ማንጎን የመታደግ ሥራ – በምርምር ግብረ ኃይሉ

 የማንጎ ተከል በዓለም በበረሃና በበረሃ ቀመስ አካባቢዎች የሚበቅል ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የገቢ ምንጭ በመሆን ያገልግላል። አሴት ተጨምሮበትም ይሁን ሳይጨመርበት ለውጭ ገበያ እየቀረበ ለሀገሮች የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል። ለሰው ልጅ የተሟላ ጤንነት የሚያስፈልጉ እንደ ቫይታሚን፣ ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲን ያሉ ነጥረ ነገሮችን በውስጡ በመያዙም በእጅጉ ይፈለጋል።

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ከሚመረቱ የፍራፍሬ ተክሎች ውስጥ ማንጎ ከሙዝ ቀጥሎ በሁለተኝነት ደረጃ ይመደባል። ከሀገሪቱ መልክዓምድር ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በዚሁ ተክል የተሸፈነ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሚበቅል ሲሆን፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና/የአሶሳ ማንጎ በሀገሪቱ በስፋት ይታወቃል/ ኦሮሚያ ክልሎች አብዛኛዎቹ ስፍራዎች ይገኛል። ቀድሞ የደቡብ ክልል ይባል በነበረውም በብዛት ይለማል።

ለአርሶ አደሩ በምግብነትና በገቢ ምንጭነት ይጠቅማል፤ ለተቀረው ሕዝብ በእጅጉ ከሚፈለጉ የፍራፍሬ ምርቶች አንዱ ነው። ወደ ውጭ ከሚላኩ ፍራፍሬዎች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። በዚህም የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ የማንጎ ምርቱ ብቻ ሳይሆን ዛፉም ይጠቅማል፤ ተክሉ በአብዛኛው በበረሃ አካባቢ ስለሚበቅል ሰዎች ሙቀትን ለመከላከል፣ ጥላ ስር ሆነው ስብሰባዎችን ለማድረግ፣ እርቅ ለመፈጸም እና ለመሳሰሉት የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ይሰባሰቡበታል።

በሀገራችን ይህ ሁሉ ፋይዳ ያለው ተከል አሁን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ አንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ችግሩ ተክሉ የተጠቀሱትን ጥቅሞች እንዳይሰጥ የሚያደርግበት ሁኔታ መፈጠሩንም ይጠቁማሉ። ይህ የሆነው ደግሞ በተለይ በሀገራችን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተው ነጭ የማንጎ ተባይ ምክንያት ነው። ተባዩ የማንጎ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀነስ አድርጓል፤ አርሶ አደሩንም ለተለያዩ ችግሮች እየዳረገው መሆኑም እየተጠቆመ ነው።

መንግሥትም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት የምርምር ግብረኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በኢንስቲትዩቱ የእፅዋት ጤና ባዮ ቴክኖሎጂ የቡድን መሪ እና የምርምር ግብረኃይሉ ተሳታፊ ዶክተር ዘላለም ግዛቸው እንደሚሉት፤ የማንጎ ችግር በአብዮት መልክ ካልተሠራ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም። ምክንያቱም በማንጎ ላይ የተከሰተው ችግር ሀገርን የውጭ ምንዛሪ እያሳጣ ነው፤ አርሶአደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዳያረጋግጥና ገቢ እንዳያገኝ እያደረገው ነው።

ለመሆኑ ነጭ የማንጎ ተባይ (white mango scale) ምንድነው? ተባዩ ከጠንካራ ነፍሳት (hard insect) የሚመደብ ሲሆን፤ የሚኖርበትን እና የሚመገብበትን ቦታ የሰም መከላከያ ሽፋን በማንጎ ቅጠል ላይ በመሥራት የሚታወቅ ነፍሳት ነው። ይህ ተባይ እንደመደበቂያ የሚገለገልበትን ሰም መሳይ የሚያጣብቅ ነገር በማመነጨት በውስጥ እየኖረ ተክሉን ይመገባል። በዚህም ቅጠሉ በብርሃን አማካኝነት ተክሎች ምግባቸውን የሚያዘጋጁበት ሂደት ፎቶሴንቴሲስ (photosynthesis) ስለማያካሂድ ወደ ቢጫነት ይቀየርና በቀላሉ ጠውልጎ እንዲሞት ያደርጋል።

