ለሀገር እድገት የከፍተኛ ትምህርት እና የግለሰቦች ተሳትፎ ሚና

በዓለም እጅግ በጣም ያደጉና ሃብታም ሀገሮች ለሕዝባቸው በሰፊው የከፍተኛ ትምህርትን ያዳረሱ፤ ለግለሰቦችም እጅግ ፍጹም የሚባል የፈጠራ እድል፣ የሥራ እድልና የባለንብረት መብት ነጻነት በፖሊሲ ያረጋገጡ፤ በተግባርም ያስመስከሩ ሀገሮች ናቸው። ከጥቂት ሀገሮች በስተቀር (ለምሳሌ፣ እንደነሳውዲ አረቢያ እና ሊቢያ ያሉት ሀገራት በስተቀር) ይህንን ሳያድርጉ ሃብታም ሕዝብ ወይም ሀገር የሆኑ በዓለም ዙሪያ የሉም ማለት ይቻላል።

የከፍተኛ ትምህርት የዜጎችን የፈጠራ ችሎታ፣ የንብረት ባለቤትነትን፣ ምርታማነትን፣ በራስ መተማመን፣ ሕግ አክባሪነትን፣ በዜጎች መካከል ያለውን እኩልነት፣ ዘመናዊና ጤነኛ ኑሮ መኖርን፣ መረጃ የመቀበልንና የማስተላለፍንና ችግሮችን የመፍታት አቅምና ችሎታ ያሳድጋል።

የከፍተኛ ትምህርት (እንደ አጠቃላይም ትምህርት) ከዚህ በላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች በርካታ ጥቅሞች ለተማሩትም ሆነ ለህብረተሰቡ ከዚያም በላይ ለሀገር ይጥቅማል። የግለሰቦች የንብረት ባለቤትነት ነጻነት ደግሞ ለሀገር እድገት ቦታና ጊዜ ሳይለይ በማንኛቸውም ክፍለ ኢኮኖሚ እጅግ አድርጎ የሚጠቅምና ለሀገር እድገትም የሚበጅና አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። የሌሎች ያደጉ ሀገሮች ሁሉ ልምድ የሚያሳየንም ይህንኑ ነው።

የከፍተኛ ትምህርት ሥርጭትንና የግለሰቦች ባለንብረትነት በአንድነት እንዲተገበር ያላደረጉ ሀገሮች ለማደግና ሃብታም ለመሆን ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀርና ወደዚሁ ሁለቱን በአንድነት አጣምሮ ወደመተግበር የተመለሱት ሀገሮች ያሳዩት ለውጥ ብዙ ሊያስተምረን፣ ሊነግረንና ሊለን እንደሚገባ መገንዘብ ይኖርብናል።

በሀገር እድገት የከፍተኛ ትምህርትንና የግለሰቦችን የንብረት ባለቤትነት መብት ጠቀሜታና ሚና በዓለማችን በግልጽ በሚያሳዩ ሶስት ሁኔታዎችን በማንሳት ለማየት እንሞክራለን። እነዚህም፡-

1ኛ. በርካታ የተማረ ዜጋ የነበራቸውና የግለሰቦች የንብረት ባለቤትነት መብት የተገደበና አነስተኛ የነበረበትን፣

2ኛ. አነስተኛ የተማሩ ዜጎች፣ ነጻነትና የግለሰቦች የንብረት ባለቤትነት መብት ያነሰና የጎደለ መሆንን፤

3ኛ. በርካታ የተማሩ ዜጎችና የግለሰቦች የንብረት ነጻነት በሰፊው የነበረባቸውን በጥቂቱ በየተራ ለማየት መሞከሩ ብዙ ያስ ተምረናል ብዬ እገምታለሁ።

በዚህ ረገድ ሲታይ፤ በአንደኛው ጎራ ቻይና እና ሩሲያ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ቻይና እና ሩሲያ ከአርባ አመታት በፊትም እንደአሁኑ ብዙ የተማረ ሕዝብ ነበራቸው። ነገር ግን ለሀገር እድገት የግለሰቦች ሚና የተገደበ ስለነበረ ይህንኑ ተገንዝበው የፖሊሲ ለውጥ እስካደረጉበት ጊዜ ድረስ ደሃም ባይባሉ በሃብታምነት ብዙም እንደዛሬ አይታወቁም ነበር።

ለምሳሌ፣ በቻይና ይህን የተገነዘቡትና ፖለቲከኛ፣ ነገር ግን ከፖሊሲ ሃሳብ አቅራቢነት ተገልለው የነበሩት ዴንግ ከማኦ ሰቱንግ ማለፍ በኋላ ሀገሪቷን የመምራት እድል ሲያገኙ በማኦ ሰቱንግ በቻይናዊነቱ ኩራት (National Pride) የሚሰማውንና የተማረ ሕዝብ በኢኮኖሚው የግለሰቦችን ሚናና ተሳትፎ በማሳደግና በማጠናከር የተማረውን ሕዝብ ተጠቅመውና ይዘው ቻይናን በአጭር ጊዜ ሀብታም እንዳደረጓት ይታወቃል፣ ይመሰከራልም።

የተማረ እምቅ ሕዝብ የነበራትን ቻይና የግለሰቦችን በኢኮኖሚ ግንባታ ተሳትፎና የግል ንብረት ባለቤትነት በእጅጉ አሳደገች፡፡ እናም አሁን ላይ ቻይና በምጣኔ ሃብት ሙያተኞችና ገማቾች በዓለም በሃብቷ ሁለተኛ ሆናለች፡፡ በቀጣይም ቻይና በ2028 የአንደኛነቱን ቦታ ከአሜሪካ ትወስዳለች ተብሎ ወደምትገመትበት ደረጃ አድርሰዋታል።

ቻይናውያን ከማኦ ያገኙትን በዜግነት ኩራትና በዴንግ መሪነት ያገኙትን ሀብታምነት አንድ ላይ አጣምረው በመሃሉ (1991-2010) ዘገም ብሎ የነበር ቢሆንም ከ2012 በኋላ በዚየንግ መሪነት ቻይናን ኃያል እንድትባል አድርግዋታል። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ቀድሞውኑ ብዙ የተማረ ሕዝብ ስለነበራቸውና የግለሰቦችን ባለንብረትነትና በሀገር እድገት የሚኖራቸውን ሚና በማሳደጋቸው፣ በማጠናከራቸውና በመለወጣቸው ነው።

በሁለተኛው ጎራ የህንድን እድገት ለማየት እንሞክራለን። ለሀገር እድገት የከፍተኛ ትምህርትን ለዜጎች በሰፊው በማዳረስና የግለሰቦችን የባለንብረትነት ሚና በማጠናከር ሌላዋ የዓለም ሁሉ ምሳሌ የሆነችው ህንድ ናት። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1945 ነጻ የወጣችው ህንድ እንግሊዞች ምንም ተትውላቸው አልሄዱም ነበር። ሆኖም ግን መሃተማ ጋንዲ ከነጻነት በኋላ ለሕዝባቸው በሰፊው እንዲዳረስ ያደረጉት የከፍተኛ ትምህርት እድልን ነበር።

የተገኘውን ነጻነትና የተሰጠውን እድል በመጠቀም ሕዝቡ እየተማረ በዓለም ዙሪያ በመሄድ እራሱንና ሀገሩን እንዲረዳ ጋንዲ በሰፊው ያስተምሩና ይህንኑ አስመልክቶ በርካታ ሁኔታዎች ለዜጎች እንዲመቻቹ ይረዱ እንደነበረ ይታወቃል። ይሄ በመደረጉም ከጋንዲ ፖሊሲ ሀገራቸው መጠቀሟን በመገንዘብ ዛሬ ህንድ በዓለም በከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ ቁጥር (5ሺህ 288 ዩኒቨርሲቲዎች) ያላት ሀገር ነች። በኢንዱስትሪም እጅግ የበለጸገች ሀገር ነች። በእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ 1ነጥብ4 ቢሊዮን የሚሆነውን ሕዝቧን በመመገብ እራስዋን የቻለች ሀገር ነች።

