
ኢትዮጵያ ለዓለም ቅርስነት ካበረከተቻቸው ዘርፈ ብዙ ሀብቶቿ መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ ነው። ይሄ በዓል መሠረቱን የክርስትና እምነት አውድ ሥር ያድርግ እንጂ፤ በእሴትና ሀብትነቱ ግን የመላው ኢትዮጵያውያን፣ አልፎም የዓለም ሕዝቦች ነው። በመሆኑም የመስቀል በዓል እንደ ኢትዮጵያ ከፍ ብለን ከምንገለጽባቸው የበዙ እሴቶቻችን መካከል አንዱ እንደመሆኑ፤ በዚሁ እሴቱ ልክ ከፍ ብለን ልናከብረው የተገባ ነው።
ምክንያቱም የመስቀል በዓል፣ ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር፤ እኛ ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስርበት እንዲሁም የዓለምን ሕዝብ ቀልብና ልብ የሚይዝበት የጋራ እሴት አለውና። ይሄ እሴቱ ደግሞ፣ ስለ ሕዝብ ራስን ማስገዛትን፤ ስለ ክቡሩ የሰው ልጅ ራስን አሳልፎ መስጠትን፤ ስለ ትውልድ ተስፋና መዳን ዋጋ መክፈልን፤ ስለ ፍቅር ሲባል መተናነስን፤ ስለ ኅብረት ሲባል በፍቅር መተሳሰር፤ ስለ ሕልምና ስኬት ሲባል ለፈተና እና ድካም እጅ አለመስጠትን፤… በውስጡ አምቆ የያዘ፤ ይሄውም አሰናስሎ የሚገለጽበት ነው።
የመስቀልን በዓል ስናከብር ልናስባቸው ከሚገቡን ጉዳዮች መካከል አንዱና ዐቢዩ ቁም ነገር፤ አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በተራሮች መካከል በመቅበርና እላዩ ላይ ቆሻሻ በመከመር እንዳይገኝና እንዲረሳ ማድረጋቸው ነበር። ነገር ግን ሁሉም በጊዜው ይሆን ዘንድ ግድ ነበርና ይሄን እንድታደርግ የተፈቀደላት ንግሥት ዕሌኒ በጥበብና ተስፋ ባለመቁረጥ የተቀበረው መስቀል እንዲወጣ አድርጋለች።
ዛሬም ይሄንን በዓል ስናከብር እንደ ሀገር በሰላማችን፣ በልማታችን፣ በአብሮነትና ኅብረታችን ላይ እንደ ቋጥኝ ተጭነው የሚያንገታግቱን አያሌ ችግሮች አሉ። እነዚህ ችግሮች ግን የእኛን ዝለት፣ ትዕግስትና ማስተዋል አልባነት፣ ጊዜና ሁኔታን አለማገናዘብ፣ ተገን አድርገው የተጫኑን ናቸው። በመሆኑም ከእነዚህ ያልተገቡ የዝለት፣ የትዕግስትና ማስተዋል አልባነት፣ የጊዜና ሁኔታን አለማገናዘብ ችግሮቻችን እልፍ ብለን፤ ጽናት፣ ብልሃት፣ ትዕግስት፣ ማስተዋልና ማገናዘብን ሀብታችን በማድረግ ልንሻገራቸው የተገባ ነው።
ይሄን የምናደርገው ግን የመስቀሉን በዓል የማክበራችንን እሴት ስንረዳ ነው። የመስቀሉ በዓል ያጎናጸፈንን ማህበራዊ እና ሰብዓዊ ልዕልና በልኩ ስንገነዘብ ነው። ይሄንን ስንገነዘብ እንጸናለን። ይሄንን ስንገነዘብ ለሰብዓዊነት ዝቅ እንላለን፤ ይሄንን ስንገነዘብ ስለ ሌሎች መኖር ራሳችንን እናስገዛለን፤ ይሄንን ስንገነዘብ አጠቃላይ ስለ ሰው ልጅ እና ሀገር ልዕልና እንተጋለን። እንደ አጠቃላይም ስለ ሕዝቦች አብሮነት፣ ስለ ሀገር ብልጽግናና ልዕልና ከችግሮቻችን ልቀን እንገኛለን።
እንዳይገኝ፣ እንዳይገለጥ፣ ለሕዝቦች የመዳን ምክንያት እንዳይሆን፣ በጥቅሉ ከፍ ያለው የሰው ልጅ አበርክቶው እንዳይገለጥ በጉድጓድ የተቀበረው እና በቆሻሻ ክምር ውስጥ እንዲሸሸግ የሆነው መስቀሉ፤ ከብዙ ድካም በኋላ እንዲገኝና እንዲወጣ የሆነውም ለፈተና አለመንበርከክን፣ ለችግር እጅ ያለመስጠትን፣ ለማደናገሪያ ሃሳቦች ቦታ መንፈግን ገንዘቧ ባደረገችው ንግሥት ዕሌኒ እንዲወጣ ከመደረጉም የምንማረውም ይሄንኑ ነው።
ምክንያቱም፣ ታሪኩ እንደሚያስረዳን፤ በ326 ዓ.ም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም። ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም። ነገር ግን የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበር አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን አካባቢ ጠየቀችው።
ሽማግሌውም፣ እሷም በከንቱ ከምትደክም፣ ሰውንም ከምታደክም ይልቅ እንጨት ሰብስባና ዕጣን አድርጋበት በእሳት እንድትለኩሰው ነገሯት። የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ሲመለስ አቅጣጫውን አይታ እንድታስቆፍርም መከሯት። እሷም የአረጋዊውን ምክር ሰምታ ያሏትን አደረገች፤ እናም ጢሱ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ የመጠቆም ያህል አመለከተ።
ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ መስቀሉ ያለበት ስለመሆኑ አምና አስቆፈረች፤ መስከረም 17 አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል በማስቆፈር መስቀሉ እንዲወጣ አደረገች።
ዛሬ እኛ የምናከብረው የመስቀል በዓልም አስተምህሮው፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የንግስቲቱን ሕልምና መሻት፤ የንግሥቲቱን ጽናት፤ የንግሥቲቱን ማስተዋል፤ የንግሥቲቱን ብልሃት፤ የንግሥቲቱን ምክር ሰሚነት፤ የንግስቲቱን ትዕዛዝ ፈጻሚነት ገንዘባችን እንድናደርግ ነው። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ዛሬ የሚያስፈልገንም ይሄው ነው።
ከዛሬ የተሻገረ የሩቅ ሕልም ስለመያዝ፤ ከዕለት ያለፈ ለብዙዎች መሻገሪያ የሚሆን አቅምን ሃብት ስለማድረግ፤ ስለ ፍቅርና አንድነት፣ ስለ ይቅርታና ዕርቅ፣ ስለ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ቆሞ ስለ መመካከር፤ በጥቅሉ ከበዙ ፈተናዎቻችን መረብ ልቀን ለመገኘታችን አቅም ስለሚሆኑን ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ስለመምከር እያሰብን ሊሆን ይገባል።
የመስቀሉ በዓል አስተምህሮም፤ የመስቀሉ አጠቃላይ እሴትም ይሄንኑ እንድናደርግ የሚያስገድደን ነው። ስለሆነም የመስቀሉን በዓል ስናከብር እነዚህንና ሌሎች አያሌ የመስቀሉን እሴቶች በመረዳትና በመላበስ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም