የዱር እንስሳት ጥበቃን በአዳዲስ መፍትሔዎች

በቀደምት ሥልጣኔ ጀማሪነት፣ በብዝኃ ባሕልና ሃይማኖት፣ ዘመናትን በተሻገሩ የታሪክና የሥልጣኔ ዐሻራ በሆኑ ቅርሶቿ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ የመሆን እምቅ አቅም አላት። በውብ ተፈጥሮና መልክዓ ምድር፣ በብርቅዬ እንስሳት መኖሪያነትና ለሰው ልጆች የመኖር ሕልውና ዋስትና በሆነ የብዝኃ ሕይወት ስብጥርም ሀገሪቱ በዓለማችን ቀዳሚ ከሆኑ ክፍሎች መካከል ትጠቀሳለች።

ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ፣ የዱር እንስሳት ለሰው ልጆች ያላቸውን ጠቀሜታም ከዘመናት በፊት በመገንዘብ የጥበቃና እንክብካቤ ሥርዓት ዘርግታለች። በ15ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከንጉሥ ዘርዓያዕቆብ ጀምሮ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የማድረግ ልማድና ባሕል እንደነበራትም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለዚህም ንጉሡ ከዛሬ 500 ዓመት ቀደም ብሎ በወጨጫ ተራራ እንዲሁም፣ ጓሳ ሣርን ለመጠበቅ በመንዝ ጓሳ ይደረጉ የነበሩ የጥበቃ ሥራዎችን በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል። ይህን አሠራር በዘመናዊው የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋማዊ ቅርፅ በማስያዝ ተግባራዊ ሥራ ከጀመረች ደግሞ ዘንድሮ 60 ዓመታት ተቆጠሩ።

የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን አስመልክቶ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ተግባራት እና የብዝኃ ሕይወት መጠቀም ፋይዳዎችን ይቃኛል። ሀብቱን መጠበቅ፣ መንከባከብና ለቱሪዝምና ለሰው ልጅ ሕይወት ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር እየተሠሩ ያሉ ተግባራትንም ይመለከታል።

የዱር እንስሳትና መኖሪያ ፓርኮች የመከለል፣ የመጠበቅና የማስተዳደር ተግዳሮቶች ምን እንደሚመስሉ የዘርፉን አመራሮች አነጋግሯል። ለተግባራዊ ሥራው የፋይናንስ ምንጭ አስፈላጊ ስለመሆኑና ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ እየገጠሟት ያሉትን ተግዳሮቶች በተመለከተ የዘርፉ አመራሮች የሚያነሱት ሃሳብ ይዞ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ በተቋም ደረጃ ከተቋቋመ ዘንድሮ 60ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ተቋሙ የተቋቋመበትን ቀንና ‹የዓለም የዱር እንስሳት ቀን›› የካቲት 24 ቀን በአዲስ አበባ ጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል አክብሯል። ቀኑ በጉብኝትና በዘርፉ ከጥበቃና ከፋይናንስ አማራጮች ጋር የተያያዘ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በሥነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ 12 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት፣ የተለያዩ የመሬት አቀማመጥና አየር ንብረት አላት። በደጋ፣ ወይናደጋ፣ ከፊልና ሙሉ በረሃ ያቀፈ የአየር ንብረት እንዲሁም ከፍተኛና ዝቅተኛ ቦታዎች የያዘች በመሆኑ ልዩ ልዩ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች የያዘች ለምድራችን ሥነ ምሕዳር መጠበቅ አስተዋፅዖ ያላት ሀገር እንድትሆን አድርጓታል።

የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንም የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ሀብትና ሥነ ምሕዳር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመንከባከብ ኃላፊነቱን ላለፉት 60 ዓመታት ሲወጣ ቆይቷል።

ከኅብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከዚህ ብዝኃ ሕይወትና ሥነ ምሕዳር ትውልዱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግም ይህን ጠብቆ የማስተላለፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። ይህንን ተግባርና ኃላፊነት በበቂ ሁኔታ በዘላቂነት ለመወጣት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋል። የዘንድሮው የዓለም የዱር እንስሳት ቀን መሪ ሃሳብ ከዚህ ከፋይናንስ ድጋፍ ጋር የተገናኘ መሆኑ ጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሻ ያስገነዝባል።