ከዚህም በላይ በዓለም በርካታ መሪዎችን ያፈራች ብቸኛ ሀገርም ነች። ይህም ማለት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ህንዳዊ ናቸው፤ የእንግሊዝም ጠቅላይ ሚኒስትር ህንዳዊ ናቸው፤ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትም ከህንዳዊ ቤተሰብ ናቸው። በዚህ ብቻ ሳያበቃ በዓለም በትልቅነታቸው ከታወቁ አምስት የአሜሪካ ድርጅቶች ውስጥ የሁለቱ የማይክሮሶፍትና የጉግል ዋና ሥራ አስኪያጆች ህንድ ገጠር ተወልደው ህንድ የተማሩ መሃንዲሶች ናቸው። ይህ ሁሉ ውጤት የተገኘው ከ1945 በኋላ ጋንዲ ለሕዝባቸው በሰጡት በስፋት የመማር እድልና የቀጠለው ጥረት ውጤት ነው።

በሶስተኛው ጎራ ደግሞ የአሜሪካንን እድገት ማየት የሚጠቅም ይመስለኛል። የተማረ ዜጋና የግለሰቦች ተሳትፎ በጣምራ በሀገር እድገት ግንባታ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ከሚያስተምሩን ምሳሌዎች መሃከል አሜሪካ ቅድሚያውን ትይዛለች። በዓለም ካሉ ስድስት ከትሪሊኦን ዶላር በላይ ዋጋ ካላቸው ድርጅቶች መሃከል አምስቱ በአሜሪካ በግለሰቦች የተመሰረቱ መሆናቸው የትምህርትንና የግለሰቦች የንብረት ባለቤት የመሆን ነጻነት ሚናን ያሳየናል።

እነዚህም ድርጅቶች 1ኛ አፕል 2ነጥብ8 ትሪሊዮን ዶላር፣ 2ኛ ማይክሮሶፍት 2ነጥብ3 ትሪሊዮን ዶላር፣ 3ኛ ጉግል 1ነጥብ7 ትሪሊዮን ዶላር፣ 4ኛ አማዞን 1ነጥብ4 ትሪሊዮን ዶላር 5ኛ ነቪዲያ 1ነጥብ1 ትሪሊዮን ዶላር

 ሲሆኑ፤ 6ኛው የሳውዲ አራመኮ በ2 ትሪሊዮን ዶላር የመንግሥት ድርጅት ነው። በመሆኑም የአሜሪካው የኢኮኖሚ ኃያልነት የመነጨው የተማረን ዜጋና የግለሰቦች ነጻነት ለሀገር እድገት በአደረጉት ጣምራ አስተዋጽኦ ነው። ይህ በአሜሪካ ለረጅም ጊዜ የቆየ ትምህርትን ለዜጎች የማዳረስ ተግባርና (ለማሳያነት፣ 3ሺህ 266 ዩኒቨርሲቲዎች አሏት) ለግለሰቦች የባለንብረትነት መብትና ነጻነት እጅግ አድርጎ ለትናንሽም ይሁን ለትላልቅ ሀገሮች የሚጠቅም ማስተማሪያ ነው ማለት ይቻላል።

ሌላው በአጠቃላይ እጅግ በጣም የበለጸጉ ሀገሮች የጋራ ባህሪይ ሁሉም በአማካይ ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ ከ40 ዩኒቨርሲቲ በላይ አላቸው። ለዜጎቻቸው የከፍተኛ ትምህርትን በሰፊው በማዳረስና ግለሰቦች በሀገር እድገት እንዲሳተፉ የሚደረገው የፖሊሲ ማመቻቸት እጅግ በጣም የሰለጠነ ፖሊሲ ሆኖ ነው የምናየው። በዚህ ረገድ በአማካይ፡-

  • ማሌዢያ 116 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፤
  • ካናዳ 101 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • ፖላንድ 99 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • አሜሪካ 97 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • ሜክሲኮ 97 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • ኢንዶኒዢያ 95 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት

እነዚህ ሀገሮች ቀደም ብለው የከፍተኛ ትምህርትን የጀመሩ ናቸው ብለን የአፍሪካ ሀገሮችንም በአማካይ በ10 ሚሊዮን ሕዝብ ምን ያህል ዩኒቨርሲቲዎች እንዳላቸው ብንመረምር፣

  • ኬንያ 24 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • አልጄሪያ 24 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • ጋና 22 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • ደቡብ አፍሪካ 17 አብዛኛዎቹ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን አላት፣
  • ናይጄሪያ 14 አብዛኛዎቹ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፣
  • ሱዳንና ዩጋንዳ 13 ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሚሊዮን አላቸው፣
  • ኢትዮጵያ ግን 6 ዩኒቨርሲቲዎች ነው ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ በአማካይ ያላት። ይህም ደግሞ ትናንሽ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ቆጥረው ነው እንጂ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ካየን ለ10 ሚሊዮን ሕዝብ 4 ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ነው ያለን።

የዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር ብቻ ሳይሆን በየዓመቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብቶ የመማር እድል የሚሰጠውንና የሚያገኘውን ተማሪ በተለይ ከአለን የሕዝብ ቁጥርና አስፈላጊነት በመነሳት መመርመሩ እጅግ አድርጎ ለሀገር እድገት የሚጠቅም ይሆናል። የሌላውን አህጉር ሀገርና ሕዝብ ትተን በአፍሪካ እንደ እኛ ብዙ ሕዝብ ያላቸውንና ጎረቤት ሀገሮችን እንኳ በሌላ መለኪያ ብናይ ለሀገራችን እድገት ብዙ ማድረግ ያለብን መሆኑንና ከአንዳንድ በጥናት ላይ ባልተመሰረቱ ውሳኔዎች እንድንቆጠብ ይረዳናል ብዬ እገምታለሁ።

ለአብነትም፣ በግብጽ በየዓመቱ ወደ ሶስት ሚሊዮን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተመዝግበው ይማራሉ። በናይጄሪያ ደግሞ በየዓመቱ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች በየዩኒቨርሲቲዎች ተመዝግበው ይማራሉ። ሕዝቧ የኛ ግማሽ ገደማ በሆነችው የጎረቤት ሀገር ኬንያ ወደ 650 ሺህ ተማሪ በተለያየ ደረጃ በየዓመቱ በየዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተመዝግቦ ይማራል።

የሌሎች ይህን የሚመስል ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን በዓመት በጠቅላላው ከ800 ሺህ ገደማ የተማሪዎች ቁጥር አልፈን የምናውቅ አይመስለኝም። እንደ 2015ቱ የዩኒቨርሲቲ አቀባበል በየዓመቱ 30 ሺህ በመቀበል የቀጠልን እንደሆነ ደግሞ በተለይ ከ4 ዓመት በኋላ ድህረ ምረቃ ፕሮግራምን ጨምሮ በጠቅላላ ዓመታዊ ምዝገባ ከ120 ሺህ እስከ 150 ሺህ ዝቅ እንደምንል ይታየኛል።

ይሄ ደግሞ የሕዝባችን ቁጥር በየዓመቱ እያደገ በሚሄድበት በአሁኑ ወቅት 150 ሺህ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ዩኒቨርሲቲዎች እያለን 30 ሺህ ብቻ መቀበላችንና ከ1ሺህ 161 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ምንም ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብቁ አልሆነም መባሉ ሌሎች የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ እየተጠጋን ሳይሆን እየራቅን ወይም ወደኋላ እያፈገፈግን መሆኑን በደንብ መገንዘብና ማመን አለብን። ማመን ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ መፍትሔ መፈለግና መተግበር አለብን።

የዛሬ ዓመት መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ መስከረም 26 ቀን 2015 ደግሞ በሪፖርተር ጋዜጣ በጻፍኩት ዝርዝር ዘገባ የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎትን ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ ይሄንን በአጭሩ ያህልም፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋናው ኃላፊነታቸው በአብዛኛው በተለያየ ሙያ ማስተማር፣ እውቀትና ክህሎትን ማስጨበጥ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የምርምር፣ የሥርጭት፣ የተከታታይ ትምህርትና የሥራ እድል የመክፈትን ተግባርም አብሮ በዋነኝነት መታየት ይገባል ። በዓለም ዙሪያ ባሉ ሀገሮች ሁሉ የተማረ ዜጋ በብዛት በአንድ ተቋም ከሚሰራባቸው ተቋማት ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአማካይ የአንደኝነቱን ቦታ ይይዛሉ። በእኛ ሀገርም እንደሌሎች ሀገሮች ሁሉ በርካታ የተማሩ ዜጎች በብዛት ከሚገኙባቸው መሥሪያ ቤቶች መሃል ዩኒቨርሲቲዎች የአንደኝነቱን ቦታ እንደሚይዙ ምንም አያጠራጥርም። ስለሆነም የተማረን ሰው አገልግሎት ተጠቅመን ማደግ ከፈለግን የዩኒቨርሲቲ ቁጥራችንን ከሕዝባችን ማደግ ጋር ማጣጣምና እንደሌሎች ሀገሮች ሁሉ ማድረግ ያለብን መሆኑን መጠቆም እፈልጋለሁ።

ልብ ልንለውና ልንገነዘበው ከሚገባን የማደግ ሃሳብ፣ አሁን አድገው የምናያቸው ሀገሮች በሙሉ በአንድ ወቅት አሁን እኛ አለንበት እድገት ደረጃ ላይ ነበሩ። ያም ሆኖ ለማደግ ከወሰዷቸው በርካታ ርምጃዎች ውስጥ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የከፍተኛ ትምህርት ሥርጭት ማሳደግና ግለሰቦች የንብረት ባለቤት የመሆን መብት ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ።

የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት ማስፋፋት አዲስ ቴክኖሎጂ መገንባት የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን የተፈጠረውን ቴክኖሎጂ ለመጠቀምና ለህብረተሰብም አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት ማለት ነው። የሀገር እድገት የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋትንና መዳረስን ከአየንና ከመረመርን የአደጉ ሀገሮች በሙሉ ከአሁን በፊትም ሆነ አሁን በተለየ መልኩ ትኩረትና ቅድሚያ የሚሰጡአቸውን የሙያ ዘርፎች ማየቱ ለአለንበት የእድገት ደረጃ እጅግ በጣም አድርጎ የሚጠቅመን ይመስለኛል። ለግብርናውና የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ፣ ለምህንድስና ትምህርትና ለሕግ ትምህርት ትኩረት መስጠቱ ለሕዝባችን የተመቻቸ የመሥራትና በሀገር እድገት የመሳተፍ እድል ያላቸውን ዜጎች ልታፈራ ትችላለች ብሎ ለመናገር ያስችላል።

ለምሳሌ፣ በግብርናውና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በቂ የተማረ ሰው ካፈራንና አመቺ የግለሰቦች የባለንብረትነትንና ተሳትፎ ፖሊሲ በሀገራችን ካደገ የግብርናው ዘርፍ ዜጎችን መመገብ የሚችል ምርት ማምረት ይችላል። ዜጎችን ከመመገብ አልፎ ለፋብሪካዎች ጥሬ እቃን በሰፊው ማምረት ይቻላል። ከዚያም በማለፍ ለንግዱ ዘርፍ ወደ ውጭ የሚሸጡ ምርቶችንና ከውጭ የሚገዙ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶችን ማምረት ይችላል። የተማረ ዜጋ በበቂ መጠን ካሰለጠንን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃውና እድገት የተጠናከረ ማድረግ ይቻላል። በተጨማሪ በጤና፣ በትምህርት ወዘተ ዘርፉም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎችም በብዛት ይኖሩናል ማለት ነው።