ይህ ተባይ በበሰለ የማንጎ ፍሬ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ይከሰታል፤ በፍሬው ላይ ጎልቶ የሚታይ ሮዝ ቀለም የመሰሉ ጠባሳዎችን (እክሎችን) በፍሬው ላይ በመፍጠር ማንጎ ከገበያ እንዲወጣ አድርጓል። በነጭ የማንጎ ተባይ የተበላው ማንጎ በሰው ጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ይኑርም አይኑርም በጥናት ባይረጋገጥም፣ ማንጎው ስለሚበሳሳ እንደፈንገስ፣ ባክቴሪያና ቫይረስ በመሳሰሉ ተዋስያን በቀላሉ ይጠቃል። ከዚህ በተጨማሪ ለእይታ ስለሚያስጠላ የማንጎ ተመጋቢው ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ማንጎው በመበሳሳቱ ምክንያት አንዳንድ ማንጎ አብቃይ አርሶአደሮች የማንጎ ዛፋቸውን መቁረጥ ጀምረዋል። ይህ ተባይ በአሁኑ ሰዓት በሁሉም ማንጎ በሚበቅልባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ተሰራጭቶ ይገኛል።

ይህ ችግር በተለይ አርሶ አደሩን በተለያየ መልኩ እየጎዳው ይገኛል ያሉት ዶክተር ዘላለም፣ አንደኛው አርሶ አደሩ ማንጎን ዋና የምግብ ምንጭ አድርጎት ቢቆይም በተክሉ ላይ የተፈጠሩ ችግሮች ከተክሉ የሚገባውን ምርት ማግኘት እንዳይችል አድርገውታል ይላሉ።

ዶክተር ዘላለም እንደሚሉት፤ የመጀመሪያው ግብረኃይሉ እንዲቋቋም ዋነኛ ምክንያት የሆነው ነጭ የማንጎ ተባይን መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ነው። ለዚህም ችግሩን ከመሠረቱ እልባት ለመስጠት ነጭ የማንጎ ተባይን ሊከላከሉ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል። አንዱ ደግሞ የተመዘገቡ ኬሚካሎችን ለእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በዚህም በግብረኃይሉ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ሥራ ማከናወን ተችሏል። እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ሦስት ሳይቶች ተመርጠውም ነበር፤ በዚህም በአሶሳና አርባምንጭ ሳይቶች ላይ ብቻ ተሠርቷል። ሦስተኛው ሳይት ማለትም አርጆ ወለጋ በጸጥታ ችግር ምክንያት የዚህ ሥራ አካል መሆን አልቻለም።

ሁለተኛው ሥራና ተልዕኮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማመንጨት ነው፤ እኛ ሀገር ላይ ያልተመዘገቡና ሌሎች ሀገራት ላይ ተመዝግበው ወደተግባር በመግባታቸው ውጤታማ የሆኑ ኬሚካሎችን በመለየት (ቫሊዴት) በግብረኃይሉ ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል።

ሦስተኛው ነጭ የማንጎ ተባይን ብቻ መመገብ የሚችሉ ነፍሳትን (ፕሪዴተርስን) በመለየትና አራብቶ በመልቀቅ ሀገራት እንዴት ጤናማ ማንጎ መፍጠር እንደቻሉ በማየትና በመመርመር ያ የተፈጥሮ ጠላት (Predators) ሌላ ጉዳት እንደማያስከትል ተረጋግጦ ሌሎች ሀገራት በስፋት እንደተጠቀሙት ሁሉ በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወን ነው ሌላው ተግባር። በዚህም እንደ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት የማንጎ ምርታቸውን በተሻለ መንገድ የጠበቁበት ቴክኖሎጂ መሆኑ መሆኑ ታውቋል፤ ልምድ የመቅሰም ሥራም ተሠርቷል። በዚህ ላይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለመሥራት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ዶክተር ዘላለም ተናግረዋል።

