መስጊዶች ከወትሮው ለየት ብለዋል። ግድግዳዎች፣ ምንጣፍና የግቢ ሥፍራዎች በአዲስ ቀለም አሸብርቀዋል። ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከተራ ድሃ እስከ ቢሊየነር፣ ከወዛደር እስከ ምሁር የእምነቱ ተከታይ ሆኖ መስጊድ ያልመጣ ያለ አይመስልም። ሁሉም በግምባሩ ሱጁድ ወርዶ (በግንባሩ ሰግዶ) የማይጸልይ፣ ወደ ፈጣሪው የማያለቅስ ለአይኔ አልታየኝም- በይቅርታ እና በአፉታ የጀመረው የዘንድሮ የረመዳን ጾም የመጀመሪያዎቹ አስር የእዝነትና የርህራሄ ቀናት።
መስጠት፣ መዋደድ፣መካፈል፣ከመጥፎ ድርጊት መቆጠብ፣ መተዛዘን ግዴታ ነው በረመዳን። ‹‹ለአላህ ብለህ ሥትሰጥ አላህ ይሰጥሃል። በሰጠህ ቁጥር በብዙ እጥፍ ማትረፍ እንጂ ቅንጣት መጉደል የለም›› እንደ አስተምህሮቱ።
የዘንድሮ የረመዳን ጾምና ጸሎት ድባቡ ምን እንደሚመስል በአካል ከተመለከትነው እና አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ካካፈሉት መካከል ጥቂቱን ልናስቃኛችሁ ወደድን።
አቶ መሐመድ ይመር ይባላሉ ያገኘናቸው የዓርብ(ጁምዓ) ሰላትን (ስግደትን) አዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ ከሚገኘው ጀርመን መስጊድ ሰግደው ሲወጡ ነው። በመስጊዱ መግቢያ ግራና ቀኝ ጠርዝ ተኮልኩለው የሚለምኑትን የኔ ቢጤዎች ምዕመኑ የአቅሙን ሰደቃ(ምጽዋት) እየሰጠ ያልፋል። እሳቸው አዘጋጅተው ያመጡትን ዝርዝር የብር ሳንቲም ከመስጠት ባለፈ የቤታቸውን አድራሻ እየገለጹ ‹‹ለኢፍጣር›› እንዲገኙላቸው ለየኔ ቢጤዎች ጥሪ ያስተላልፋሉ።እኛም የጥሪው አካል ሆነናል።
ሰዓቱን ጠብቀን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ደምበል ጀርባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተገኝተናል። ሙስሊም፣ክርስቲያን፣ሀብታም ደሃ፣የሚታወቅ፣የማይታወቅ እንዲሁም ጎረቤት ጭምር የታደመበት ‹‹የአፍጡር›› ግብዣ። በሚበላውም በሚበላውም(ጠብቆ) በኩል የነበረው ሥብጥሩ እጅጉን ያሥደስታል።
ረመዳን የተገኘውን እና ቤት ያፈራውን አብሮ ተካፍሎ የሚበላበት፣የይቅርታ፣የእዝነት፣ የአንድነት እና የመዋደድ ወር ነው የሚሉት አቶ መሐመድ፤አብሮ መብላት፣አብሮ ተዋድዶ መኖር፣መተዛዘን አቅሙ ያለው ከበፊትም
የሚያደርገው ባህል ቢሆንም በረመዳን የጾም ወቅት ‹‹ማስፈጠር››ግን ከመቼውም የላቀ ፋይዳ አለው። በፈጣሪም ዘንድ የሚያስገኘው ዋጋ ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ረመዳንን ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጉጉትና በናፍቆት የሚጠብቀው ወር ነው። ‹‹በኢፍጣር›› ሰዓት የሚስተዋለው ግርግር፣ በመስጊዶች የሰላት(የስግደት) ሰዓት አካባቢ የምታስተውለው የአማኝ ብዛት፣ ተራዊህ(ምሽት ከእንቅልፍ በፊት ረዘም ላለ ጊዜ የሚደረግ ስግደት) እና ሌሎች የማይረሱ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል። ዘንድሮ የሚስተዋለው የጀምዓው ሙሀባ(የህዝብ ፍቅር) እና አንድነት ከመቼውም የተለየ መሆኑን አክለዋል።
ባለቤታቸው ወይዘሮ ኑሪት አህመድ በበኩላቸው ‹‹በኢፍጣር››የተገኙላቸውን እንግዶች አመስግነው ረመዳን የእዝነት ወር ነው። በመሆኑም ልንተዛዘን ይገባል። እኛ እርስ በርሳችን ስንዋደድ፣ስንከባበር፣በጋራ ተፋቅረን ሥንኖር የፈጣሪ(የአላህ) እዝነትና እርህራሄ አብዝቶ ይደርሰናል። በማንኛውም ጊዜ ሁላችንም ከልባችን ልንዋደድ፣አብረን በሰላም ልንኖር ይገባል። የሰው ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ ለፈጠረው አምላክ ሊገዛ የመጣ ባሪያ ነው። ሥለዚህ ቀኑ ደርሶ ሲሞትም በፈጣሪው እጅ መሆን አለበት። ሰው በሰው ሊጠፋ ባልተገባ ነበር። አመላችን እንጂ አገራችን ጠባብ ሆና አይደለም የምንጋጨው። ሥለዚህ የረመዳን ወር የእዝነትና የመተጋገዝ፣የማብላትና የማጠጣት እንዲሁም የመተሳሰብ ወቅት ስለሆነ ደግነት ከእኛ (ከሰው ልጆች) ሊርቅ አይገባም ብለዋል።
