አዲስ ዘመን ድሮ

ኢትዮጵያ ከሰማንያ ዓመታት በፊት ምን አበይት ጉዳዮችን አስተናገደች፣ ምንስ ጉዳይ በዋና ዋና መገናኛ ብዙሃኖች የዜና ሽፋን አገኙ የሚለውን ጉዳይ ከአንጋፋው ጋዜጣ የበለጠ ሊነግረን የሚችል አይኖርም፡፡ በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን ከሰማንያ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ መለስ ብለን በ1930ዎቹ የነበሩ ክስተቶችን እናስታውስ፡፡

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 3ኛው ዓመት ስለመጀመሩ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲቁአቁም የግርማዊነታቸው ፈቃድ ሁኖ ሥራው ከተጀመረ ሁለተኛው ዓመት አልፎ እነሆ ሦስተኛው ዓመት መጀመሩ ነው፡፡

ይህም ሦስተኛው ዓመት በሚጀምርበት ጊዜ፤ የሥራ ዕድሜው በሆኑት በዓለፉት በሁለቱ ዓመቶች ውስጥ፤ ከአዕምሮአቸው በመነጨው መልካም መልካም የምክር ቃል ባለበት ጽሕፈታቸው የረዱትንና በትጋት እየተከታተሉ የተመለከቱ አንባቢዎቹን በተለይ እያመሰገነ ለወደፊቱም እንደዚሁ እርዳታቸውን እንደማያጎድሉበት ይተማመናል፡፡

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30 ቀን 1935 ዓ.ም)

በታላቁ ቤተ መንግሥት የይሁዳ አንበሳ የተባለው ፊልም ስለመታየቱ

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊት እቴጌ ፊልሙ ከሚታይበት ክፍል ገብተው በዙፋናቸው ከተቀመጡ በኋላ ሲኒማው ተጀመረና ብዙ የጦር ፊልም አስደናቂ በሆነ አኩኃን ታየ፡፡ የአየርና የባሕር፣ የምድር ጦርነት ሲደረግ ለሕዝቡ አማን በአማን ከዚያው ከጦርነቱ ውስጥ ያለ ሁኖ ይታየው ነበር፡፡

የዚህም አይነት ፊልም በሰፊው ከታየ በኋላ የግርማዊ ንጉሠ ነገሥትን የድል አድራጊነት ወደ አዲስ አበባ መግባት የሚያሳየው የይሁዳ አንበሳ የተባለው ፊልም መታየት ተጀመረ፡፡

……..

እንዲሁም ድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳ፤ ጎምለል ጎምለል እያለ ሲታይ ተመልካቹ ደስታውን በጭብጨባ ሲገልጽ ቆየና በመጨረሻው የልዩ መጠጥና የቡና ግብዣ ተደርጎ ሲኒማው ተፈጸመ፡፡

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30 ቀን 1935 ዓ.ም)

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ከሎንዶን ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ

ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም፤ ግርማዊት እቴጌ በመጡ ጊዜ፤ ልዩ የክብር ጉዞ ተደርጎለት 1933 ዓ.ም ነሐሴ 23 ቀን መጥቶ በግርማዊነታቸው ሥዕል ቤት በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ቆይቶ ነበርና፤ ግርማዊነታቸው አንድ የተለየ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰራለት ስለአሰቡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል አጥር ግቢ አንድ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋጀ፡፡

…….

ከዚሁ በኋላ ይኸው ግርማዊነታቸው በድል አድራጊነት የገቡበት ቀን የመድኃኔ ዓለም ዕለተ በዓል ስለሆነ፤ የበዓሉ መጀመሪያ በዚሁ እንዲሆን በፕሮግራም ተወሰነ፡፡

…….

ከዚህ በኋላ ስለመንፈሳዊ ግብረ ተልእኮ በጣም የሚፋጠኑት አባ ሐና፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በስደት ሳሉ ስለሀገራቸው ያደረጉትን መልካም አድራጎትና ከእግዚአብሄርም የተደረገላቸውን ብዙ ቸርነት በዚያም ያሉ ምእመናን ስለሀገራቸው ፍቅር ይዘምሩት የነበረውን መዝሙር በሚያሳዝንና ልብ በሚነካ ቃል ሲናገሩ፤ እግዚአብሄር ለኢትዮጵያ ያደረገላት ተአምር ጠልቆ ይሰማ ነበር፡፡

ከመዝሙሩም በኅብረት የተዘመረውንና በጣም ልብ የሚነካውን ቃል ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ በታች አትመነዋል።

