ቤት ለእንቦሳ

የተወለደችው አዊ ዞን አገው ምድር ዳንግላ ነው። እስከ ስምንት ዓመቷ ድረስም በተወለደችበት አካባቢ በአያት እጅ የማደግ እድሉን አግኝታለች፤ የዛሬ የሕይወት ገጽታ ዓምድ እንግዳችን ወይዘሮ መስከረም ተስፋዬ።

ወይዘሮ መስከረም በትውልድ አገሯ ላይ በምታድግበት ወቅት እንደ እድሜ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ሄዶ ፊደል ለመቁጠር አልታደለችም። ይልቁንም እድሜዋ ሰባት ዓመት ሲደርስ በአገር ባህልና ወግ መሰረት ትዳር ትመሰርት ዘንድ ለጋብቻ ተሰጠች።

ጨቅላዋ መስከረምም አብሮ ማደግ በሚባለው የአገሩ ባህል መሰረት አግብታ ወደልጁ እናት ቤት ሄደች፤ ካገባችው የ15 ዓመት ታዳጊ ልጅና ከእናቱ ጋር ኑሮን ተያያዘችው።የእድሜዋ ማነስ ስለ ትዳርም ሆነ ስለኑሮ እንድታስብ አይፈቅድላትም፤ እሷም ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም፤ በዚህም ምክንያት አንድ ወር አማቷ (የባሏ እናት ጋር ) በቀጣዩ ወር ደግሞ የራሷ ቤተሰቦች ጋር እያለች እንደምንም አንድ ዓመት በትዳር አሳለፈች።

እድሜዋ ስምንት ዓመት ሲደርስ ግን አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አጎቷ ሊጠይቋቸው መጡ፤ ባዩትና በሰሙት ነገር ተደናገጡ።” እንዴት ይችን አንዲት ፍሬ ህጻን ትድራላችሁ?” ሲሉም ጥያቄ አቀረቡ መልሱ ባህልና ወጋችን ነው ከእሱ መውጣት አንችልም ደግሞ አብረው ያድጋሉ የሚል ሆነ። የመስከረምም የእድሜዋ ለጋነት በጣም ስላሳዘናቸው ብሎም ነገ በመውለድና በሌላም ምክንያት በጤናዋ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር እንዲሁም ብትማር ለራሷም ለአገሯም ለቤተሰቧም የምትተርፍ ታዳጊ መሆኗን ከግምት ውስጥ አስገብተው ይዘዋት ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ይወስናሉ። እኔ ጋር ሆናም ትማራለች ብለው ቤተሰቧን በማሳመን ከትዳሯ ያስኮበልሏታል።

አዲስ አበባ ለእሷ እንግዳ፤ ባህል ወግ አኗኗሩን የማታውቀው ከተማ ቢሆንም ከእድሜዋ ልጅነት የተነሳ አካባቢውን ለመልመድ ሰውን ለማወቅና እንዴት መኖር እንዳለባት ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባትም። እናም በአጎቷ ቤት ኑሮን ቀጠለች። ነገር ግን መስከረም ከአገሯ ስትመጣ ቃል የተገባላትና አዲስ አበባ አጎቷ ቤት የገጠማት ነገር የሰማይና የምድር ያህል ተራራቀባት። አጎቷ ልጆቻቸውን ያስተምራሉ መስከረም ተማሪ የሆኑትን የአጎቷን ልጆች ጠዋት የመሸኘት ማታ የመቀበል ስራ ትሰራለች። እሷ ግን ትምህርት አልተላከችም።

በኋላም አጎቷ የማታ ትምህርት እንድትማር ቢልኳትም የእሳቸው ልጆች ቀን እየተማሩ አስተምርሻለሁ ብለው አምጥተው ማታ ተማሪ ማለታቸው በጣም ስላስከፋት ትምህርቱን እንደማትፈልገው በማናገር ትምህርት ቤት ሳትሄድ ቀረች።

“……..ከአገሬ አስተምራታለሁ ብሎ ይዞኝ መጥቶ በዚህ መልኩ የማታ ተማሪ ሲለኝ በጣም አዘንኩ፤ ተበሳጨሁ፤ በዚህም ከእሱም ከባለቤቱም ጋር መጋጨት ሆነ ስራችን ።በዚህም ምክንያት ከሰባት ዓመት ቆይታ በኋላ ቤቱን ጥዬ ጠፋሁ” ትላለች።

ምንም እንኳን አዲስ አበባ ላይ ከአጎቷ በስተቀር የምታውቀው የምትጠጋበት ችግሯን ነግራው መፍትሔ የሰጣት አንድም ሰው ባታውቅም አጎቷ ቤት ግን ከዛ በላይ መኖር ስላቃታት ዝም ብላ ጎዳና ስለመውጣቷ ትናገራለች።ፈጣሪ ጥሎ አይጥልምና መስከረም እንደከፋት ጎዳና ወጥታ አልቀረችም አንዲት የማታውቃትን ሴት አገኘች፤ ሴትየዋም በቤት ሰራተኝነት እንደምትቀጥራት ነግራ ወደቤቷ ወሰደቻት።