ሌላው ‹‹በኢፍጣር›› ፕሮግራሙ ያገኘናቸው ጎረቤት አቶ ወንድሜነህ አለኸኝ እንደተናገሩት፤እኔ ሁልጊዜም በረመዳን ጾም ቴምርና ሾርባ ትዝ ይለኛል።በእምነቴ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ። በተለይም ቴምር በረመዳን ብቻ የሚበላ ያህል ይናፍቀኛል። የትኛውንም በዓል ከልጅነታችን ጀምሮ አብረን እያከበርን ያደግን ነን። የረመዳንን ወር መምጣት ቀን እየቆጠረ የሚያሰላው የእስልምና እምነት ተከታይ ማህበረሰብ ብቻ አይምሰላችሁ። የክርስትና እምነት ተከታዮችም ጭምር እንጂ።
ለዚህ ደግሞ በአንድ አርሰው፣ በአንድ ቆርሰው፣ ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ተዋደው ለዘመናት በተፈጥሮ ሕግ ሥር ሕዝቦች ተዋህደው መኖራቸው በምክንያትነት ይነሳል፤ ሀዘንንም ሆነ ደስታን ተለያይቶ ማሳለፍ አይችሉበትም።ሰርግና ድግስ ካለባቸው እኮ ተጠያይቀው ምቹ ወቅት ላይ እንዲሆን ያደርጉታል ሲሉ ትውስታቸውን አንስተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጺ ወረዳ ጋሌሳ ቀበሌ ነዋሪው ሸህ የሱፍ ቃሲም እንዳብራሩት ደግሞ፤ የረመዳን ጾም ከአምስቱ የኢስላም መሰረቶች አንዱ ነው። ማንኛውም የእምነቱ ተከታይ የመጾም ግዴታ አለበት። በመሆኑ እጅግ የተለየ የረህመት(ጸጋ የበዛበት) ወር ነው። ከመጥፎ ሥራዎች በመራቅ በጾም፣ በጸሎት፣ በሥግደት፣ የተቸገሩትን በማብላትና በማጠጣት ይከወናል። እያንዳንዷ የምንሰራት በጎ ሥራ በፈጣሪ ዘንድ እጅግ የላቀ ፋይዳ አላት። የበዛ ዋጋ (ምንዳ) ታስገኛለች።
የዘንድሮ የረመዳን ጾምን ከበፊቱ ምን ለየት ያደርገዋል? ላልከኝ፤ በጣም በብዙ ነገሮች የተለየ ነው። ምንም እንኳን እዚህም እዚያም ግጭቶች ቢኖሩም በአገሪቱ እንደ ዘንድሮ ዜጎች በመሪዎቻቸው ተደስቶ አይቼ አላውቅም። የእዚህ ረህመት(ትሩፋት) ለእኛ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞችም ደርሶናል።
ከዚህ በፊት በመካከላችን በነበሩት የርስ በርስ አለመግባባቶች ምክንያት ነፍስያችን (ሕይወታችን) ትፈተን ነበር። ጸሎታችንም የሙስሊሙን ጉዳይ እንደዜጋ የሚያይ፣ በውስጣችን መከፋፈልን የማይፈጥር፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር በተንኮል የማያናቁር መንግስታዊ አስተዳደር እንዲኖር እያለቀስን አላህን(ፈጣሪን) ለምነነዋል።
አሁን ደግሞ ‹‹የሙስሊሙ አንድ መሆን ከራሱ አልፎ ለአገርም ይጠቅማል›› ብሎ መንግሥት ክብር ሰጥቶ አፉን (ይቅርታ) አባብሎ በንጹህ ልብ፣በአንድነትና በፍቅር ረመዳንን መጾም አስችሎናል።ይህ ለእኛ ከአላህ የተሰጠ ራህመት(ጸጋ) ነው። የእርስ በርሳችን አንድ መሆን፣በፍቅርና በአንድነት አብሮ መብላትና ተደስቶ መኖር አገርን ከመጥፎ ነገር ይጠብቃል። በአገሪቱ የሚገኘው ሁሉም ሙስሊም አሁን አንድ ሆኗል። መዋደድ ተፈጥሯል።
በመካከላችን በተፈጠረው መዋደድና አንድነት እያመሰገንን ሙስሊሙ የመንግሥትን ጥሪ ሰምቶ ለውጡን በመደገፍ ለሁላችን የምትመች፣ ሰላምና መዋደድ እንዲሁም እድገት የሞላባት ኢትዮጵያ ልጆቻችን እንዲኖራቸው የድርሻውን እንዲያበረክት እየመከርን ነው። አላህ እንደሚሳካልን እምነት አለኝ›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
ሙሐመድ ሁሴን