የሀገር ፍቅር መዝሙር

ኢትዮጵያ ሆይ! አገራችን፤

ረስቼሽ እንደሆን ቀኜ ትርሳኝ፡፡

አላሰብሁሽ እንደሆን መላሴ በትናጋዬ ይጣበቅ፡፡

ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢትዮጵያ ሆይ፤

ከፍ ከፍ አላደረግሁሽ እንደሆን፡፡

አቤቱ ፈጣሪያችን

በኢትዮጵያ ቀን የጠላትዋን ልጆች አስብ፡፡

አፍርሱአት አፍርሱአት፤

እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱአት ያሉዋትን፡፡

አንቺ የተፈታሽ የጠላታችን ልጅ፤

ያደረግሽብንን ብድራት የሚመልስልሽ፤

ፈጣሪያችን የተመሰገነ ነው፡፡

ልጆችሽንም ይዞ በድንጋይ የሚደቁሳቸው፤

አምላካችን ምስጉን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሆይ! ሀገራችን፤

ረስቼሽ እንደሆን ቀኜ ትርሳኝ፡፡

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30 ቀን 1935 ዓ.ም)

በሸመታ ምክንያት ስለተነሣው ችግር

ቀለብተኛው ወታደር በሺሊንግ እህል ልሸምት ሲል ባላገሩ ብር እንጂ ሺሊንግ አልቀበልህም በማለት በአዲስ አበባ፣ በሰንዳፋ፣ በደብረ ብርሃንና በደብረ ሲና፣ በደሴ፣ በጎጃም፣ በትግሬ፣ በሐረርና በጂማ፣ በቢሾፍቱና ባዳማ፣ በአምቦና በጌዶ፤ በሌላውም አገር በገበያም ሆነ በየመንገዱ እህሉን ከባላገሩ ላይ ስለወሰዱበት በባላገርና በወታደር መካከል የተነሣውን ታላቅ ችግርና በዚህም ምክንያት ባላገሩ እህሉን ለሸመታ አላወጣም ማለቱን ማንም አላስተወም፡፡

ደሀና ገበያ ሳይገናኙ ይኖራሉ

ደሀና ገበያ ሳይገናኙ ይኖራሉ ማለት፤ ዕቃው ሸቀጡና ጨርቁ በረከሰ ጊዜ ገንዘቡ የማይገኝ ይሆናል፡፡ ገንዘቡም በተገኘ ጊዜ ዕቃውና ሸቀጡ ይወደዳል፤ ስለዚህ ደሀና ገበያ ሳይገናኙ ይኖራሉ ይባላል፡፡

የሥራና የሠራተኞች ክርክር

ሠራተኞች ነን የሚሉ ሁሉ ሥራ አጣን እያሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ፤ ሥራ ደግሞ ሠራተኞችን አላገኘሁም እያለች በበኩልዋ ታማርራለች፡፡ የሁኖ ሆኖ ሥራ አልተሰራሁም ትል እንደሆን እንጂ መኖራቸው እርግጥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንግዲህ ለማን ወይም በማን ይፈርደዋል? በሥራ ነውን ወይስ በሠራተኞች?

ፖሊስ ጣቢያ

ግንቦት 14 ቀን ከጠዋት 2 ሰዓት ተ20 ደቂቃ ሲሆን ሰፈሩ ቄራ ሰፈር የሆነ ገብረ ጻድቅ ተስፋዬ የሚባል ሰው ያንድ እግር ጫማ፣ 2 የቆዳ ገንባሌ ይዞ ሲሔድ በእቴጌ መነን መንገድ ተገኝቶ በጥርጣሬ ኪዳኔ ይማም በሚባል ፖሊስ ተይዞ መጥቶ ዋቢውን እስኪያቀርብ ታስሮአል፡፡

ግንቦት 14 ቀን ከቀኑ 4 ሰዓት ሲሆን የሰሜን ምሽግ ገፈርሣ የሚጠብቁት የጦር ሚኒስቴር ወታደሮች ኃይለ ማሪያም ዘለቀና ማሞ ወልደ ጻድቅ የሚባሉት ሌቦች ሌሊት ሁለት ሁነው 7 ሰዓት ላይ የምሽጉን ቆርቆሮ ሰርቀው ሲሔዱ ሮምታ ብንተኩስ ተሁለቱ አንዱን ሌባ ገደልነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 1936 ዓ.ም)

የአፍሪካ ጦርነት ፍጻሜ

ከዓለማት ባንዱ ክፍል ዓለም በአፍሪካ ተስፋፍቶ የነበረው ጦርነት፤ ዛሬ በመፈጸሙ በጣም ደስ አሰኝቶአል። ይህ የድል እርምጃ አስቀድሞ በኢትዮጵያ በመልካም ሁኖ ስለተመሠረተ ዛሬ በመላው አፍሪካ ተስፋፋ፡፡

ከሁለት ዛፍ ያረፈች ወፍ ሁለት ክንፍዋን እንደምትነደፍ ወዲህ በአፍሪካ፤ ወዲያ በአውሮፓ እስፋፋለሁ ያለው የአክሲስ ጦር በታላቅ ኃይል ተሰባበረ፡፡

(አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 1935 ዓ.ም)

ዛሬ የት እንጫወት?፤

ፍልውሀ ሒደን፣ ምሳ በልተን፣ በነፋሻ ስፍራ ተቀምጠን ብንጫወት በጣም መልካም ነው፡፡

(አዲስ ዘመን መስከረም 7 ቀን 1936 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You