የእነዚህን ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ነጭ የማንጎ ተባይን የሚመገቡ ነፍሳትን ለማላመድና ለመልቀቅ የሚያስችሉ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆናቸውን የሚገልጹት ዶክተር ዘላለም፤ በቀጣይ ዓመት እነዚህን ነፍሳት እኛ ሀገር አስገብቶ በማባዛት ወደ ማንጎ ዛፎች የሚለቀቅበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።

ይህ ከመሆኑ በፊት በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ ዶክተር ዘላለም። ይህን ለማድረግ አንዱ ቤተ ሙከራዎችን ማዘጋጀትን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ለዚህ ተግባር ምቹ ናቸው የተባሉ የባዮ ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ቤተሙከራዎች ተመርጠው ኃላፊነትን መውሰዳቸውን ዶክተር ዘላለም አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር ዘላለም የማንጎ ተክልን ሌሎች ችግሮችም እንደፈተኑት ይጠቁማሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የሀገር ውስጥ የማንጎ ዝርያዎች አሁናዊ ሁኔታ በተለያየ ችግር ውስጥ የወደቀ ነው። ከጅምሩም ቢሆን ማንጎ በርካታ ችግሮች አሉበት። አሁን ነገሮችን እያባባሳቸው የመጣው ለተክሉ ልዩ ትኩረት አለመሰጠቱ ላይ ነው፤ ተክሉ በብዙ መልኩ የምርት መቀነስ እያጋጠመው ይገኛል። አንዱ በአስተዳደር ዙሪያ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። ተክሉ ለመሰብሰብ በሚመች መልኩ እየተተከለ አይደለም፤ እንክብካቤ አይደረግለትም፤ የአመራረት ዘዴውም በጣም ባህላዊና በዘፈቀደ የሚከወን ነው።

እሳቸው እንደጠቆሙት፤ በኢትዮጵያ ያለው የማንጎ ዛፍ ዝርያ በጣም ትላልቅ መሆኑ ምርቱን በቀላሉ የመሰብሰቡን ሥራ አዳጋች አድርጎታል። ተክሉ ለተባይ የተጋለጠ መሆኑ ደግሞ ጤናማ የሆነ ማንጎን እንዳያመርት እንቅፋት ሆኖበታል። ችግሮቹ አምራቹ በብዛት ምርቱን እንደልቡ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ገቢ ማግኘት እንዳይችልም አድርገውታል። ችግሩ የማንጎን ምርታማነት ከመቀነስ በተጨማሪ ሀገር ከማንጎ የወጪ ንግድ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጎታል ሲሉም ይብራራሉ።

በማንጎ ዛፉ ትልቅነት የተነሳ ምርቱን በአግባቡ መሰብሰብ እየተቻለ አይደለም። በዚህ ምክንያትም ከ40 እስከ 50 በመቶ ምርት ይባክናል። በእዚህ የተነሳም የሚጠበቀው ገቢ እየተገኘበት አይደለም። በተለይ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተው ነጭ የማንጎ ተባይ ምክንያት የኢትዮጵያ የማንጎ ምርት ፈተና ውስጥ ወድቋል። አርሶ አደሩ ተስፋ ቆርጦ የማንጎ ተከሉን እየቆረጠ ይገኛል፤ የችግሩ እየተባባሰ መምጣት ኢትዮጵያ ማንጎን ወደ ውጭ መላክ እንድታቆም አድርጓታል። እነዚህ ችግሮች አምራቹ ተክሉን በሌላ መተካትን ጨምሮ ወደ ሌላ ያልተፈለገ መስመር ወስደውታል ሲሉ ዶክተር ዘላለም ይጠቁማሉ።

ዶክተር ዘላለም አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች ማንጎ እንደሚመረት ጠቅሰው፣ የማንጎ ዝርያዎቹ ለማየት እንኳን የሚጋብዙ እንዳልሆኑና ጥቅም ላይ የመዋላቸው ሁኔታ መቀነሱን ያመለክታሉ። ፈላጊ ስለሌላቸው ለገበያ እንኳን ሲቀርቡ ዋጋቸው ርካሽ መሆኑን ይገልጻሉ። የሀገር ውስጥ ፍላጎት ሳይቀር አሁን ላይ እየተሸፈነ ያለው ከውጭ በሚመጡ ማንጎዎችና ጁሶች መሆኑንም ያመለክታሉ።

