አዲስ አበባ፡- ባጋጠመው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንደምትቀንስ የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከግንቦት 1ቀን 2011ዓ.ም የተጀመረው የፈረቃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011ዓ.ም እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ትናንት በአገሪቱ እያጋጠመ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ በአገሪቱ የ476 ሜጋ ዋት የሀይል እጥረት መከሰቱን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን ታቀርበው የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጥ መሆኑንና ለጅቡቲ ትልክ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን እንደምትቀንስ ጠቁመዋል። ከሁለቱ አገራት ከሀይል ሽያጭ በዓመት 82 ሚሊዮን ዶላር ይገኝ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
በዚህ ዓመት የውሀ ፍሰት መጠንና በግድቦች የተያዘ የውሀ መጠን ማነስ በመታየቱ ችግሩን ለመቅረፍ የሀይል አቅርቦትን ከግንቦት 1ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ በፈረቃ ማዳረስ መጀመሩንና ይህም እስከ ሰኔ 30ቀን2011 ዓ.ም እንደሚቆይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በተከሰተው እጥረት ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱ በሶስት ፈረቃ የሚሰጥ ሲሆን፤ የሀይል ሥርጭት ክፍፍሉም ከማለዳ 11 ሰአት እስከ ረፋዱ 5 ሰአት፣
ከረፋዱ 5 ሰአት እስከ ቀኑ 10 ሰአት፣ ከቀኑ 10 ሰአት እስከ ምሽቱ 4 ሰአት ድረስ ይሆናል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የተከሰተው የሀይል መቆራረጥ ያጋጠመው ግድቦች በቂ ውሀ ባለመያዛቸውና ሀይል ለማመንጨት ከወትሮው ያነሰ መጠን በማስተናገዳቸው ሲሆን፤ በአገሪቷ በተከሰተ የአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡና የዝናቡ ወቅት ሲያልቅ ከሀይል ስርጭቱ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ጊቤ 3 እና መልካ ዋከና የሀይል ማመንጫዎች በቂ ውሀ አለመያዛቸውም የችግሩ መንስኤ ናቸው።
በሀይል መቆራረጡ ምክንያት የሲሚንቶና የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ሀይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች የሀይል አቅርቦት በግማሽ እንደሚቀነስባቸው፤ የምግብ ማቀነባበሪያዎች፣ መድሀኒት ፋብሪካዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ግን ሀይል እንዳይቋረጥ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
አዲሱ ገረመው