ስለ ነገው ምን ታስቧል?

የአንዳንዱ ሰው ግዴለሽነት ከማስገረም አልፎ ያናድዳል። ነገ ሌላ ቀን አይመስለውም። ውሎ አድሮ ስለሚከተል ችግር ፣ ስለሚኖር ተጽዕኖ አንዳች አያስብም።፡ ባገኘው አጋጣሚ ያሻውን ይናገራል። ምስሉን ፣ ፎቶውን በፈለገው መልኩ አዘጋጅቶ ለሚፈልጋቸውና ለማይፈልጉት ጭምር ያሰራጫል።

እንዲህ ሲባል ጉዳዩ በዚህ ብቻ ይቋጫል ማለት አይደለም። ከሚለቀቀው ምስል ጋር አባሪ የሚሆን አስገራሚ መልዕክት አይጠፋም። የኔ ርዕሰ ጉዳይም ይኸው ነው። ምስላቸውን ከአጓጉል መልዕክት ጋር ለጥፈው ‹‹ስሙን፣ ጉዳያችንን እዩልን›› ብለው ነውራቸውን ስለሚያጋሩን አንዳንዶች።

መቼም ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ይሉት አያሳየን የለም። ከራስ ታሪክ ጀምሮ እስከሌሎች ጉድ ያስቃኘናል። ይህ አጋጣሚ ምስጢርና ነውር ስለሚባሉት እውነታዎች የሚጨነቅ አይደለም። ባለቤቱ የማያውቀውን ጉድ አውጥቶ ከአደባባይ ማስጣት ልማዱ ነው። አንዳንዶች በዚህ ማህበራዊ ሚዲያው አያምኑም። ተሳትፎው የላቸውም። ስማቸው በፌስ ቡክ ፣በቲክቶኩ መንደር አይነሳም። እንደውም ብዘዎቹ የሌሎችንም ገጽ ገልጦ የማየት ልምዱን ትተውታል። በእነሱ እሳቤ ይህን ማድረጉ ቢጎዳ እንጂ አይጠቅምም።

እንዲህ አይነቶቹ ወገኖች ታቅቦ መቀመጥን እንደ አማራጭ ቢወስዱትም ‹‹እናውቃችኋለን›› ባዮቹ ደግሞ ላይተዋቸው ይችላሉ። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ስማቸውን ያጠፋሉ ፣ ታሪካቸውኝ ያጎድፋሉ። ታዲያ ይህ ሁሉ ዘመቻ የሚካሄድባቸው ተጠቂዎች የሆነባቸውን በደል ላያውቁት ሁሉ ይችላሉ።

ስማቸው ስለመነሳቱ ከሌሎች በሚነገራቸው ጊዜ ግን እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። ምላሽና ማስተባበያውን ሊሰጡ ‹‹አለን›› ማለታቸው አይቀሬ ይሆናል። በዚህ ሰበብ ሳያስቡት ከዚህ መንደር ዘልቀው ቤተኛ ይሆናሉ። በስድብና በጥላቻ የተለጠፈባቸውን ስም ለመፋቅ ሲሊ ምላሽ ከሚዲያው መንደር ከርመውም የልማዱ ሱሰኛ ሆነው ይዘልቃሉ።

እንዲህ አይነቶቹን በርካታ አጋጣሚዎች ምሳሌ እየመዘዙ ማንሳት ይቻላል። ለዛሬው ግን እያስገረመኝ ስላለው አንድ እውነት ላነሳና ልታዘብ ግድ ብሎኛል።

በቅርብ ጊዜ ነው። ከአንድ የዩቲብ ሚዲያ ጋዜጠኛ ጋር ቃለመጠይቅ የሚያደርግ አንድ ግለሰብ አትኩሮት በሰጠበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር ትልቅ ውይይት ያደርጋል። የተነሳው ርዕስ የቤተሰብ ብሎም የባልና ሚስት ግንኙነት በመሆኑ በርካቶች እየተከታተሉት ነው። ጋዜጠኛው ይጠይቃል ። ግለሰቡ ፊቱ ሳይሸፈን ፣ድምጹ ሳይደበቅ ስለሚስቱ ገበና አንድ በአንድ ይዘረዝራል።

ወዳጆቼ! ልብ በሉልኝ እየተነሳ ያለው ጉዳይ ስለ ባልና ሚስት ነው። ተናጋሪው ደግሞ በግልጽ ማንነቱ ይታያል። የማን ባል፣ የነማን አባት እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም። በዚህ ጥላ ስር የተገነባው ቤተሰብ የሚባል ትልቁ ተቋም ህልውናው የታሰበበት አይመስልም። ሰዎች በቤታቸው በግል አልያም በምስጢር ሊያነሱት የሚገባው ጉዳይ የባቄላ ወፍጮ ሆኖ መከካት መቦካት ተይዟል።

ጋዜጠኛው አሁንም ይጠይቃል። በሚስቴ ተበድያለሁ ባዩ አባወራ የጀመረውን የቤቱን ገበና እንደክር ይተረትራል። የሚወራው ጉዳይ የተለመደው የቤት ወጪ፣ የቅናትና ጠብ ነገር አይምሰላችሁ ። ያለነውር እየተዘከዘከ ያለው የባልና ሚስቱ የፍቅር ግንኙነት ነው።

እንዲህ ስላችሁ ጉዳዩ በቃላት ብቻ አይወሳም። በሁለቱ ይሁንታ ሊቀር የሚገባው የአልጋ ላይ ጥምረት በግልጽ ተገልጦ ፀሀይ እንዲሞቀው፣ ሁሉም እንዲያውቀው እየሆነ ነው። ውይይቱ ጥንዶቹ ከሁለት አስር ዓመታት በላይ በዘለቁበት የትዳር ጎጆ የነበራቸውን ግንኙነት በገሀድ አውጥቶ ያሳያል።

በቆዩባቸው ጥቂት የማይባሉ የትዳር ዓመታት በቁጥር የተወሰነውን የፍቅር ግንኙነታቸው እያሰላ ውጤቱ አንሷል ፣ሳስቷል በሚል እሳቤ በግልጽ ይፈርዳል። ይህን ውይይት የሚከታተሉ ተመልካቾች ደግሞ ሰውየውን ደግፈው ሚስቲቱን አነውረው ያሻቸውን ይላሉ።

በጣም የሚገርው ነገር በዚህ መሀል ሊታሰብበት የሚገባው የልጆችና የመላው ቤተሰብ ጉዳይ ከምንም ያለመጣፉ ነው። ይህ እውነታ የሚዲያ ፍጆታ ከሆነ በኋላ የሚረሳ የሚዘነጋ ነው። ምንአልባትም የአንድ ሰሞን ግርምታን አጭሮ ርዕስ ከመሆን ይፋቃል። በእኔ ዕምነት ግን በሚመለከተው አካል አእምሮ አሳርፎ የሚያልፈው የበደል ጫና በቀላሉ አይታይም።

በተለይ ደግሞ የጉዳዩን ባለቤት በእጅጉ ያሸማቅቃል። በአካል ተገኝቶ ምላሽና ማስተባበያ በማይሰጥበት አጋጣሚ ስሙ መብጠልጠሉ ጉዳቱን ከፍ የሚያደርግ ስብራት ያስከትላል። እንደ ግለሰብ ጥንካሬው ካለ ግን በህግ መጠየቅና መክሰስ ጭምር ይቻል ይመስለኛል። ብዙ ጊዜ ግን በተለይ በቤተሰቦች መሀል እንዲህ ማደረጉ ላይ አልተለመደም።

በዚህ መሰሉ ውይይት መሀል ማንነታቸው በግልጽ የሚታወቁ ልጆች በባልንጀሮቻቸው ዘንድ ጥርስ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። የእከሊት እናት አባት፣እህት፣ ወንድም እየተባለ ስማቸው በእኩል ይነሳል። ይህ ክፉ አጋጣሚ ደግሞ እንደሚጠቀሰው የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ይወሰናል። ልጆቹ በዚህ አጋጣሚ ነውርነቱን ፣አሳፋሪነቱን በእኩል መጋራታቸው አይቀሬ ነው።

አንዳንዴ አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው ያልፈቱትን ችግር ከሚዲያው አምጥተው ‹‹ፍረዱኝ›› ሲሉ ይሰማል። በእኔ ግምት እንዲህ ማድረጋቸው ለሌሎች መጠቀሚያ ካልሆነ በቀር ስለነሱ ኢምንት ታህል ፋይዳ አይኖረውም።

በግልጽ የሚወጣውን ምስጢር በእኩል የሚጋሩ ተመልካቾች ደግሞ ሁሉም እኩል እሳቤ የላቸውም። አንዳንዶቹ የአንዱን ወገን ይዘው ሚዛን አልባ ሃሳብ ይሰጣሉ። ሌሎቹ ደግሞ ይባስ ብለው በስድብ ያጥረገርጋሉ። ከፊሎቹም ‹‹እናውቃለን›› በሚሉት ሌላ ምስጢር ተሳትፈው እሳት ለማቀጣጠል ይፈጥናሉ።

እንደ እኔ ዕምነት አብሮን የቆየው የሽምግልና ባህላችን በማህበራዊ ሚዲያው ሲሽሞነሞን አልኖረም። በጥንዶች መሀል ችግር ቢኖር በቤተዘመድ ጉባኤ መፍታቱ ተለምዷል። ‹‹አንተም ተይ ፣ አንተም ተው›› ይሉት ልማድ የጠበቀ ቋጠሮን ለመፍታት አቅም አያንሰውም።

እንዲህ አይነቱ የባልና ሚስት ችግር ሲፈታ የቆየው በፌስቡክ፣በቲክቶክና በዩቲዩብ ገጾች አልነበረም።እንዲህ በሆነ ጊዜ ‹‹በድያለሁ፣አልያም ተበድያለሁ›› የሚል አካል ዕምነት ሃይማኖቱ ጭምር ለመፍትሄው ይጠቀማል። በልጆቹ፣ በጎረቤቶቹ ይዳኛል። እንደዘንድሮ ፍርድ ውሳኔው የሚሰጠው በማህበራዊ ሚዲያ አይደለም። ‹‹ጉዳዬ ጉዳያችሁ›› ያሉ ወዳጆች፣ምስጢርን ድብቅ ፣ሽሽግ አድርገው መፍትሄውን ይሰጣሉ። ጠብን አርቀው ፍቅርን ያወርሳሉ።

አሁን ላይ ግን ይህ ሁሉ እውነታ ከስጋት እየወደቀ ነው። የቤተሰብ ምስጢር ፣ ገበና ይሉት የለም። ነውር ፣ ህጋዊ ሆኖ ካደባባይ ወጥቷል። የአንዱን ቤት ገበታ የሚቆርሰ ው፣የሚቦጠቡጠው የማህበራዊ ገጽ ዕድርተኛው እየሆነ ነው።

ይህ ክፉ ጅማሬ ሊቆም ይገባል።ስለነገ ህይወት፣ስለልጆች ሞራልና ማንነት ማሰብ መጠንቀቅ የግድ ነው። ‹‹የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ፣ ‹የሚያድግ ልጅ አይጥላህ፡›› ይሉት ተረት ያለነገር አልተባለምና ልቦና ይስጠን።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You