እያገረሸ የሚገኘው የወባ ወረርሽኝ ስጋት

የክረምቱ ወቅትን መገባደድ ተከትሎ የበጋ ወቅት ሲመጣ ሙቀት ስለሚኖር ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ በዚህ ወቅት የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ሥራ የሚሠራው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶችና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የወባ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ትልቅ ስጋት አለ። ከዚህ አንፃር ማኅበረሰቡ ራሱን በወባ በሽታ ምክንያት ሊከሰት ከሚችል ህመምና ሞት እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ፣ በተለይ የሚዲያ ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይታመናል። ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም እንደዚያው።

የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ጌትነት እንደሚናገሩት፣ በመጪው ጊዜ የወባ ወረርሽኝ ሊከሰትና ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋት አለ። ወባ በአመት ሁለት ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ይከሰታል ተብሎ ይታሰባል። አንደኛው የዝናብ ወቅት ከተገባደደ በኋላ መሆኑ ማኅበረሰቡ የወባ መቆጣጠሪያና መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ፣ ሁልጊዜና በትክክል መከተል ይኖርበታል። ምን አልባት ደግሞ የወባ በሽታ ምልክቶችን ካየ ባስቸኳይ ወደ ሕክምና ቦታ በመሄድ አስፈላጊውን ሙያዊ እርዳታ ማግኘት ይጠበቅበታል። ለዚህም በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል። ማኅበሩም እየሠራ ያለው ይህንኑ ነው።

ማኅበሩ በሃያ አምስት አመታት ጉዞው የወባ በሽታን በሚመለከት ለማኅበረሰቡ በከፍተኛ ደረጃ ግንዛቤ ሲያስጨብጥ ቆይቷል። በተለይ ደግሞ ወባ ገዳይ በሽታ እንደሆነና ትኩረትም እንዲያገኝ የጥብቅና ሥራ ሠርቷል። ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ደግሞ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ በማተኮር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በዋናነት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ሁኔታዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሠራል። ከሚሠራባቸው አጋላጭ ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ ትምባሆ፣ አልኮል፣ ጤናማ ያልሆኑ አመጋገቦችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን አለማድረግ ይገኙበታል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ባለፉት ሃያ አመታት የወባ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ነበር። ባለፈው አመት ግን ወረርሽኙ 50 በመቶ እንደጨመረ መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች ላይም መዘናጋት ተፈጥሯል። ይህም በጥናት መለየትና ተረጋግጦ መውጣት ይጠበቅበታል። ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትልም ማኅበረሰቡ የወባ መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ ይጠበቃል። ማኅበሩም ይህንን መልዕክት በተለያዩ መንገዶች እያስተላለፈ ይገኛል።

የወባ ወረርሽኝ በዚህ አመት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን መረጃዎች የሚያሳዩ በመሆናቸውና በቀጣይም ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ስጋት በመኖሩ የወረርሽኙን ስጋት ለመቀልበስ ማኅበረሰቡን በስፋት ማስተማር ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወባ ታክሞ የሚድን በሽታ ከመሆኑ አኳያ ቢቻል የወባ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል።

ለምሳሌ አጎበርን ሁልጊዜ በአግባቡ መጠቀም፣ በገጠር አካባቢዎች የወባ ትንኝ ማጥፊያ ኬሚካል ከተረጨ በኋላ በእበት ወይም በአመድ ግድግዳን አለመለቅለቅ፣ የወባ መራቢያ አካባቢዎችን ማዳረቅና የታቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስ ይገባል። በሽታውና ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሳይቻል ቀርቶ በበሽታው መያዝ ቢመጣ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም በማምራት አስፈላጊውን ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋል።

የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አበረ ምህረቴ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ ወባ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ከፍተኛ ተዛምዶ ያለው በሽታ ስለሆነ የአየር ንብረትና የወባ ባለሞያዎች ተገናኝተው መረጃ ቢቀያየሩና በጋራ ቢሠሩ ወረርሽኙን መተንበይ እንደሚያስችል በጥናት ለማረጋገጥ ተችሏል። ከሁለቱ ባለሞያዎች የተውጣጣ አንድ ግብረ ኃይልም ተቋቁሟል። ሁለቱ ባለሞያዎች በአንድ ላይ በመሥራታቸው ተሞክሯቸው ውጤታማ ነበር። በተለይ የአማራን ክልል ለአመታት በማጥናትና በተሞክሮነት በማየትና አመርቂ ውጤት ማግኘት በመቻሉ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲና የአማራ ጤና ቢሮ በጋራ ለመሥራት ሥራውን ተረክበዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የወባ ወረርሽኝ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ አንፃር ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በተቻላቸው አቅም ለኅብረተሰቡ የማስጠንቀቂያ ደወል ማሰማት ይኖርባቸዋል። በተለይ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች አደጋ ውስጥ ሊገቡ ስለሚችሉ ሁሉም በጋራ ሊረባረብና ኅብረተሰቡን የማዳን ሥራ ሊሠራ ይገባል። በተለይ ደግሞ የሚዲያ አካላት ከሌሎች በተለየ በሽታውን በሚመለከት ኅብረተሰቡ የቅድመ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ እንዲያከናውን የማስገንዘብ ኃላፊነት አለባቸው።

‹‹ማሌሪያ ኮንሰርቲየም›› በተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት የፀረ-ወባ ባለሞያ ሆነው የሚሠሩት ዶክተር አጎናፍር ተካልኝ እንደሚገልፁት፣ ወባ ድምፅ አልባ በሽታ ነው። በአብዛኛው እናቶችንና ሕፃናትን ያጠቃል። እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ በኢትዮጵያ በወባ በሽታ ምክንያት የሚመሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ነበር። ይሁንና ባለፈው አመት በርካታ ሰዎች በወባ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በወሊድ ምክንያት አንድም ሴት መሞት የለባትም ተብሎ ትግል እየተደረገ እንደመሆኑ መጠን በወባ በሽታም አንድም ሰው ሕይወቱን እንዳያጣ ጠንካራ ሥራ መሠራት አለበት። መከላከል እየተቻለና ሕክምና እያለ በወባ ምክንያት ለምን ሰው እንደሚሞትና በአሁኑ ጊዜ ለምን የወባ ስርጭት እየጨመረ እንደመጣ ማጥናት ያስፈልጋል። በርግጥ ለወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ መምጣት አንዱ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ የወባ ወረርሽኝ ከፍ ሊል ችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሕክምና አገልግሎት የተደራሽነት ችግር ተፈጥሯል። ይህም ማለት ግጭት በተፈጠረባቸው የሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደልብ ገብቶ መድኃኒቶችንና የወባ መከላከያዎችን መስጠት አልተቻለም። በሌላ በኩል ደግሞ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ግብአት እጥረት ይታያል። በተለይ የመድኃኒቶች፣ መመርመሪያ ኬሚካሎችና የባለሞያዎች እጥረት አለ። ይህም ለወባ ወረርሽኝ መስፋፋት የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል።

የወባ ትንኝና ተህዋሲያኑ መላምድም ሌላው ከወባ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ የሚነሳ ችግር ሲሆን፣ ከዚህ ችግር ጋር በመጋፈጥ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በገንዘብ እጥረት ምክንያት የወባ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚያችሉ በርካታ ግብአቶች በጊዜው ሊደርሱ አልቻሉም። በባለሞያዎችም ሆነ በሚመለከተው ክፍል ትኩረት የመስጠት ችግር አለ። ይህም አንዱና ዋነኛው ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ከግጭትና ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ደግሞ የሕዝቦች መፈናቀል አለ። ለተፈናቃዮች በወባ በሽታ እንዳይጠቁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ አይደለም። በዚሁ መነሻነት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን በቀጣይ ተፈናቃዮችን ትኩረት ያደረገ የወባ መከላከል ሥራ ለመሥራት ታቅዷል።