በተለያዩ የምህንድስና ዘርፎች የተማረ ዜጋ ለኢንዱስትሪው፣ ለቴክኖሎጂው፣ ለግብርናው፣ ለማዕድን ለተለያዩ ግንባታዎች፣… ዘመናዊነትና መስፋፋት እጅግ አድርጎ መሠረት ይጥላል። እጅግ አድርገው በተለያየ መስክ በላቀ መልኩ የሰለጠኑና በመሰልጠን ያሉ የዓለም ሀገሮች በሙሉ ለምህንድስና ትምህርት የሰጡትና የሚሰጡት ትኩረት እጅግ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም ከጃፓን፣ ከምስራቅ ኤዢያና ከስሜን አሜሪካ የሃምሳና የመቶ ዓመታትን ልምድና ያለፉበትን ቆም ብሎ መመርመሩ እኛስ መሃንዲሶችን በብዛት በማስተማር እንዴት እንደግ ለሚለው ጥያቄ አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ስለሆነም የምህንድስናውን ትምህርት በማስፋፋት ፖሊሲ አውጪዎች ሌሎች ያደጉበትን ቅደም ተከተል መርምረው ለእኛ የሚበጀውን በመለየት ልንጠቅምበት ይገባል እላለሁ።

የሕግ ትምህርት መስፋፋትንና ለሀገር እድገት ያለውን ሚና ለማስረዳት ብዙ ማለት ይቻላል። ነገር ግን በአጭሩ ሕግ በአደጉት ሀገሮች እንዴት እንደሚከበርና ማንም ከሕግ በላይ መሆን እንደማይችል በተግባር የሚታየው ለሕግ ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል። የሕግ አገልግሎት በደንብ በሰፈነባቸው ሀገሮች ማንም ካጠፋ በሕግ በማንኛውም ጊዜ ተጠያቂ ይሆናል። በሕግ ጥላ ከለላ ያላቸው መሆኑን የሚያውቁ ዜጎች ደግሞ ለሀገራቸው ያላቸውን አስተዋጽኦ መመርምሩ ለእኛም ሀገር መማሪያ መሆን ይችላል እላለሁ።

ለዚህ ማሳያው፣ እጅግ በጣም የተማረ ዜጋና በሕግ የሰለጠኑ በርካታ ዜጎች ያላቸው የስካንዴቪያ ሀገሮች ለፖሊስና ለሕግ አስከባሪዎች ብዙ ወጪ አያወጡም። ለዚህም መነሻው ዜጎቻቸው የሀገራቸውን ሕግ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው ማለት ይቻላል። ጥርት ያለ የሕግ ከለላ ከአለ የግለሰቦች የመሥራትና የንብረት ባለቤት የመሆን መብት የተረጋገጠ ይሆናል። በሀገር ደረጃም ይሁን በክፍለ ኢኮኖሚ የሚወጡ ሕጎች ሁሉ የግለሰብ ውሳኔ ሳይሆኑ በሕግ የሚመሩ የቡድኖች ሥራ ሊሆኑ ይችላሉ። የሕግ ትምህርት ባልተስፋፋበት ሀገር በተለያየ ደረጃ የሚያገለግሉ ብዙ መሪዎችን፣ ሕግ አውጪዎችንና አስፈጻሚዎችን ማፍራት አይቻልም። ስለሆነም ከአለንበት የእድገት ደረጃ ከፍ ለማለት በርካታ ሕግ ተምረው የሚያገለግሉን ዜጎችን ማፍራት የግድ ነው።

ሀገራችንን ለማሳደግ የግለሰቦች ተሳትፎና ዜጎችን በሰፊው ማስተማር አብዛኛዎቹ የአደጉ ሀገሮች የተጠቀሙባቸውና ተከትለዋቸው ከነበሩ በርካታ የእድገት መንገዶች መሃከል መሆኑን ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ። እኛም ሀገራችንን ለማሳደግ የምንተገብራቸው ሥራዎች የራሳችንና ከራሳችን አቅም ጋር የተጣጣሙና ከሌሎች ልምድ የምናገኛቸው ቢሆኑ ሊጠቅሙን ይችላሉ። ይህ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ ያደረጉት በመሆኑ እኛንም እንደሚጠቅም ብዙም አያጠራጥርም። ቢያንስ ዜጎቻችንን በሰፊው በማስተማርና የግለሰቦችን ተሳትፎ በየዘርፉ በማሳደግ በጣም እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር በማንኛውም ጊዜ መመገብ፣ ማልበስና መጠለያ ያለው እንዲሆን ማድረግ እንደምንችል እርግጠኛ መሆንና መቻል አለብን።