የዱር እንስሳት ጥበቃና መኖሪያ ቦታ እንክብካቤ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ባሕል እና ለአካባቢው ማኅበረሰቦች መተዳደሪያ የሚሆን ከፍተኛ ሀብት በማስገኘትም አስተዋፅዖ ያደርጋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ዕድል በተገቢው መልኩ ለመጠቀም ቢያንስ በየዓመቱ 300 ሚሊዮን ብር አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ይህንን የፋይናንስ ድጋፍ እንደ ሀገር ለማሰባሰብ የዓለም የዱር እንስሳት ቀን እና የኢትዮጵያ የ60 ዓመት የዘርፉ ጥበቃ ጉዞ “የዱር እንስሳት ጥበቃ ፈንድ ማረጋገጥ፦ በሰዎች እና በምድራችን ላይ ኢንቨስት ማድረግ ነው” በሚል ዓለም አቀፍ መሪ ቃል በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በእግር ጉዞ ጉብኝትና በፓናል ውይይት ማክበር ማስፈለጉን ይገልፃሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት፤ የመንግሥት ተቋማትን፣ የጥበቃ ባለሙያዎችን፣ የግሉን ዘርፍ እና የአካባቢ ማኅበረሰቦችን በማቀናጀት የዱር እንስሳት ጥበቃን ማጠናከር ያስፈልጋል። በዱር እንስሳት ጥበቃ ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና ዘላቂ የዱር እንስሳት ጥበቃን ለማጠናከር የፋይናንስ ድጋፍ ቁልፍ ጉዳይ ነው። በመሆኑም የብዝኃ ሕይወት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በጤናማ ሥነ-ምሕዳር እና በማኅበረሰብ ደኅንነት መካከል ያለውን ወሳኝ ትስስር ለማጠናከር በትኩረት ልትሠራ ይገባል፤ ይህንን የሚደግፍ በቂ የፋይናንስ አማራጭ ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በመንግሥትና የግል ሽርክና፣ ዓለም አቀፍ ትብብር እና ተፈጥሮን መሠረት ባደረጉ የመፍትሔ ሃሳቦች ለጥበቃ የሚያገለግል የፋይናንስ አማራጭን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የሚያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ጥበቃን በተመለከተ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት በተለይ በዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እና ውጤት ለማምጣት አንድነት እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዋል። አንድነቱ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ ለሰው ልጆች ደህንነት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ለዱር እንስሳት ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጡ አዳዲስ መፍትሔዎችን ተግባራዊ በማድረግ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን አቶ ኩመራ አስታውቀዋል። ማኅበረሰቡ የዱር እንስሳት መጠለያ አካባቢ የመኖር ልምድ እንዳለው የሚያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንንም ጥበቃውን በማያውክና ዜጎችን በፋይናንስ፣ በትምህርት እንዲሁም በሌሎች የሥራ አማራጮች እንዲደግፍ ለማድረግ በተጓዳኝም የብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅ እየሠራች ነው ብለዋል። ለስኬታማነቱም ለዱር እንስሳት ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጡ አዳዲስ መፍትሔዎች ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ልዩ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል የጥበቃ ሽፋንን ይመለከታል። በዚህም ኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽፋንን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈረንጆች የዘመን ቀመር በ2030 የምድሪቱን የዱር እንስሳት የጥበቃ ቦታ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ።

አሁን ያለው ለዱር እንስሳት ጥበቃ የሚሆን የዓለም የጥበቃ ቦታ ሽፋን በአማካኝ 17 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ደግሞ 14 በመቶ እንደሆነ ይገልፃሉ። በቀጣይም የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽፋን ከፍ በማድረግ ለዓለም የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ ሽፋን ማደግ የበኩሏን እንደምታበረክትም ተናግረዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው እንደገና አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዱር እንስሳት ጥበቃ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚ በተለይ ለቱሪዝም ሥነ ምሕዳር እድገት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአረጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተፈጥሮን የማሰቀጠል ሥራን አቅዳ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ይናገራሉ።

