አዲስ አበባ ፡- የአደባባይ ስብሰባዎች ወደአዳራሽ እንዲመጡ የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል። የአደባባይ ላይ ግርግር እና ሰልፍ ወደ አዳራሽ ንግግር እና መደማመጥ መዞር አለበት የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ሃሳብ ተግባራዊ የማድረግ ጭላንጭሎች ይታያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ወዲህ የአዳራሽ ውይይቶችን በማስተባበር ረገድ አምስተኛ የሆነውም መድረክ አዘጋጅቷል።
መድረኩም በአፍሪካ የመንግስታቱ ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን/ኢሲኤ/ ነበር ትናንትና የተሰናዳው። ከፖለቲካው፣ ከማህበራዊ፣ ከሲቪክ ማህበራቱም በአጠቃላይ ከተለያዩ ሙያዎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ ተገናኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እስከ ሻይ ሰዓት ድረስ የቀረቡ የውይይት ሃሳቦችን አጢነው ወደ ሌላ ጉዳይ አምርተዋል። የመወያያ ርዕሶቹ ደግሞ በፌዴራሊዝም፣ ሰላም እና ለውጥ እንዲሁም ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ሰሚር የሱፍ የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ተቃርኖዎች፣መንስኤዎችና ውጤቶች የሚል ጽሁፍ አቅርበዋል። እንደ እርሳቸው፣ ብሔር
የሚባለው አስተሳሰብ በኢህአዴግ ዘመን ሳይሆን ቀድሞ የመጣ ጉዳይ ነው። መንግስት ግን ጥያቄውን ያስኬደበት እና ለማስተዳደር የሞከረበት መንገድ ተቃርኖ ፈጥሯል። መንግሥት ብሔርን ከውጭ ሆኖ ወደ ውስጥ የሚገለጽ እና በድንበር ተወስኖ የሚቀር እንዲሁም ተለዋዋጭነት የሌለው አድርጎ መቀበሉ ትክክል አልነበረም።
ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ የብሔር እና ቡድን ጥያቄን ለማስተናገድ ከማዕከላዊ መንግሥት ስርዓት ጋር መደባለቁ ውስብስብ ችግር አምጥቷል። በተቋማት ደረጃ ብሔር ተኮር አወቃቀር መዋቀሩ እና እያንዳንዱ የእራሱ ባንዲራ እንዲሁም ከባቢያዊ ነገር መፍጠሩ ተቃርኖ ፈጥሯል። በተለይ ፌዴሬሽን ምክርቤቱ የተቃርኖ ማዕከል ሆኗል። ምክንያቱም በአንድ ወቅት የተለያዩ የነበሩትን የደቡብ ብሔርብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልን ወደአንድ አምጥቷል። ይህ ደግሞ ከብሔር ጋር ተቃርኖ ሲፈጥር በሌላ አካባቢ ደግሞ ብሔርን ያማከለ ስራ በመኖሩ ፌዴሬሽን ምክርቤቱን ወደተቃርኖ መርቶታል።
ተቃርኖው ደግሞ ተገዳዳሪ ብሔርተኞችን በመፍጠሩ አንድም ኢህአዴግ ፓርቲን አፍረክርኮ ለውጥ እንዲመጣ እንዳደረገ ዶክተር ሰሚር ይናገራሉ። ይህ ችግር አሁን የማዕከላዊ መንግሥት እንዲጎዳ እና የተዋረድ አስተዳደር እንዳይኖር እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም ፌዴሬሽን ምክርቤቱ የጋራ ግንዛቤ ላይ መስራት ይኖርበታል። ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ መፍትሄዎችን በጥናት ማምጣት ይገባል። በተለይ የቡድን እና የግል መብት አንዳንዴም የሚለያዩበት፣ የሚገናኙበት እና የሚጋጩበትን ሁኔታዎች ምንድን ናቸው የሚለውን በማጥናት ፌዴራሊዝምን ዳግም መፈተሽ ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ፓርቲ ምክትል መሪ አቶ አንዱአለም አራጌ ደግሞ የሰላም ምንነት፣አስፈላጊነትና የባለድራሻዎች ሚና በሚል መወያያ ሃሳብ አቅርበዋል። ለውጥ በመምጣቱ እና የነጻነት ብልጭታ በመታየቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት በአንጻሩ ተችተዋል። የዜጎች ልዕልና እና ነጻነት እንዲጎለብት ሁሉንም ያካተተ ስራ በመንግስት በኩል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። እንደእርሳቸው፤ ህግ ከሚፈቅደው በላይ የሚንቀሳቀሱ አምባገነኖችም ሆነ ህግ ከሚፈቅድላቸው በታች የሚሰራ መንግሥት ሁለቱም ጥፋተኝነት አለባቸው። መንግሥት ህግ ከሚፈቅደው በታች ትዕግስተኛ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።
<<መንግሥት በሆደ ሰፊነት እና በህግ የበላይነት መካከል ያለውን ደረቅ መሬት የማግኘት ችግር አለበት>> የሚሉት አቶ አንዱአለም፤ ችግር ሲከሰት መንግሥት የሚያሳየው ትዕግስት አቅም እንደሌለው ተደርጎ እንዲታሰብ እንዳደረገው ይናገራሉ። በመሆኑም መንግሥት ተከትሎ መቆጣጠር የሚያስችል አቅም እንዳለው ማሳየት ይኖርበታል። በሌላ በኩል ህዝቡ ለውጥ በጥቂቶች ብቻ እንደሚመጣ አድርጎ የመቀመጥ ችግሩን እንዲተው መደረግ ይኖርበታል። ጥቂት አጥፊዎች ብዙ መንቀሳቀስ ከቻሉ ሰፊው በጎነገር ፈላጊ ደግሞ ብዙ መስራት እንደሚችል ማሳየት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በሌሎች አገራት ቢሆን 10 ዓመት ሊፈጅ የሚችሉ ለውጦችን በአጭር ጊዜ መከናወናቸውን በዝርዝር ህዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ግን በሰላምና ነጻነት ረገድ የተሄደው ርቀት አጭር የሚቀረው ጉዞ ደግሞ ረጅም መሆኑን አውቆ ሁሉም ወደ ሥራ መግባት ይኖርበታል።
የሰላም ግንባታና ዕርቅ ባለሞያው ፕሮፌሰር እዝቅያስ አሰፋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስለሚታየው ግጭት እና መፍትሄው ያነሳ ሃሳብ አቅርበዋል። እንደ እርሳቸው፤ ግጭት በሰዎች ዘንድ አይቀሬ ጉዳይ ነው። ግጭቱ በአግባቡ ካልተያዘ ግን የመገዳደያ እና የመውደቂያ መንገድ ይሆናል። ግጭትን ግን ብልጦች ከተጠቀሙበት እና በአገባቡ ከተያዘ የመፍትሄ ማፈላለጊያ መሳሪያ መሆን ይችላል። በመሆኑም ግጭት ሲከሰት ለመፍትሄ ማፈላለጊያ በማዋል አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሳይሆን ሁሉም የሚጠቀሙበት ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደ ፕሮፌሰር እዝቅያስ ከሆነ፤ በሌላ በኩል ባለመጥፎ ውጤት ግጭት የሚፈጥሩ ዘረኝነት፣ ስርቆት እና ማታለል ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ በቀጥታ ከሐይማኖት እና የአምላክን ትዕዛዝ ካለማክበር ጋር ይገናኛሉ። በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ጥሩ ስነምግባር ያለው እና እልቂት የማይፈጥር እንዳይሆን የሐይማኖት አባቶች በቂ ግንዛቤ በመፈጠር ረገድ ብዙ ጥረት ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪ ግጭት እንዳይስፋፋ ከተፈለገ በጎ ማሰብ ይገባል። በዚህ ጽንሰሃሳብ ውስጥ ደግሞ አንዱ ተጠቃሚ አንዱ የበይ ተመልካች እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ነገርግን አንዱ በይ አንዱ ተመልካች ከሆነ ጊዜ ቢቆጠርም አስከፊ ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
ጌትነት ተስፋማርያም