አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ሠላምና አንድነት ለማስጠበቅ ብሎም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ህገመንግስቱን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ላይ የሚመክር መድረክ ትናንት በጁፒተር ሆቴል ተካሂዷል። በመድረኩ ለዓመታት በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነት የቆዩት አቶ ልደቱ አያሌው እንደተናገሩት፤ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት እየተጓዘችበት ያለው መንገድ ወደፊት ችግሮችን የሚደቅን በመሆኑ ማስተካከል ይገባል። በተለይም ደግሞ አገሪቱ እየተመራችበት ያለው የፌዴራሊዝም አሰራር በርካታ ጥያቄዎች ባለመመለሱ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል።
ህገመንግስቱን በሚገባ ለመተርጎም በተጨማሪም አሁን ያለው ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና እና የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መንገድ መቃኘት እንዳለበትም አቶ ልደቱ ጠቁመዋል። በአገሪቱ ያሉ ፖለቲካዊ አደረጃጀቶችና ተቋማዊ አሰራሮችን መፈተሽ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ አስተዳደር ትምህርት ኮሌጅ የሰብዓዊ መብት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ክልሎች ያላቸው አወቃቀርና አሰራር ፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የተጣጣመ እንዳልሆነና መርህ እየተጣሰ መሆኑን አብራርተዋል። ክልሎች በተለየ ሁኔታ እየገነቡት ያለው የፀጥታ መዋቅርም ከፌዴራሊዝም አሰራር ጋር የሚጋጭ እንደሆነ አስረድተዋል።
አንዳንድ ክልሎች በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች ብሄሮች እውቅና የሚሰጥ ሲሆን፤ በሌሎች ክልሎች ደግሞ አግላይ አሰራር መከተላቸው በአገሪቱ መረጋጋትና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዳይኖር ማድረጉን ጠቁመዋል። በመሆኑም ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ብሎም ክልላዊ አወቃቀሮች በአዲስ መልክ መቃኘት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ካልተደረገ አገሪቱ በቀጣይ ወደ መጥፎ አቅጣጫ ልታመራ እንደምትችል ተናግረዋል። በተለይም በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠው አንቀፅ 39 በሌሎች ዓለማት ካለው አሰራር ሆነ ትርጓሜ ብሎም አተገባበር አኳያ በእጅጉ የሚፃረር መሆኑን አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል ዩጎዝላቪያ እና ሶቭየት ህብረት መሰል አሰራሮችን በመከተላቸው ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን፣ ግዛቶቻቸው ለመፈረካከስ ብሎም እድገታቸው እንዲገታና ለበርካታ ውስብስብ ችግሮች እንዲጋለጡ ማድረጉን አመልክተዋል። በመሆኑም ምሁራንንና መንግስት በጉዳዩ ላይ በአንክሮ መምከር እንዳለባቸው ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር