ወላጆችም ይማሩ!

ከዓመታት በፊት ለበዓል ወደ ቤተሰብ በሄድኩበት አጋጣሚ አንድ መምህር ጓደኛዬን አግኝቼው ያጫወተኝ ነገር በትምህርት አጋጣሚዎች ሁሉ ትዝ ይለኛል። ይህ ጓደኛዬ አብረን የተማርን ሲሆን እሱ እዚያ የተማርንበት ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር ሆነ። በተገናኘን ቁጥር ያለፈ ትዝታችንን እያነሳን እንጫወታለን። ከዓመታት በፊትም ተገናኝተን ተጫወትን።

በጨዋታችን ውስጥም ያው ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› የሚለው በሁለታችንም በኩል ተነሳ። በተገናኘን ቁጥር የሚነግረኝ ነገር የተማሪዎችን ጎበዝ አለመሆን ነበር። እኔም የቅርብ ጓደኛዬ ስለሆነ ‹‹መምህሩ ጎበዝ ሲሆን ነው ተማሪ ጎበዝ የሚሆን›› እያልኩ በቀልድም በቁም ነገርም እነግረዋለሁ። እሱም ‹‹ስላላየኸው ነው የምትፈርድ! ምንም ማንበብና መጻፍ የማይችልን ተማሪ ከየት ጀምሮ ነው ጎበዝ ማድረግ የሚቻል›› እያለ ይሞግተኛል (እሱ የሚያስተምረው ሁለተኛ ደረጃ ነው)። ይሄም ከታች ክፍል ያሉ መምህራን ችግር ነው እየተባባልን እንከራከራለን።

በዚያ ዓመት የነገረኝ ነገር ግን ከዚህም ከበድ ያለ ሆነ። ‹‹ተማሪዎችን ‹ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?› ብትላቸው፤ እንደ ድሮው ‹ዶክተር፣ ኢንጂነር..› የሚሉ እንዳይመስልህ! ምኞታቸው፤ ሴቶች ወደ አረብ ሀገር፣ ወንዶችም ወደ ወርቅ ቁፋሮ ነው የሚሉህ›› አለኝ። ምኞታቸው ብር የሚያገኙበትን አጋጣሚ ማመቻቸት ነው። ትምህርት የማይማሩ ጓደኞቻቸው ሄደው የመጡበት አካባቢ መሄድ ነው ፍላጎታቸው። ወላጆችም ገንዘብ ካመጡልን በማለት ብዙም አይቆጧቸውም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ የሚፈቅዱላቸውና ሂዱ የሚሏቸውም አሉ። ቁጥራቸው በዛ ያለው ከ5ኛ ክፍል በታች ያሉት ናቸው። እነሱም ዕድሜያቸው ገና ለመሄድ ስላልደረሰ ነው።

ይሄ የመሄድ ፍላጎት ገና በልባቸው ሲጠነሰስ ለትምህርቱ ትኩረት አይሰጡም። መሄድ ሳይችሉ ቢቀሩ እንኳን ፈተና አያልፉም። እንኳን ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ የክፍል ውስጥ ፈተና እንኳን የሚያመጡት ውጤት ዝቅተኛ ነው።

ከዚህም በላይ አሳዛኙ ደግሞ የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመምህራኑም ተስፋ መቁረጥ ነው። ‹‹ምክንያቱ ምን ይሆን›› ያልኩት ጓደኛዬ እንደሚለው የብዙ መምህራን ቅሬታ ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር፣ ከሥራ መሰላቸት ጋር የመጣ ነው። የሥራ መሰላቸቱንም ያመጣው ከኑሮ ውድነት ጋር የሚከፈለን ክፍያ አይመጣጠንም በሚል ቅሬታ ነው።

ይሄ ነገር ትውልድ ገደላ ነው። መምህራን መንግሥት ላይ ያላቸውን ቅሬታ የሚገልጹት ተማሪ ላይ ከሆነ ይሄ የእውቀት አባትነት ሳይሆን ጨለማን ማውረስ ነው። እርግጥ ነው የሚከፈለው ክፍያ በቂ ነው ማለት አይደለም። በቂ አለመሆኑ ግን የተማሪዎችና የወላጆች ችግር አይደለም፤ የመንግሥት ችግር ነው። ያንን ከመንግሥት ጋር ነው መነጋገር። እልሃቸውን ተማሪ ላይ አይደለም መወጣት ያለባቸው። የጠየቁት ጥያቄ ካልተመለሰ ወይም በውይይት መፍትሔ ላይ ካልደረሱ ሥራውን መልቀቅና የተሻለ ካለ መፈለግ ነው!

በነገራችን ላይ ይሄ ችግር የሚታየው መምህራን ላይ ብቻ አይደለም። በብዙ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቀጣሪ ሰራተኞች ላይ የሚታይ ነው። የግል ትምህርት ቤት ላይ ቢዝረከረክ በነገታው እንደሚባረር ስለሚያውቀው ማንም አይዝረከረክም። የመንግሥት ተቋማት ላይ ግን ይሄ ነገር ጎልቶ ይታያል። ብዙ ጊዜ የታዘብኩትን ነገር ልንገራችሁ።

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሾፌር ይቀጥራሉ። ሹፌሮችም ሠራተኞችን ወደ ሥራ ቦታ ይወስዳሉ። ይህ ሲሆን ታዲያ ሾፌሮች በለቅሶና በጭቅጭቅ ነው። ከመስሪያ ቤት ሲወጡ አለቃቸው ያዘዛቸውን ‹‹እሺ›› ብለው ይወጣሉ። ከዚያ በኋላ ከሠራተኛው ጋር ጭቅጭቅ

 ትለግሳለች።

ይፈጥራሉ። ‹‹እዚህ ቦታ አልሄድም፣ በዚህም አልሄድም፣ እዚህ አልጠብቅህም›› ይላሉ። ይባስ ብሎ በፉከራ ‹‹ማን አባቱ ነው የሚያዝዘኝ፣ እስኪ ማን እንዲህ አድርግ እንደሚለኝ አያለሁ!›› እያሉ ፉከራ!