በእነዚህና መሰል ምክንያቶች በኢትዮጵያ የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ መጥቷል። በቀጣይም ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ስጋት አለ። ከዚህ አንፃር ስጋቱን ለመቀልበስ ከአንዱ በስተቀር ለሁሉም መፍትሔ ይኖራል። ይኸውም የአየር ንብረት ለውጥ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያመጣቸው ችግሮች ግን መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ይቻላል።

በይበልጥ ኅብረተሰቡ የተዘናጋ እንደመሆኑና በወቅቱ አጎበርን የመሳሰሉ የወባ በሽታ መከላከያዎችን የማይጠቀም በመሆኑ፤ እንዲሁም፣ የበሽታውን ምልክት ሲያዩ በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም ስለማይሄዱ የወባ በሽታ ስርጭት ከፍ እንዲል የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚህ አንፃር በተለይ መገናኛ ብዙኃን የወባ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በሚመለከት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ባለፈ የወባ በሽታ አጀንዳ እንዲሆንና ሁሉም ሰው ትኩረት እንዲሰጠው የጤና ልማትና ፀረ ወባ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መደገፍና ማበረታታት ከሁሉም ይጠበቃል።

ወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች በአፍሪካ አሳሳቢ እየሆኑ ስለመምጣታቸው በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ የአፍሪካ ወባና ትንኝ ቁጥጥር ማኅበር /PAMCA/ በአዲስ አበባ በተካሄደው ዘጠነኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ መነገሩ ይታወሳል። በዚሁ ጉባኤ ወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎችን በሚመለከት በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል። በተለይ አፍሪካ በርካታ ችግሮች ያሉባትና ከበሽታዎች ጋር በተያያዘም በርካታ ጫና እንዳረፈባት በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች አማካኝነት በጉባኤው ተነግሯል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ አለ የሚባለው የወባ በሽታ ከ90 በመቶ በላይ በዚሁ የአፍሪካ አህጉር መሆኑ ተገልጿል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖም ለወባ በሽታ ጫና ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተጠቁሟል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጉባኤው ኢትዮጵያ በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አማካኝነት ከዚህ ቀደም የወባ ስርጭትን ለመቀነስ ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንና እ.ኤ.አ በ2020 በሽታው ገዳይ እንዳይሆን መቆጣጠር መቻሉ ተጠቁሟል። ይሁንና ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ተከትሎ የወባ በሽታ እንደ አዲስ እያገረሸ መሆኑ ተነግሯል። ወባ ብቻ ሳይሆን ትንኝ ወለድና ሌሎች ወባ መሰል በሽታዎች እየተከሰቱ ስለመሆናቸው ተገልጿል። ለአብነትም ዴንጌ፣ ችጉንጉኛ (ቅልጥም ሰባሪ)፣ የሎ ፊቨር የተሰኙ የበሽታ ዓይነቶች በኢትዮጵያና በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት እንደገና እየታዩ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በዚህም የወባ ወረርሽኝ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ እየጨመረ ስለመምጣቱ ተጠቁሟል። ከዚህ ቀደም የሚታወቀው የወባ ትንኝ የነበር ቢሆንም አሁን ላይ ግን Anopheles stephensi የተሰኘች የወባ ትንኝ ዝርያ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እ.ኤ.አ በ2016 ስለመከሰቷ ተነግሯል። ይህች ትንኝ በተለየ ሁኔታ በሽታውን በከተሞች አካባቢ ማስፋፋቷ ደግሞ አደገኛነቷን እንደሚያሳይ ተመላክቷል። ይህንን ለመቆጣጠር ታዲያ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን በጉባኤው ተጠቅሶ፣ ነገር ግን ሥራው በቂ ባለመሆኑ አጠናክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ተደርሷል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You