት ዘመን ማኅበረሰቡ የተስማማበትን ያልተጻፈ ሕግ በማክበር የሕግ የበላይነትን ሲያሳይ ኖሯል። ዛሬስ የሕግ የበላይነት ከቃል በዘለለ በተግባር እንዴት እየታየ ነው? የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በትላንትናው እለት በአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ «የሕግ የበላይነት፡ ጽንሰ ሐሳቡ፣ መገለጫዎቹና የማረጋገጫ መንገዶቹ» በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።
በመድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ ሀሳብ ካቀረቡት መካከል ዶክተር ጌታቸው አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። በአንድ አገር ላይ የሕግ የበላይነት አለ ወይም የለም ብሎ መፈረጃ መንገዱ ምኁራንን በሁለት ወገን የመደባቸው እንደነበር ያነሳሉ።
በአንድ ወገን የሕግ የበላይነት አለ ለማለት የተወሰኑ መስፈርቶችን የሚያስቀምጡ አሉ። እነዚህም ሕግን በተመለከተ የሚሠሩ ተቋማትና አደረጃጀቶች በአግባቡ መኖር ላይ ትኩረት ሲያደርጉ፤ በወጣው ሕግ ተደራሽነት፣ የወደፊቱን አመልካች ስለመሆኑ፣ ግልጽነቱ፣ ነጻ ፍርድ ቤቶች ስለመኖራቸው ይጨነቃሉ። ነገር ግን አንድ ሕግ ጥሩ ነው ወይም አይደለም፤ ምን ያህል ይጠቅማል ወይም ይጎዳል የሚለውን አይመለከቱም።
በሌላ ወገን በይዘቱ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት የሚሉ ምኁራን እንደነበሩ ዶክተር ጌታቸው ይጠቅሳሉ። በመጨረሻ ታድያ የሕግ የበላይነት መኖር በሁለቱ እሳቤዎች ድምር እይታ የሚገለጽ ሆኖ ይገኛል። በአንድ ጎን መዋቅራዊና ተቋማዊ አሠራር ሲሆን በሌላ በኩል የሚወጡ ሕግ ይዘቶች አግባብነትና ትክክለኛነትን ያካትታል። ታድያ ግን በየትኛውም የዓለማችን አገር ላይ የሕግ የበላይነትን በፍጹም ያረጋገጠ አንድም አይገኝም ይላሉ።
በጽንሰ ሃሳቡ መሰረት ሕግ ማክበርም ሆነ ማስከበር የሕግ የበላይነት መታያዎች ሆነው ይቆጠራሉ። በዚህ መሰረት ደግሞ ሕግ አለማስከበርም በራሱ የሕግ የበላይነትን እንደመጣስ ይቆጠራል። ይሁንና ሕግን ማስከበር እና አምባገነንነት መካከል ያለውን ልዩነት መንግሥት ሊለይ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ሰዓት መንግሥት አምባገነን ከመሆን ለመታቀብና አምባገነንነትን በመስጋት ሕግን ማስከበር እየተሳነው መሆኑ በዚህ ሃሳብ ተጠቅሷል።
ወጣቷ የሕግ ባለሙያ አክሊል ሰለሞን በበኩሏ፤ የሕግ የበላይነት ጉዳይ ዛሬ ላይ በስፋት ርዕስ ሆኖ ይነሳ እንጂ ቀደም ብሎም የታየ ችግር መሆኑን ትጠቅሳለች። ነገሩ ዛሬ ላይ ፖለቲካዊ መልክ ሳይዝ በፊት በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አንዲት ሴት በበርካታ ወንዶች ተደፍራ ሕይወቷ ሲያልፍ፣ አሲድ ሲደፋና በደሎች ሲፈጸሙ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር። እናም የሕግ የበላይነትን መርጦ መጠየቅ አደገኛ ነገር መሆኑንም አሳስባለች።
በተጨማሪ የሕግ የበላይነትን እውን ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑ አክሊል ታስታውሳለች። በቅድሚያ ግን ማኅበረሰቡ ለሕግ የበላይነት መገዛት እንዳለበት፤ ማኅበረሰቡ ለሕግ ተገዢ እንዲሆን ደግሞ መሟላት አለባቸው ያለችውን ጠቅሳለች። ከዚህም መካከል የሕግ አውጪው ማንነትና ተዓማኒነት፣ የሕጎች በጥናት ላይ ተመርኩዞ መዘጋጀት፣ ሕግ የማስፈጸሙ ሂደት ግልጽ መሆን፣ ለሕግ የመገዛት ባህል መዳበር፣ የሲቪክ ማኅበራት እንቅስቃሴና የመገናኛ ብዙኅን ሚና እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ሞጋችነት ያስፈልጋል፤ እንደ አክሊል ገለጻ።
አሁን ላይ በአገራችን የሕግ የበላይነት እየተከበረ ነው ለማለት እንደማይቻልና ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ያነሱት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ደረጄ ዘለቀ ናቸው። ዶክተር ደረጄ እንዳሉት የሕግና የሕግ የበላይነት መተዋወቅ የሰውን ልጅ ከሰው አገዛዝ ወደ ሕግ አገዛዝ ያሸጋገረው እርምጃ ወይም ሂደት ነው። ታድያ በአገራችን የመንግሥት ስርዓቶች ሲዳሰሱ በንጉሡ እንዲሁም በደርጉ ዘመነ መንግሥት የሕግ የበላይነት አለ ባይባልም፤ የሕግ የበላይነት መርህ ዓላባውያን ነበሩ ማለት ይቻላል ይላሉ።
በኢህአዴግ ይልቁንም በህወሃት መራሹ ስርዓት የሕግ የበላይነት እንዲኖር ቢጠበቅም በተለያዩ የማስገደጃ ኃይሎች መቆየቱን ነው አያይዘው የሚያነሱት። ባለፈው አንድ ዓመት ያለው እውነታ ሲታይ ደግሞ ሕግን በአግባቡ ማስከበር ባለመቻሉ የሚታየው ክፍተት የሕግ የበላይነት ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚከተውና አልፎም የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ እንደወደቀ አውስተዋል።
ዶክተር ደረጄ ለዚህ መፍትሄ ብለው ባቀረቡት ሃሳብ፤ መንግሥት ሕግን በማስከበር በኩል ግዴታውን እንዲወጣ ማድረግና ከሌላው ጉዳይ ይልቅ የሀገር ህልውና ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። በመድረኩ ላይ በተሰጡ አስተያየቶችም የተለያዩ የሙግት ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን፤ በይበልጥ «በሕግ አምላክ» ተብሎ መፍትሄ ከሕግ እንዲገኝና ስርዓት እንዲሰፍን በመግሥት በኩል በአምባገነንነትን እና ሕግን በማስከበር መካከል ያለው ልዩነት ሊታወቅ እንደሚገባ በጉባኤው የተነሳ ሃሳብ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
ሊድያ ተስፋዬ