የቅሬታቸውን ምክንያት ሲናገሩም፤ ‹‹በዚህ ደመወዝ አልሰራም! አንተ ይህን ያህል እየተከፈለህ እኔ ልፈጋልህ ነው!›› እና ታዲያ ሥራውን ለቆ የተሻለ ካለ መፈለግ ነዋ!

ወደ መምህራኑ ስንመለስ የእነርሱ ደግሞ ከዚህም ይከፋል። የእነርሱ ማኩረፍ እንደሌላው ማኩረፍ አይደለም። ትውልድ ላይ ነው እየሰሩ ያሉት።

የተማሪዎች ተስፋ መቁረጥ ግን የመምህራን ችግር ብቻም አይደለም። ይሄ የወላጆችም ችግር ነው። አለፍ ሲልም የትምህርት ዋጋ ማጣት ነው። ከእነርሱ በፊት የተማሩ ሲያማርሩ ከሰሙ ከታች ያሉት ተስፋ ይቆርጣሉ። ተምሮ ሥራ የለም፤ በደመወዝ መኖር ከባድ ነው፣ ሥርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል እውቀት ላይ ያተኮረ አይደለም… የሚሉ ቅሬታዎች ተደጋግመው የሚሰሙ ናቸው። ታዲያ ይሄን እየሰሙ ይሆን?

የትምህርት ነገር ገና ብዙ ያልተስተካከለ ነገር አለው። በቅርብ ዓመታት በወጣው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ዲግሪ ያለው ይሆናል ተብሏል። ይሄ ጥሩ ነገር ነው። የመምህራን ብቃትና ቆራጥ ውሳኔም አንዱ አጠያያቂ ነገር ስለነበር። ከ10ኛ እና ከ12ኛ ክፍል ውጤት ያልመጣለት ተማሪ ነበር እኮ መምህር የሚሆነው! ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀውም ቢሆን ብዙም የተሻለ አይደለም። ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ ትምህርት ክፍል የሚመደቡት ከ12ኛ ክፍል ዝቅተኛ ውጤት ያመጡት ናቸው። እነዚህ ወሳኝ እና ለሁሉም የትምህርት ክፍል መሰረት የሆኑት የትምህርት አይነቶች ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ‹‹ኮምፒቴሽናል ሳይንስ›› በሚለው ውስጥ ናቸው። ይሄ ዘርፍ ማለፊያ ነጥቡን ብቻ ያመጡ ተማሪዎች ሳይመርጡት የሚመደቡበት ነው። እንደ ህክምና፣ ምህንድስና፣ ጤና፣ መሬት አስተዳደር፣ የመሳሰሉ የትምህርት ክፍሎችን መርጠው የሞሉ ተማሪዎች ያንን ካላገኙ የሚመደቡት ‹‹ኮምፒቴሽናል›› እና ‹‹አዘር ሳይንስ›› የሚባለው ውስጥ ነው። መምህር የሚወጣው ደግሞ ከዚህ ዘርፍ ውስጥ ነው። አሁን ግን በመጀመሪያው ዓመት ጠቅላላ የሆነውን ነገር ተምረው ከዚያ በኋላ ነው የሚመርጡት።

የትምህርት ክፍሎችን አወቃቀር ለአሰራሩ እንተወውና ወደ ተማሪዎች የትምህርር ፍላጎት እንመለስ። ይህን ነገር ብዙ ሰው በአዲስ አበባ ዓውድ ካየው ልክ ላይሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የተሻለ (ቢያንስ የማንበብና የመጻፍ) ችሎታ ይኖራቸዋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ከአንድ ዓመት በፊት እንደገለጹት፤ ምንም መጻፍና ማንበብ የማይችሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተገኝተዋል። ስሌቱንም በመቶኛ ሲያስቆምጡት ነበር፤ ያ መደገም የለበትም።

ትምህርት ሚኒስቴር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ብዙ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፤ ዳሩ ግን የልጆቹና የወላጆች አመለካከት ላይ ደግሞ መሰራት አለበት። ዛሬም ቅስቀሳ የሚፈልግ ወላጅ ያለበት አካባቢ አለ። እነዚያ ልብ መባል አለባቸው። በከተሞቹ ዓውድ ብቻ መታየት የለበትም። አንዳንድ ወላጆችና ልጆች ወደ ትምህርት ቤት በጊዜ የማይሄዱት ከሥርዓተ ትምህርቱ ጋር በተያያዘ ጉዳይ አይደለም፤ በአመለካከት ነው። የሥርዓተ ትምህርቱ መሻሻል ብቻውን የነበረውን የተዛባ አመለካከት አይቀይረውምና ዛሬም ግንዛቤ ሊሰጣቸው የሚገባ አሉ። ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማያስገቡ ወላጆችንም ማንቃት አስፈላጊ ነው። ‹‹በዚህ ዘመን ልጁን የማያስገባ አለ እንዴ?›› ማለት የተሳሳተ ግምት ነው። ለዚህ የተሳሳተ ግምት የሚዳረገው ደግሞ በከተማው ዓውድ ብቻ የሚረዳ ሰው ነው። በዚህ ላይ አሁንም ዘመቻ ያስፈልጋልና ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ቅስቀሳ ሊደረግ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You