‹‹ኢትዮጵያ ለዱር እንስሳት ጥበቃ ቅድሚያ በሚሰጡ አዳዲስ መፍትሔዎች ላይ በማተኮር እየሠራች ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንድታዝመዘግብ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ይገልጻሉ። ዘላቂነቱን ለማረጋገጥም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራውን ለማስቀጠል እንደምትሠራ አመልክተዋል። የዱር እንስሳት ጥበቃ ማጠናከር ለሀገር እድገት ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል እንደሚረዳም አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ በኢኮ ቱሪዝም፣ በዘላቂ ግብርናና ደን ልማት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሕይወታቸው ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ ነው። የዱር እንስሳት ጥበቃ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ ደግሞ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ዕድል ፈጥሯል፤ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልማት የሚያደርገውን ተሳትፎም ይበልጥ ያጠናክረዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ የዱር እንስሳት ባለቤት ብትሆንም፣ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ባለመቻሉ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች። ከባለፉት የለውጥ ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅዖ ማድረግ እንዲችል በስፋት እየሠራ ነው። ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም መንግሥት ብቻውን ይሠራ የነበረበትን ዘርፍ የግል ባለሃበቱም እንዲሳተፍበት አድርጓል።

መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የዱር እንስሳት ሃብትን በጋራ በመጠበቅ ዘርፉ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቅሰው፣ የፌዴራል መንግሥት ከሚሠራው የዱር እንስሳት ጥበቃ በተጨማሪ ክልሎች በራሳቸው አቅም ለዱር እንስሳት የሚሆኑ ፓርኮችን የማዘጋጀት ተግባር እንዲያከናውኑ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። በቀጣይ የዱር እንስሳት ሀብትን ወደ ተሻለ የቱሪዝም መዳረሻ አማራጭነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በዓለም አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ዕፅዋትና እንስሳት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ለዚህም የዓለም የብዝኃ ሕይወትና የዱር እንስሳት ጥበቃን ማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ውስጥም የሰው ሠራሽ አደጋን (ወደ ፓርኮች በሚስፋፋ እርሻ፣ ደን ምንጣሮና ሕገወጥ አደን) ጨምሮ የተፈጥሮና ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች በዱር እንስሳትና ብዝኃ ሕይወት ሀብት ላይ ስጋት ደቅነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሀገሪቱ ያሏት የተፈጥሮ ሀብት፣ ብርቅዬ እንስሳት፣ ፓርኮችና ሌሎች የቱሪዝም መስሕቦች እጅግ አስደናቂና በርካታ ቢሆኑም፣ መንግሥትም ሆነ ዜጎች ከዘርፉ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አይደሉም።

የዘንድሮው የዓለም የዱር እንስሳት ቀን እና የኢትዮጵያን የ60 ዓመታት የዱር እንስሳት ጥበቃ ጉዞ የተመለከተው ይህ በዓል፣ እነዚህን ቁልፍ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት መፍትሔ ለማበጀት ያለመ ምክክር የተካሄደበት ነው። በበዓሉ ላይ የዱር እንስሳት ጥበቃን ለማጠናከር የሚያግዝ የፋይናንስ አማራጭና ውስንነት እና አዳዲስ የዱር እንስሳት የጥበቃ ስልቶችን የሚመለከቱ ገለጻዎች ተደርገዋል፤ በበዓሉ ላይ ምሑራን፣ አምባሳደሮች፣ አጋር አካላት፣ የባለሥልጣኑ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎች እና የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የጥበቃ ሥራ የረጅም ዓመታት ጉዞ፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራ እና ከመስኩ የሚገኝ ፋይናንስና ለመስኩ የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍን አስመልክቶ እንዲሁም ለጥበቃ ሥራ ፋይዳ ያላቸው አዳዲስ አሠራሮችን ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችም በተለያዩ የመስኩ ምሑራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You