ለባለውለታዎች የተበረከተው የአረጋውያን ማዕከል

በጉብዝና ወራቸው እውቀትና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ባላቸው ጊዜ ሁሉ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፣ ሀገራቸውን በሚገባ አገልግለዋል። የዛሬዎቹ አረጋውያን ትውልድን ቀርጸው፤ ሀገርን አቅንተዋል። ሀገር ለመውረር የመጣን ጠላት በብርቱ ክንዳቸው አሳፍረው መልሰዋል። ድልድይ ሆነው ይህችን ሀገር ለዛሬ አድርሰዋል። የከፈሉት መስዋዕትነት ጥቂት አይደለም። እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች በእድሜያቸው አመሻሽ ወድቀው እንዳይቀሩ በግለሰብም ይሁን በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል።

ባለፈው መስከረም 03 ቀን 2016 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ ለምርቃት የበቃው ‹‹የአረጋውያን መጦሪያ መጠለያና እንክብካቤ ማዕከል›› ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው ‹የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን› ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው 30ሺ ካሬ ሜትር ላይ በ634 ሚሊየን ብር ወጪ ማዕከሉን ገንብቷል። የተገነባው ማዕከልም ለሰባት መቶ ሰላሳ አረጋውያን እንክብካቤ የማድረግ አቅም አለው።

የከተማዋ ባለሀብቶች ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣትን ባህል እያደረጉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሰሚት አካባቢ የተገነባውን ማዕከል ምሳሌ አድርገው ተናግረዋል። ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕም በገባው ውል መሠረት ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል ገንብቷል።

ጧሪ ያጡ አረጋውያን በመጨረሻ ዕድሜያቸው የትም ወድቀው እንዳይቀሩ፤ ለምድራቸውም በረከታቸውን እንጂ እርግማናቸውን ትተው እንዳይሄዱ በሕይወት እስካሉ ድረስ እነርሱን የሚያስደስቱ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ያመላከቱት ከንቲባዋ፤ ማዕከሉን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። ማዕከሉ ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆንም የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እንደተማሉለት አስረድተዋል።

አረጋውያኑ በዚህ ዕድሜያቸው በማዕከሉ ቁጭ እንዳይሉ የእደ ጥበብ፣ የግብርናና የመሳሰሉት ግብአቶችን በማሟላት ዛሬም በስራ ምሳሌ እንዲሆኑ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ማዕከሉ የሕክምና እና የሥነ ልቦና አገልግሎት የሚሠጡ ክሊኒክ፣ መድሃኒት ቤት፣ ዘመናዊ ላውንደሪ፣ ምግብ ማብሰያና መመገቢያ እንዲሁም የመዝናኛ ስፍራዎችን ያየዘ ነው። ማዕከሉን በቋሚነት በገቢ እንዲደግፍ ከባለ ሶስት ወለል ህንፃ ኪራይ የሚገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ አጋዥ ይሆናል።

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ እንዲህ አይነቱን ሥራ ለመሥራት ልበ ቀና መሆንን ይጠይቃል። መንግሥት ብቻውን ሠርቶ የዜጎችን ጥያቄ መመለስ አይቻልም። የዜጎችን የሕይወት ጫናም ማቅለል አይቻልም። ስለዚህም የመንግስት አንዱ ሥራ እንደዚህ አይነት ሥራ ማበረታታት ነው። ባለሀብቶች ቢዝነስ ብቻ ሠርተው እንዲያተርፉ ሳይሆን ሠውን እንዲያተርፉ እና የሠውን ጫና እንዲያቀሉ ማድረግ ይገባል። ለዚህም መንግሥት ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል።

‹‹የከተማ አስተዳደራችን የትናንት ባለውለታ የሆኑት አረጋውያንን ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ አበክሮ እየሠራ ይገኛል። ማዕከሉ በአሁን ወቅት 80 አረጋውያንን ተቀብሎ ማስተናገድ የጀመረ ሲሆን፤ በዘላቂነትም ሌሎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም አለው።›› ያሉት ደግሞ የከተማዋ የስትራቴጂክ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር እሸትአየሁ ክንፉ ናቸው።

በከተማ ውስጥ እንዲህ ያለውን ሥራ መሥራት እና ማቅረብ ግብ ብቻ አይደለም፤ ለታለመለት አገልግሎት እንዲውል ማድረግ ይገባል። ያንን ለማድረግም አስተዳደራዊ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ እንደሆነም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል። እንዲህ ያለውን ያማረ እና ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል በከተማዋ መገንባት በመቻሉም ለፋውንዴሽኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት ዶክተር ሳሙኤል ታፈሰ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ለአረጋውያን ምቹ በሚሆን መልኩ ተገንብቷል። ድርጅቱ እያከናወነ ካለው ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነትን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎው ላቅ ያለ ነው። ለአብነት ያህልም በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ የገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት ይጠቀሳሉ። እንዲሁም እርሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተማሩበት የፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት የዲጂታል ላይብረሪ፣ ሚኒ ሚዲያና ክሊኒክ ገንብተው ማስረከባቸውን አስታውሰዋል። ከነዚህ በተጨማሪም አነስተኛ የገቢ ምንጫ ያላቸው ልጆች፤ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ላጡ፣ የትምህርት ዕድል ላላገኙ ታዳጊዎች እንዲሁም መማር እየፈለጉ ዕድሉን ማግኘት ላልቻሉ ዜጎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ በበጎ አድራጎት መንፈስ በኦሮሚያ ክልል ነቀምት፣ በትግራይ ክልል አክሱም እንዲሁም በደቡብ ክልል አገና ሥራ ከጀመረ 12 ዓመታትን ማሳለፉንም ያወሳሉ። በቅርቡም በአማራ ክልል በደብረ ብርሀን ከተማ በ54 ሚሊየን ብር ወጪ አራት መቶ ተማሪዎች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ለምርቃት እንደሚበቃ ጠቁመዋል።

ኩባንያው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የራሱን ገቢ አመንጭቶ እስከ ሰባት መቶ ሀምሳ አረጋውያንን ማስተዳደር የሚችል፤ በሀገራችን ደረጃ የመጀመሪያ እና ሞዴል ሊባል የሚችል ዘመናዊ የአረጋውያን ማዕከል ለአገልግሎት እንዲውል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ። አክለውም ድጋፍ ላደረጉላቸው ለወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ለሌሎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ማህበራዊ ፍትህ እንዲነግስ እና ሁሉም ነዋሪዎቿ ከልማቷ ትሩፋት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ለማስቻል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ዶክተር እሸትአየሁ ገልፀዋል። እንዲህ አይነት ማዕከል በብዛት መገንባት እንደሚኖርባቸውም ያብራራሉ። ከተማችን አዲስ አበባ 5ነጥብ2 በመቶ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን ይገኛሉ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም በርካታ አረጋውያንን መንከባከብ እና መጦር እንደሚገባ አሃዞች አመላካቾች መሆናቸውን በመጠቆም፤ በከተማዋ የሚገኙ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በእንዲህ አይነቱ ማህበራዊ ኃላፊነትን በሚጠይቅ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እዲቀላቀሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You