በሌላ በኩል ደግሞ ከተፈጥሮ ሃብታችን፣ የአየር ጠባያችንና ከሀገራችን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ልናገኝና ልንጠቀም የምንችለውን ጥቅም ማግኘት የምንችለው ዜጎቻችንን በሰፊው ስናስተምርና አሥራ ሦስቱንም ወራት የእርሻ ምርት ማምረት ስንችል ነው። ይህን ማድረግ ከቻልን እኛ የምናመርተውንና በርካታ በቅርብ ያሉ በረሃማ ሀገሮች የማያመርቱትን አምርተን ለመጠቀም፣ አውሮፓ በበረዶ ሲሸፈን የማያመርቱትን አምርተን ለመጠቀም እንድንችል በርካታ የተማረ ሰው ያስፈልገናል።

ከዚህም በተጨማሪ በሀገራችን በአለፉት ጥቂት ዓመታት ከተመቻቹ በርካታ ሁኔታዎች ውስጥ በበቂ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የኃይል ማመንጨት አቅም በመጠቀም በየዘርፉ ምርት ለማሳደግ፣ በየዘርፉ የተማሩ ብዙ ዜጎች ያስፈልጉናል። የሕዝባችንን የእድገት ፍጥነት ካየን የምንለብሰውን ልብስ ሁሉ ከውጭ እያመጣን ከመልበስ ደረጃ አቅጣጫችንን በቶሎ ለመቀየር በጥጥ፣ በሱፍና ሲንተቲክ ፋይበሮችን በማምረትና ሕዝባችንን በሀገር የተመረተ ልብስ ለማልበስ አሁንም የተማሩ ዜጎች በብዛት ያስፈልጉናል።

80 በመቶ የሚሆነውን የገጠር ሕዝባችንንም ኑሮ ለመለወጥ ከዚያው ከገጠር የመጡና ወደገጠር ለመመለስና ተቀላቅሎ ለማገልገል ፈቃደኛ የሚሆኑና የሚችሉ ከገጠር የወጡ ብዙ የተማሩ ዜጎች ያስፈልጉናል። በቅርቡ የተቀላቀልነውን የBRICS አባል መሆን የቻልንባቸውን በርካታ ሁኔታ ከፍተኛ ዋጋ ሰጥተናቸው የኢኮኖሚ የዲፕሎማሳዊና የፖለቲካ ጥቅሙን ለሀገራችንና ለሕዝባችን በረጅም ጊዜ በተግባር ለማየት እንድንችል እንደሌሎቹ አባሎች ሁሉ ቢያንስ ሕዝባችንን በብዛት ማስተማር አለብን፣ አምርተንም እዚህ ሰፊ ገበያ ውስጥ ለመግባት አስፈላጊ ጥረት ማድረግ አለብን።

ፍላጎትንና ፍጆታን ለማጣጣም በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች መሥራትና እንዳለባቸው ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን በብዙ ዘርፍ ለማሳደግ የግለሰቦች የንብረት ባለቤት የመሆን መብትንና ተሳትፎ አስፈላጊነትን፣ የከፍተኛ ትምህርትን እና በከፍተኛ ትምህርትን የተማሩ ዜጎች በጣምራ ያላቸውን ጥቅም ለማሳየት ነውና የሀገራችን ፖሊሲ አውጪዎች በዚህ ረገድ ብዙ ማድረግ እንዳለባቸው ለመጠቆም እወዳለሁ።

ጋሹ ሀብቴ (ዶ/ር)

Ghabte12@aol.com

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016

Recommended For You