በዩኔስኮ የሚመዘገቡ ቅርሶች መበራከት ለሀገራዊ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው!

 ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ነች፡፡ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ደርጅት (ዩኒስኮ)ይህንኑ ድንቅ ሃብቶቿን በመገንዘብ ቀደም ሲል 11 ቅርሶችን መዝግቦላት የነበረ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ቅርሶችን በማከል በአፍሪካ 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ከአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1978 ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ደርጅት (ዩኒስኮ) የኢትዮጵያን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ሲመዘግብ የቆየ ሲሆን በዋነኝነትም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፤.የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፤ የፋሲል ግቢና ሌሎች የጎንደር ሐውልቶች፤ አክሱም፤ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፤ የጢያ ትክል ድንጋይ፤ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የአርኪኦሎጂ ስፍራ፤ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፤ ኮንሶ፤ መስቀል፤ ፍቼ ጫምባላላ፤ የገዳ ሥርዓት፤ ጥምቀት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ አሥራ ሁለት የሥነ ጽዑፍ ሀብቶችን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች፡፡

ቅርሶቹ ከአክሱም ሐውልቶች እስከ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውበታል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያበቋት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 11 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር የነበረች ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክንና የጌዲዮ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መልክዓ ምድር፣ በማስመዘግብ በዩኒስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦችን ቁጥር 13 ማድረስ ችላለች፡፡

ሌሎች በምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ ቅርሶችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የድሬ ሼክ ሁሴን መስጊድ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የመልካ ቁንጡሬ የአርኪዮሎጂ ሥፍራ፣ ከባህላዊ ቅርሶች ደግሞ የትግራይና የአማራ (ሰቆጣ) የአሸንዳ/አሸንዲዬ በዓላት ይገኙበታል፡፡

የእነዚህ ቅርሶች መመዝገብም ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ በቂ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ከማስቻሉም በላይ የሀገሪቱን ገጽታ ከስር ከመሰረቱ የሚለውጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድታመራ ከሚያደርጓትና በመንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ሲሆን በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሀገር በሚል እሳቤ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ መዲናችን አዲስ አበባን ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተከውነዋል፡፡

በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድነት፤ የወዳጅነት እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል፡፡ ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች፡፡ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤ የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡

እስካሁንም በተሰሩት ሥራዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከመላው ዓለም በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሀገር ጎብኝዎች የሚመጡ ሲሆን ከጎብኝዎችም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ገቢ ሀገሪቱ እያገኘች ነው፡፡ ይህም ገቢ ከሀገር ውስጥ ምርት ምጣኔ (GDP) 5 በመቶውን በመሸፈን የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት እየደገፈ ይገኛል፡፡ ለበርካታ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ ዕምቅ የሆነ የቱሪዝም አቅም ቢኖራትም በጦርነት፤ በግጭትና በአለመረጋጋት የተነሳ ያላትን ሀብት እንዳትጠቀም እንቅፋት ሆኖባታል፡፡ ለአብነትም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች እና መዳረሻዎች ቀዳሚ የኾነችው አክሱም፣ በየዓመቱ ከ25 ሺህ በላይ በሚደርሱ የውጭ አገር እንግዶች፣ ታሪካዊ ቅርሶቿ ይጎበኙ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም ቢኖራትም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ግን በሚገባ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። አሁን በለውጡ ዘመን በተሰሩ ትላልቅ ሥራዎች ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየበት ሲሆን ከሰሞኑ የተመዘገቡ ቅርሶችም ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ላላት ተስፋ ብሩህና ትልቅ አቅም የሚሆን ነው!

አዲስ ዘመን  መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You