ወይዘሮ ውድነሽ ኤደር በአዲስ አበባ የጎዳና ፅዳት ሥራ ከተሰማራች አስራ አምስት ዓመት አልፏታል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ኑሮ በብርቱ ፈትኗታል። ከእለት ጉርስ በማታልፈው የ500 ብር ደሞዟ የላስቲክ ቤት ተከራይታ አስከፊ የድህነት ሕይወትን አሳልፋለች። የምተበላው አጥታ ፆሟን ያደረችባቸው ቀናትም ጥቂት አይደሉም። ልጇን ለማሳደግ የማትችልበት ደረጃ ላይም ደርሳ ነበር። ከወር እስከ ወር የማያደርሰው ደሞዟ ሁሌም ብድር ውስጥ እየከተታት የተብቃቃ ሕይወት እንዳትመራ አድርጓት ቆይቷል።
አሁን ግን እናት ባንክ እና ‹‹እንደዜጋ ማህበራዊ እንደራሴ›› የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ከአንድ ዓመት በፊት በጋራ ባዘጋጁት ‹‹የእናት ለእናት›› ሥልጠና መርሀ ግብር ተጠቃሚ ከሆኑ 60 እናቶች ውስጥ አንዷ በመሆኗ ሕይወቷ ተቀይሯል። በዚሁ መርሃ ግብር ሶስት አይነት ሥልጠናዎችን ወስዳለች። በወሰደችው ሥልጠና መሠረት በእናት ባንክ ከሃያ ብር ጀምሮ በመቆጠብ ከዋና ሥራዋ በተጨማሪ ሁለትና ሶስት ተጨማሪ ሥራዎችን እንድትሠራ አጋጣሚ ተፈጥሮላታል። በዚህም ከዚህ ቀደም የነበረውን ኑሮዋን በእጅጉ ማሻሻል ችላለች።
ዛሬ ላይ ወይዘሮ ውድነሽ ሥልጠናው ከምታገኘው ገቢ ላይ የቤቷን ወጪ ሸፍና የሚተርፋትን በመቆጠብ ገንዘብ በሚያስፈልጋት ጊዜ አውጥታ ለመጠቀምና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ተጨማሪ ገንዘብ እንድትበደር አስችሏል። ከዋና ሥራዋ በተጨማሪ በትርፍ ሰአቷ ቆሎ በመሸጥ ተጨማሪ ገቢም ማግኘት ችላለች። በተጨማሪም መንግሥት የቀበሌ ቤት ሰጥቷት ከቤት ኪራይ ተገላግላለች። የሚከፈላት ደመወዝም ቢሆን ከበፊቱ ተሻሽሏል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሥልጠናው ሕይወቷን በብዙ መልኩ ቀይሮታል። የሌሎቹም እናቶች እንደዚሁ።
የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ገነት ሀጎስ እንደሚናገሩት ባንኩ ‹‹እንደዜጋ ማህበራዊ እንደራሴ›› ከተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት በጎዳና ፅዳት ለተሰማሩ እናቶች ሥልጠናዎችን በመስጠትና በማደራጀት በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲያግዙ የሚያስችል ‹‹እናት ለእናት›› የተሰኘ ፕሮጀክት ነድፎ ለሶስት ወራት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህም በጎዳና ፅዳት የተሰማሩ 60 እናቶች በሥልጠናው ተጠቃሚ ሆነዋል።
በሥልጠናው እናቶቹ ገንዘብ በመቆጠብ ከሚሠሩት ዋና ሥራ በተጨማሪ ሌላ ሥራ በመሥራት እንዴት ገቢያቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ እውቀት አገኝተዋል። እንደየአቅማቸው ከሃያ ብር ጀምሮ በመቆጠብና በቆጠቡት ገንዘብ ከችርቻሮ ንግድ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል። በዚህም ኑሯቸውን ማሻሻል ችለዋል። በዚሁ ፕሮጀክት ተሳታፊ ለሆኑ ሁሉም እናቶችም ባንኩ ቤተሰባዊ የበዓል ስጦታ አበርክቶላቸዋል።
በሥልጠናው ሂደት የወረዳው ድጋፍም ጠንካራ የነበረ ሲሆን እናት ባንክና እንደዜጋ ማህበራዊ እንደራሴ በጋራ በመሆን የእናቶችን የፅዳት ሥራ በጋራ ሞክረዋል። ሥራው ምን ያህል አድካሚና ምስጋና የሚቸረው እንደሆነም ለመረዳት ችለዋል።