ነጭ የማንጎ ተባይ በሀገራችን ችግር ሆኖ ማንጎን ከገበያ እያስወጣ ቢሆንም በሌሎች ሀገሮች በተመሳሳይ የተከሰተ ነገር ግን በቁጥጥር ስር የዋለ ተባይ ነው። ለአብነት ያህል ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ጎረቤታችን ኬንያ ጭምር ችግርነቱን አስቀርተው ጤንነቱ የተጠበቀ ማንጎ በማምረት ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም የምርምር ግብረኃይሉ ዋና አላማ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል። ተባዩ ችግር እንዳይሆን የሚያደርግበትን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገም ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው አንዱ ተባይን የሚመገቡ ነብሳትን ለቆ እነርሱን ማጥፋት ነው።

ሌላኛው ደግሞ በጣም ረጃጅም የሆኑ ዝርያዎችን ቆርጦ አጫጭር በሆኑ ዝርያዎች መተካት ነው። ይህ ዝርያ ደግሞ በማዳቀል ቴክኖሎጂ የሚገኝ ሲሆን፤ ለግብርና ባለሙያዎችና ለአርሶአደሮች ለማስተዋወቅ እየተሠራ ነው። በአጠቃላይ ሀገራዊ የምርምር ግብረ ኃይሉ ሁሉንም የመፍትሔ መንገዶች ተጠቅሞ የማንጎን ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ሥራው የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

በንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በአግሮ ኢንዱስትሪ ላይ የመሰማራት ፍላጎታቸው አናሳ በሆነበት፤ ተባዩ የማንጎ እጥረቱን በብዛት በፈጠረበት፤ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሌሎች ምርቶች ባልተሠራበት ሁኔታ ምርምር ብቻ ዋጋ አይኖረውም ሲሉ ዶክተር ዘላለም ያስገነዝባሉ። በግብረኃይሉ ብቻ ሥራ ብቻ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻልም ያመለክታሉ።

ዶክተር ዘላለም መንግሥት በአቮካዶና ስንዴ ላይ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ለማንጎ ተክልም ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። ከእነዚህ ምርቶች በፊት ማንጎ የውጭ ገቢያችንን ደጓሚ ነበር ያሉት ዶክተር ዘላለም፣ እናም ወደነበረበት ተግባሩ ለመመለስ አዎንታዊ እንቅስቃሴን ይፈልጋል ይላሉ።

ዶክተር ዘላለም ከተመራማሪውና ከግብረኃይሉ ባልተናነሰ መልኩ እንደ ግብርና ሚኒስቴር ያሉ በዘርፉ የሚሠሩ አካላትም ሊሠሩ ይገባል ይላሉ። ሁሉም የበኩሉን ማበርከት እንዳለበትም ነው ያመለከቱት። በርካታ ሀገራት ማንጎ አምራች ሳይሆኑ ከሌሎች ሀገራት ማንጎ እያስገቡ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ያለውን ምርትም በአግባቡ ለመጠቀምም እሴት ጨምሮ መሸጥ ልምድ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።

እነዚህ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት ተቀብለው እሴት በመጨመር ጁስ አድርገው በከፍተኛ ዋጋ ለሌላ ሀገር ያቀርባሉ። እኛ አሁንም በአለንበት ሁኔታ ይህንን ተግባር ለመከወን የሚያስችል ምርት ቢኖረንም እሴት ጨምረን መጠቀም አልቻልንም። ድካም አለው በማለት የሌሎችን ምርቶች አምጥቶ ማከፋፈል አለያም መጠቀምን እንመርጣለን። ስለዚህም ይህ ሁኔታ መታረም አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ግብረኃይሉ አሁን እየሠራ ያለውን ተግባር እንደሚቀጥል ጠቅሰው፣ ይህንን ሲያደርግም ማንጎን ከተባይ በመከላከል፤ በፖሊሲ ደረጃ ትልልቅ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፤ የተለያዩ ዝርያዎችን በመጠቀም ያለውን ጥቅምና የማንጎ ተክል በትኩረት እንቅስቃሴ እንዲደረግበት በማሳመን ላይ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

 ጽጌረዳ ጫንያለው

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You