አዲስ አበባ፡- ከፍተኛ የድምጽ ብክለት ታይቶባቸዋል በተባሉ 305 የማምረቻ ተቋማት ላይ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ቁጥጥር በማድረግ ለ251 ያህሉ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው፤ በ104 ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የድምጽ ብክለት ባለሙያ አቶ እንዳሻው ግርማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ የድምጽ ብክለቶች እየተስተዋሉ መጥተዋል። ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ ለመስጠት በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የድምጽ ብክለት ቁጥጥር በመካሄድ ላይ ነው።
ኮሚሽኑ ቁጥጥር ባደረገባቸው የኦሮሚያ፣ የትግራይና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 607 የድምጽ ብክለት ያለባቸው አካባቢዎች ተለይተዋል። በዚህም መሰረት በመቐለ 120 ጭፈራ ቤቶች፣ በአዳማ ቢሾፍቱና ዱከም ከተሞችም እንዲሁ 110 ተመሳሳይ ቦታዎችን በመለየት 50 በሚሆኑት ላይ እርምጃዎች ተወስዷል። በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ክልል በተደረገው ቁጥጥር 102 ያህል ቦታዎች በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የድምጽ ብክለት እያደረሱ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ከ305 በላይ የማምረቻ ተቋማት፣ ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው መሆኑን እንደተረጋገጠ አቶ እንዳሻው አስረድተዋል። ከነዚህ ተቋማት መካከል 251 ያህሉ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው በ54ቱ ላይ ደግሞ የማሸግና
የገንዘብ ቅጣት በመጣል አስተዳደራዊ እርምጃዎች የተወሰደባቸውም መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሚባል የድምጽ ብክለት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የቦሌ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዝ ሲሆን የአራዳና የቂርቆስ ክፍለ ከተሞችም ተመሳሳይ ክስተት እንደታየባቸው ባለሙያው ይናገራሉ።የቁጥጥር ሂደቱ የሚከናወነው በቀንና በምሽት በተቀመጠው የድምጽ ምጣኔ መስፈርት መሆኑን የሚገልጹት አቶ እንዳሻው ተቋማቱ ግን ከመስፈርቱ አቅም በላይ ሆነው መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ችግሩ በተስተዋለባቸው ቦታዎች ላይ አስቀድሞ የምክርና የግንዛቤ ሥራ የተከናወነ ሲሆን የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት በድርጊታቸው በገፉ ተቋማት ላይ ኮሚሽኑ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ባለሙያው ተናግረዋል። እርምጃዎችን ለመውሰድ ከፖሊስና ከደንብ አስከባሪዎች
ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ እንዳሻው፤ ይህ መሆኑም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ማስቻሉን ገልጸዋል።
የድምጽ ብክለቱን ቁጥጥሩ ለማካሄድ በቅርብ ጊዜ በግዢ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ዘመናዊ መሳሪያ ስለመኖሩ የገለጹት ባለሙያው፤ ይህም በአጭር ጊዜና በተቀላጠፈ ሂደት ምዘናውን ለማካሄድ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። መሳሪያው ተቋሙ በዋነኛነት ለሚያተኩርባቸው የድምጽ፣ የአየር፣ የውሃና የአፈር ብክለቶች ቁጥጥር አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም አመልክተው፤ ወደፊትም ችግሩን በመለየት ተገቢ እርምጃዎችን ለመውሰድ አመቺ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ብክለት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥቆማዎችን በመስጠት በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ባለሙያው መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
መልካምስራ አፈወርቅ