የሁላችንም በዓል፤ የሁላችንም ድምቀት

ከመስከረም እስከ ነሐሴ በሚዘልቀው አስራ ሁለቱ ወራት በእያንዳንዱ ወራት ውስጥ 30 ቀናትን ቆጥረን ዓመት ሞላው ብለን ሳናበቃ እንደገና በእኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ የተለየች አቆጣጠር ጳጉሜን አምስት ወይንም ስድስት ቀን አክልን ይኸው አንድ ዓመት ደፈነ ብለን አዲስ ዓመትን አከበርን።ቡሄ ካለፈ፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት ብለን ዝናብ ባያቋርጥም መስከረምን ከክረምቱ ነጥለን ይኸው አንድ ብለን ጀመርን::

በክረምት ዝናብ የጨቀየው መሬት ውሃውን ከከርሱ አምቆ ይዞ፤ መሬቱም ጠገግ ብሎ አዲስ የማለዳ ጀንበር ፈንጥቃ በአበባዮሽ ሙዚቃ ደምቀን፤ አደይ አበባ ታቅፈን እንኳን አደረሳችሁ ተባብለን እነሆ በመልካም ምኞት፣ በተስፋና ነገም መልካም እንደሚሆን እንቁጣጣሽ (የአዲስ ዘመን መለወጫ) በዓል አለፍን:: እንቁጣጣሽም በተራዋ ሌሎች በዓላት ተራዋን አስረክባ ከደስታ ማግስት ሌላ የደስታ መንገድ ተረክበናል::

እንቁጣጣሽ

እንኳን መጣሽ፤

በአበቦች መሃል

እንምነሽነሽ::

እያልን የአበባዮሽ ሆይ! ዜማ እና ቅላፄ ከጆሯችን ሳይጠፋ፣ የቡና ጠጡ ስሜት ሳይርቀን፣ የአበባ ድምቀትና ውበት ሳይጠወልግ፣ የዕጣኑ መዓዛ እንዳወደን፣ የቄጠማው ውበት ሳይነጥፍ፣ የበዓሉም ድባብ ከቤታችን ሳይርቅ ደግሞ ይኸው የሙስሊም ወንድሞቻችን የመውሊድ በዓልን እና ከተራ በአንድ ላይ ከትመው መስከረም 16 አብረን ልንደምቅ ነው::

የመውሊድ በዓል የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ወ) የልደት በዓል ሲሆን፤ ይህም በዓል የሚከበረው ፍቅር ለማስረፅ፣ ክብራቸውን ከፍ ለማድረግ፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር፣ ለዳዕዋና ለታሊም ጭምር በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ይከበራል:: በዚህ በዓሉም በርካታ ወገኖች የሚዘያየሩበት፣ የተቸገረ የሚታገዝበት፣ ዕዝነት የበዛበትና የፍቅርና አንድነት ተምሳሌት በዓል ነው:: መውሊድ ሙሃባ ነው፤ መውሊድ ፍቅር ነው፤ መውሊድ አንድነት ነው፣ መውሊድ ከዱኒያ ፍቅር የበለጠ ወደ ፈጣሪ የበለጠ የምንቀርብበት ቀንም ነው::

ከመውሊድ ማግስት ደግሞ መስከረም 17 ደግሞ የመስቀል በዓል ልናከብር ሽር! ጉድ! ላይ ነን:: የበዓሉን ብዛትና በረከት የበለጠ ሊያንረው አንድነትና መተሳሰብን የበለጠ ሊያሳምረው በዚህ ወር በዓላት ከበራፋችን ላይ ቆመዋል:: እነሆ! መስቀል ደረሰ።መንፈሳዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የሚዘክርበት በዚህም ሃይማኖቱ ተከታዮች ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው:: ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደመራ በመደመር የመስቀል በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል::

የመስቀል በዓልን አክብረን ስናበቃ ደግሞ፤ ከሳምንት በኋላ ደግሞ ኦ! ያ ማሬ ሆ! ብለን እርጥብ ሣር ይዘን ፈጣሪን ልናመስግን ኢሬቻ በዓልን በጉጉት እየጠበቅን ነው:: ኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ‹‹ዋቃ›› ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ ጥናታዊ ጽሑፎችና የገዳ ሥርዓት መረጃዎች ሲተነትኑት::

የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ እና ወደ ብርሃን በመውጣቱና ለምለም ምድር በመመልከቱ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል። በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ በወርሃ መስከረም በደስታ እና ፈንጠዚያ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኘን ብሎ ለፈጣሪው ኦ! ያ! ማሬ ሆ! እያለ በአባ ገዳዎች እና ሃዳ ስንቄዎች ዝማሬ ታጅቦ ምስጋና ያቀርባል።

ይህ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው:: ኢሬቻ የሰላም የአንድነትና የፍቅር በዓል ነው። በቀጣይ ሳምንት የምናከብረው የኢሬቻ በዓለም የእኛው ባህል መገለጫ ነው:: ይህ በዓል በጋራ ምሥጋና የሚቀርብበት ሲሆን፤ በእሬቻ ውስጥ ያለውን እሴት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ እሴት እንዲሆንም መረባረብና ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መንገድ ማስኬድ ተገቢ የሁላችንም ኃላፊነት ይሆናል::

እንግዲህ ወርሃ መስከረም በበዓል ድባብ የሁሉም እምነት ተቋማትና ሃይማኖቶች በሚባል ደረጃ ግጥምጥሞሽ የተፈጠረበት ወር ሆኗል፤ ደስም ይላል:: ታዲያ እነዚህ በዓላት የጋራችን፣ የሁላችንም መድመቂያችን መሆናቸው ማሳየት ይጠበቅብናል:: አንዱ ለሌላው ክብር ሊኖረው፤ ፍላጎቱንና እምነቱን ሊጠብቅበት የውዴታ ግዴታ መሆኑን ማሳየትም ማወቅም ይጠበቅበታል::

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የሀገሪቷ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወዳጆች እና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ለዚህ አንድነትና ፍቅርም የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። የሁላችንም በዓል፤ የሁላችንም ድምቀት መሆኑን ለዓለም ሕዝብም ማሳየት የመላው ኢትዮጵያውያን ድርሻ ይሆናል::

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን እየገጠማት ካለው ቀውስ ለማላቀቅ ሁነኛ መፍትሔ የመጠቆም ሀገራዊ፣ መንፈሳዊ ሙያዊ እና ሞራላዊ ግዴታም የምናሳይበት ወቅት ሊሆን ይገባል:: ዛሬም፣ ነገም ከነገ ወዲያም የጋራ ሃብታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገን አንድነታችን የምናሳይበት ጊዜም መሆን አለበት::

በዓሎቻችን የሁላችንም በዓል፤ የሁላችንም ድምቀት፤ የሁላችን ፍካት ስለመሆናቸው አስረግጠን መናገር፤ ከመናገርም ባለፈ በተግባር የምናሳይ መሆን አለበት:: በአበቦች ሕብረ ቀለም አምረን ከአዲስ ዓመት ተሻግረን፤ በነብያችን መውሊድ ተደስተን፣ ከመስቀሉ በዓል አሸብርቀን፣ በእሬቻ ምስጋና በእርጥብ ሣር ተከበን ልንደምቅ እነሆ ይህን ወር ጀምረናል:: 2016 የድምቀታችን፣ የአንድነታችን አንዱ በዓል የሌላችን መሆኑን የምናሳይት፤ የአንዳችን ደስታ የሌላችን እንዲሆንም በብርቱ የምንተጋበት አለፍ ሲልም ህመሞቻችን የምናጋራት ሊሆን ይገባል::

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You