ሠላማዊ መንገድ አማራጭየሌለው ምርጫችን ነው

በአዲሱ ዓመት ወደ ሠላም፣ እድገትና የተሟላ ማንነት ሊወስደን የሚችል አዲስና የተሻለ አስተሳሰብ መያዝ እንዳለብን ይታመናል። ይህንን ለማሳካት «ጊዜ ብቻ ሳይሆን መቀየር ያለበት እኛው እራሳችን ጭምር ነን» የሚል እሳቤ ያላቸው ብዙኃን ናቸው።

ምክንያቱ ደግሞ ዓመቱ ተቀይሮ አስተሳሰባችን ቀድሞ የነበረበት (የጥላቻ፣ የዘር፣ የግጭት) እሳቤ ውስጥ የተዘፈቀ ከሆነ ጊዜ መቀየሩ ብቻ ዕድሜን ከመቁጠር ውጪ የሠላም፣ የፍቅር የአንድነት እሳቤን ስለማይሰጠን ነው። ከዓመቱ ጋር ወደ ፍፁም የሠላምና የአንድነት ልዕልና የምንሻገር ከሆነ ግን እውነትም «ከጊዜው ጋር እኩል ተቀይረናል» ለማለት ያስደፍረናል።

ከላይ ያነሳነውን ተጠየቅ ተንተርሰን እኛ (ኢትዮጵያውያን) የመረጥነውን መንገድ ለመፈተሽ ብንሞክር ምላሻችን በጊዜ ሂደት የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከእስካሁኑ ግን «ጊዜው ብቻውን እንጂ እኛም ከጊዜው ጋር» አለመቀየራችንን ለመታዘብ የሚቸግር አይመስለኝም። ለዚህም መልካም ምኞቶችን እየተመኘን በሁከትና በብጥብጥ ያሳለፍናቸው አመታትን መቁጠር በቂ ነው።

ልዩነቶቻችንን ቁጭ ብሎ በመነጋገር አጥብቦ በሠላም ከመመላለስ፤ ዛሬም ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ያልተገቡ ጥረቶች ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሰፊውን ማኅበረሰብ የሚወክል ባይሆንም ወደ እሱ ለማጋባት የሚደረጉ ጥረቶች አደገኝነት በራሱ የሀገራዊ ስጋት ምንጭ መሆኑ አይካድም።

«ማኅበረሰብን አንቂ ነን፤ የፖለቲካ ሊሂቃን ነን፤ ተፅእኖ ፈጣሪ ነን» ወዘተ የሚሉ ግለሰቦች ዘመኑን በማይዋጅ በዚህ አስተሳሰብ ታጅለው በየአደባባዩ ሲንገዋለሉና ሲጮሁ መስማት የተለመደ ነው። እውነታው በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ከመከተት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

«አዲስ ዓመት ብለን» ልዩነታችንን የምናቻችልበት አዲስ እሳቤና የተሻለ አማራጭ ለመያዝ ቁርጠኝነቱ ከሌለን ነገም በትናንቱ ችግራችን ውስጥ መቆየታችን የማይቀር ነው። አዲሱንም አመት አሮጌ ማድረጋችን የማይቀር ነው።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአዲስ ዓመት መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት «ችግሮቻችንን በጊዜያዊ ጥገና ሳይሆን ከመሠረቱ ለመፍታት የምንንቀሳቀስበት ዘመን እናድርገው፡፡ በሠላም ግንባታ፣ በውይይትና ምክክር፣ በጋራ ጉዳይ ሀገራዊ መግባባት ላይ በመድረስ፣ ጥላቻ፣ መናናቅ፣ መገፋት፣ ጥቃትን በጽኑ በመታገል መብቶችን በማክበር፣ በማስከበር ሁላችንም ድርሻ አለን፡፡ የዓመቱ ዋና ትኩረታችን ይሁን፡፡ አዲስ ዓመት አዲስ እይታን፣ የአስተሳሰብ እድሳትን፣ የተሻለ እንድንሠራ ቃል መግባትን ይጋብዛልና እንጠቀምበት» ማለታቸው ይታወሳል።

መልዕክቱ ከሁሉም በላይ እንደ ሀገር ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ወደኋላ እየጎተተን ከሚገኝ ችግር መውጣት እንደሚጠበቅብን የሚያመላክት ነው። ዓመቱ ሲቀየር እኛ በአዲስ እሳቤ ለመቀየር በመቸገራችን ሰቅዞ ከያዘን የልዩነት አዙሪት መውጣት አለመቻላችንን የሚጠቁም ነው።

ለችግሮቻችን ሰላማዊ መንገድ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ይነግረናል። ሥልጣኔን፣ እድገትና አብሮነት በዚህ መሰል ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚገኝ እንጂ ለዓመታት በቆየንበት የጥላቻ፣ የመገፋፋትና ልዩነትን የማጉላት መንገድ እንደማይመጣ በግልፅ የሚያስረዳ ሆኖ እናገኘዋለን።

ላለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ጫፍና ጫፍ በረገጡ እሳቤዎች ተወጥረው ቆይተዋል። እነዚህ ፅንፍ የያዙ መሳሳቦች ማኅበረሰባችን ሰላማዊ ሕይወቱን እንዳይመራ፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዳይፈጠር አድርገዋል። ከመነጋገር ጠብ-መንጃን ምርጫ ማድረግ ዛሬም እንደ ሀገር ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል እያደረገን ነው።