እንደ ዜጋ ማህራዊ እንደራሴ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እዩኤል ካሳሁን በበኩላቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከመንግሥት ፍቃድ ወስዶ ተመሥርቷል። ላለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ ለሀገራቸው የተሻለ ነገር ማበርከት የሚችሉባቸው መድረኮችን ለማምጣት እየሠራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እጣፈንታ በዜጎቿ እንደመሆኑና ዜጎቿ ደግሞ መፍትሄ ያላቸው በመሆኑ ብሎም የራሳቸው ታሪክ፣ ባህልና እውቀት ያላቸው በመሆኑ ድርጅቱ ይህን አቅም በማስተባበር አንድ ርምጃ ወደፊት ለማራመድ አበክሮ ይሠራል። ይህንንም ‹‹የእናት ለእናት›› ፕሮጀክት ድርጅቱ ሲጀምር በሁለት ዓመት ውስጥ 5 ሺ እናቶችን በኢኮኖሚ፣ ራስን በማስቻልና ሥልጠና በመስጠትና በማገዝ እንዲሁም ብድርን በማመቻቸት በተለይ በጎዳና ፅዳት የሚተዳደሩ እናቶች ባላቸው ትርፍ ጊዜ ተጨማሪ ሥራ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው።
በ60 እናቶች ላይ ተግባራዊ የሚሆን የሙከራ ፕሮጀክት በማዘጋጀት የሶስት ወር ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። በዚህም ውጤታማ ሥልጠና በመስጠት እናቶች ተጨማሪ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ሕይወታቸውን የሚያሻሽሉበትን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል። በቀጣይም ተጨማሪ እናቶችን በማካተት ይህ ፕሮጀክት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የድርጅቱ ዋና ዓላማም ዜጎች በሀገራቸው ሊጠቀሙ የሚገባቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑና እንደዜጋ በማሰብ ደግመው ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ነው።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልሃዲ ረሺድ እንደሚገልፁት እናትና ባንክና እንደዜጋ ማህበራዊ እንደራሴ በጋራ የጀመሩት ፕሮጀክት በክፍለከተማው የሚደገፍና የሚበረታታ ነው። በተለይ ደግሞ ፕሮጀክቱ ትኩረት ያደረገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እናቶች እንደመሆኑና እናቶች ደግሞ በቤተሰብ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደመሆኑ ይህ ተግባር በክፍለ ከተማው በደንብ ይደገፋል።
በአዲስ አበባ ከተማም ቢሆን እናቶች እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ መቀመጫ እንደመሆኗ ፅዳቷንና ውበቷን በየቀኑ በመጠበቅ ረገድ እናቶች ከፍተኛውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር ለእናቶቹ የተደረገው ድጋፍና ምስጋና የሚያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም። ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ ይዞ የተነሳው ዓላማም ትልቅና ለተሻለች ሀገር ግንባታ እንደዜጋ መኖርን እሴት ያደረገ ማህበረሰብን መፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅምና ተስፋ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ያሉትን አቅሞች በአግባቡና በትብብር መጠቀም ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ደግሞ ሴቶችን ማሳተፍ የግድ ይላል። ክፍከተማውም የፕሮጀክቱ ቤተሰብ ሆኖ ይቀጥላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2016