አዲስ አበባ፡- ከእንጦጦ እስከ አቃቂ ለሚሰራው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ ይፋ በሆነው የ‹‹ሸገር ገበታ›› 255 ሰዎች በባንክ 1 ነጥብ 275 ቢሊዮን ብር ገቢ ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አስታወቀ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሸገርን ለማስዋብ ከተያዘው የ56 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ውስጥ ለሸገር ገበታ 255 ሰዎች እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ብር አስገብተዋል። የእራት ሥነሥርዓቱ በነገው እለት 9 ሰዓት ላይ በቤተመንግስት በሚኖሩ ጉብኝቶች ይጀመራል። ለእራት መስተንግዶዎች 132 ዓመት የሞላው የአፄ ምኒልክ ቤተመንግስት አዳራሽ ተሰናድቷል።
እንደ ዲያቆን ዳንኤል ገለፃ፤ 56 ኪሎ ሜትር ከሚወስደው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት 14 ኪሎ ሜትር ግንባታው በቻይና መንግሥት የተሸፈነ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ተከታታይ የገቢ ማስገኛ መርሐግብሮች እንደሚዘጋጁም ተናግረዋል። በተለይ ለአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የሚሆን 29 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ስለሚታወቅ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የኢትዮጵያ ድርጅቶች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በይበልጥ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ቢሮ ፣ግቢ፣ ከተማና አገር በተባሉ አራት ምዕራፎች የተከፋፈለ መሆኑን አመልክተው፤ በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቢሯቸውን ማስተካከሉን መጨረሳቸውን ጠቁመዋል። በዚህ መሰረትም በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ቤተመንግሥቱ ህዝብ እንዲጎበኝ ይፋ የሚደረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ እስከ አቃቂ የውሃ ማከሚያ ፋብሪካ የሚደርስ የወንዝ ዳርቻ እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን የሚያጠቃልለው ይኸው ፕሮጀክት በቀጣይ ደግሞ ዞኖች፣ክልሎችና መንደሮች ለኑሮ ምቹ ሆነው እንዲቀየሩ በአገር ደረጃ ሥራው እንዲቀጥል መታቀዱን አስታውሰዋል።
በተለይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትን ለመደገፍ ትልቅ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ዲያቆን ዳንኤል፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ለዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን የላቀ ተሳትፎ የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል። «ይህም እኛ ኢትዮጵያውያን የእራሳችንን ታሪክ እራሳችን ለመፃፍ ትልቅ ዕድል ይፈጥርልናል» ሲሉ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግማሽ ቢሊዮን ብር፣ ኢትዮ ቴሌኮም 100 ሚሊዮን ብር፣ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እና የየድርጅቱ ልማት ፕሮግራም እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ 600 ሺ የአሜሪካን ዶላር፣ የጣልያን መንግስት አምስት ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ወስነዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቹ ምቹ ማድረግን ያለመው የሸገር ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ የሦስት ዓመታት እቅድ የተያዘ ሲሆን ግንባታውን በተመለከተ ዝርዝር ጥናቶች ይዘጋጃሉ። ለፕሮጀክቱ ግንባታ ገንዘብ በሚያዋጡ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ስም የሚሰየሙ መንገዶችም ይኖሩታል።ፕሮጀክቱ 29 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ጌትነት ተስፋማርያም