ከዚህ በዘመናት መካከል ብዙ ዋጋ ካስከፈለንና ዛሬም እያስከፈለን ካለው አሮጌ ጊዜ ያለፈበት የፖለቲካ ባህል፤ ወጥተን ችግሮቻችንን በውይይትና በመነጋገር መፍታት ወደምንችልበት ያደገ የፖለቲካ ባህል መጓዝ አለብን። ለዚህም ሃሳብን በኃይል ገዥ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አደብ መግዛት ይኖርባቸዋል። ይህ የአሮጌው ዘመን እሳቤ ማብቂያ ሊበጅለት ይገባል።

ዛሬም ለውይይትና ለድርድር፤ ለሃሳብ ልዕልና በራቸውን ክፍት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ መሆን ሲችል ብቻ ነው ከዘመኑና ቀን ቆጥሮ ከሚቀየረው አዲስ ዓመት ጋር እኛም መቀየራችንን እርግጠኝ መሆን የምንችለው። ለመልካም ምኞታችን ባለ ጉዳዮች የምንሆነው።

በርግጥ ምሁራን፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ጦር የሰበቁ አካላት ሁሉም የሚያነሱት የልዩነት ጥያቄዎች ሊኖራቸው ይችላል። የማያግባቡ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ርዕሰ ጉዳዮችና አጀንዳዎችም አይጠፉም። ይህ እንደ እኛ ባለ ብዝሃነት መገለጫው ለሆነ ማኅበረሰብ አዲስ ሊሆን አይችልም። የሚጠበቅ ነው።

ዋናው ቁምነገር መሆን የሚገባው ግን፤ የትኛውንም ዓይነት ልዩነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት፤ የሃሳብ የበላይነት መሠረት ባደረገ መንገድ ለመፍታት እራስን ሁሌም ዝግጁ ማድረግ ነው። ይህንንም በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ፤ ሉዓላዊነትን በማይጥስ አግባብ ለመከወን ለሚያስችል መርህ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆን ነው።

ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ብዙ ሂደቶችን አልፎ ወደ ሥራ ለመግባት እየተንደረደረ ያለው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ትልቅ አቅም ነው። መንግሥት የሀገሪቱ ያደሩ ሆኑ ከነሱ የተዋለዱ አሁነኛ ችግሮቻችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል። ለተፈጻሚነቱም ገለልተኝ ተቋም መሥርቷል (ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን)።

በርግጥ ለሀገሪቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስቦ መነጋገር ወሳኝ ነው። ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ያካተተ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ በመድረኩ ሁሉም ልዩነቶች በአግባቡ ሊታዩ እና ሊመረመሩ ይገባል። ተጨባጭ ስለመሆናቸውም ማስተማመኛ ማግኘት ያስፈልጋል።

ለዘመናት የቆዩ ቁርሾዎችን ፈር ለማስያዝ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት፣ የልማት፣ የወሰን እና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት አዲሱን ዓመት በአዲስ እሳቤና ቀና መንፈስ ልንቀበለው ይገባል። የሰው ልጅን ሰብዓዊ ክብር ከሚያዋርደው ጦርነትና ግጭት ከቂምና ቁርሾ ባለፈ የምናተርፈው ምንም እንደሌለ በአግባቡ ማጤን ይገባናል።

በድህነትና በልማት እጦት ችግር ውስጥ የሚገኝን ማኅበረሰብ ወደ ግጭትና ጦርነት ገፋፍቶ «ከድጡ ወደ ማጡ» ከመውሰድ ይልቅ ልዩነቶችን እና ሃሳቦቻችንን በንግግር የመፍታት ልምድ ማዳበር ይኖርብናል። እነዚህ ልዩነቶች ደግሞ ከሕዝብ ሠላም ከሀገር አንድነት በታች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ቀደም ሲል እንዳነሳሁን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ ነው ፤ ይህንን ጥረት በማገዝ የሀገርን ሰላም ማጽናት ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። በተለይ «በአዲስ ዓመት አዲስ እሳቤ» መያዝ ካለብንና ትናንት ከነበርንበት ያረጀ አመለካከት ለመውጣት ከወሰንን የሠላምን ቀና መንገድ ልንመርጥ ይገባል።

ሀገር አሸናፊ እንድትሆን ቅሬታን የፈጠሩ ጉዳዮችን ወደ ውይይት መድረኩ መጥተው መፍትሔ እንዲያገኙ የጋራ ጥረት ይፈልጋል። ከሁሉም በላይ ግን በመካከላችን የተፈጠሩ አጥሮች ሉዓላዊ ከሆነችው ኢትዮጵያ እንደማይበልጡ መተማመን ላይ መድረስ ይኖርብናል።

በዚህ መንገድ የሃሳብ ልዕልናን ብቻ መሠረት በማድረግ፣ መነጋገርን እና መደማመጥ ብቻ በማስቀደም፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መፍትሔ የሚሆኑ ሠላማዊ አማራጮችን ማግኘት እንችላለን። ለዚህ ነው በራችንን ለሠላሙ መንገድ ብቻ መክፈት የሚኖርብን። ሠላም!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You