አዲስ አበባ፡- ለአምስተኛ ጊዜ እየተካሄዳ ካለው የሕክምና መሳሪያዎችና አገልግሎቶች ዓውደ ርዕይና ጉባዔ በአሁኑ ወቅት በጤና ዘርፍ የተጋረጡ ፈተናዎች መፍታት የሚያስችሉ ቁልፍ የመፍትሄ ሃሳቦች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ።
በምግብ መድኃኒትና፣ ጤና ጥበቃ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና ፕራና ኤቨንትስ ትብብር የሚያካሂደው አውደ ርዕይ ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ የተጀመረ ሲሆን፣ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆይበት ጊዜ 16 የህክምና ባለሙያዎች ማህበራት በአጋርነት መሳተፋቸው ታውቋል።
የፕራና ኤቨንትስ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ለማ በሕክምና መገልገያዎችና መድኃኒት እንዲሁም የጤና አጠባበቅና ክብካቤ ዙሪያ የሚካሄደው አውደ ርዕይና ጉባዔ በጤና ዘርፉ ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን ማስወገድ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል። እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣትና የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲቀርቡ በማድረግ ለዘርፉ ልማት የላቀ አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት ጉባዔዎች የሕክምና ሙያ ዘርፎች ተከታታይ የሙያ
ማጎልበቻ መድረክ በመሆን ማገልገሉን አቶ ነብዩ አስታውሰው፤ ዘንድሮም የሕክምና ልህቀት፣ የታካሚ ደህንነት፣ የጨረርና ላቦራቶሪ ምርመራዎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤና መድኃኒት ላይ ተከታታይ ትምህርት የሚሰጥበት መሆኑን አስገንዝበዋል። በተጨማሪም የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ውይይት በማድረግ ለህግ አውጪዎች ግብዓት የሚገኝበት መድረክ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም በዓውደ ርዕዩ በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የምርምር እንዲሁም የትምህርት ተቋማት በአንድ ላይ በመሰብሰብ ምርትና አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር የወደፊት አቅጣጫዎችን የሚያዩበትን መድረክ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አቶ ነብዩ ጠቁመዋል።
በዚሁ ጉባዔ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሳተፉት 16 የሕክምና ሙያ ማህበራት መካከል ጥቂቶቹ የራሳቸውን ዓመታዊ መርሐግብሮች ከጉባዔው ጎን ለጎን እንደሚያካሂዱ የገለፁት አቶ ነብዩ፣ የዓለም ነርሶች ሳምንት የመጨረሻ ቀን ፕሮግራም በአውደ ርዕዩ የመዝጊያ ቀን በሚሌኒየም አዳራሽ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በጉባዔውና አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ፣ ባንግላዴሽ፣ ቻይና፣ሕንድ፣ ታይላንድ፣ቱርክና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች መሰረታቸውን ያደረጉ ኩባንያዎች ከ4ሺ በላይ ከሚሆኑ የአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች ጋር በጋራ ለመስራት አስበው የንግድ ትርኢቱን መከፈት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ቦጋለ አበበ