በሴትየዋ ቤትም በጥሩ ሁኔታ ተይዛ ልክ እንደ ልጅ እያየቻት ለብዙ ዓመታት አብራት እንድትኖር ሆነ። በዚህ መካከል መስከረም የራሷን ኑሮ መኖር ስላማራትና ትዳር መያዝም እንዳለባት ስላሰበች ይህንን ሀሳቧን ከመሬት ላነሳቻት አሰሪዋ ነገረቻት፤ አሰሪዋም ደስ እያላት ልክ እንደልጇ አድርጋ በመዳር ጎጆ እንድትቀልስ አገዘቻት።

“…….ሁሌም የሚገርመኝ ነገር አጎቴ እንደልጄ አስተምራታለሁ ብሎ ቢያመጣኝም የገጠመኝ ነገር ፍጹም የተለየ ነበር፤ ነገር ግን የማታውቀኝ ሴትዮ ሰውነቴን ብቻ አስባ ከዘመድ በልጣ እንደልጇ አድርጋ ጎጆ እንድመሰርት አገዘችኝ። በዚህም ትዳር ለመመስረት በቃሁ” በማለት ትናገራለች።

መስከረም ትዳር መስርታ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ወደምትገኘው የጫንጮ ከተማ ነበር የሄደችው። እዛም ጠላ እየጠመቀች፣ ፈጣን ምግቦችን ሰርታ እያቀረበች ጎጆዋን ባለቤቷን መደገፍ ጀመረች። ነገር ግን መስከረም የባለቤቷ ቤተሰቦች ጎረቤቶቿ መሆናቸው ብዙም ምቾት ሳይሰጣት ቀረ በተለይም የመጀመሪያ ልጇን ከጸነሰች በኋላ ከባለቤቷ እህት ጋር በረባ ባልረባው መጋጨት ሆነ ስራቸው።

“…..በወቅቱ በጣም ልጅነት ያጠቃኝ ስለነበር አንዳንድ ነገሮችንም ማገናዘብ አልቻልኩም ፤ ከእህቱ ጋር በሆነ ባልሆነው ነበር የምንጣላው፤ መጣላቴም በቤቴ በኑሮዬ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ምንም አላውቀውም ነበር” በማለት ዛሬ ላይ ቆማ ስታስበው በመገረም ትናገራለች።

መስከረም ከእህቱ እንዲሁም ከሌሎች ቤተሰቦቹ ጋር መስማማት ባትችልም የመጀመሪያ ልጇን ግን እዛው በሰላም ተገላገለች ፤ ነገር ግን አሁንም ስላልተቻቻሉ በወለደች በ14 ቀኗ ልጇን ይዛ ከቤት ወጥታ አዲስ አበባ ገባች።

“…….አዲስ አበባ መጀመሪያ የዳረችኝ ሴት ጋር የ14 ቀን ልጄን ይዤ መጣሁ፤ ነገር ግን እሷ ከነልጄ የመቀበል ፍላጎት ባለማሳየቷ ቀደም ብዬ የማውቃት ጓደኛዬ ጋር በመሄድ ችግሬን ነገርኳት፤ እሷም ከነልጅሽ ቀጥረው የሚያሰሩ ሰዎች አይጠፉም ብላ ሰው ቤት በሰራተኝነት አስገባችኝ ” ትላለች።

መስከረም ከነልጇ የሚቀጥሯት ሰው በማግኘቷ ተደሰተች ።አዲስ አበባ ቤላ አካባቢ ያገኘችው ቤትም ከብቶች ያሉበት በመሆኑ የእነሱን ቤት ማጽዳት፣ አዛባ መዛቅና መጠፍጠፍ እንዲሁም ሌሎች የማዕድ ቤት ስራዎችን መስራት ደግሞ ኃላፊነቶቿ ነበሩ።

“……..በወቅቱ የ14 ቀን ልጅ ይዤ ስራ ማግኘቴ በጣም ነበር ደስ ያለኝ ፤ ስራ የቀጠሩኝንም ሰዎች ያልኳቸው ልጄን አትበድሉብኝ እንጂ እኔ ለአንድ ዓመት ያህል ምንም ዓይነት ደመወዝ አልጠይቅም ነበር። እነሱም በዛ መሰረት ስራውን ማሰራት ጀመሩ። እኔም ልጄን እያጠባሁ ስራውንም እየሰራሁ ነበር የምውለው።በወቅቱ እኔ ልጎዳ እንጂ ልጄ ግን በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነበር።” ትላለች።

ነገር ግን መስከረም ልጇ በደንብ እንዲያዝላት ብቻ በማሰብ ስራ ስራዋን በምትልበት ጊዜ ያላስተዋለችው ወይም ያልተረዳችው ነገር ነበር፤ ይኸውም የቤቱ ባለቤት የኤች አይ ቪ ቫይረስ ታማሚ መሆኑን ነው፤ ይህንን አለማወቋ ደግሞ ለእሷም ለልጇም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዳታደርግ አደረጋት።

አሁንም ስራዋን ከመስራት አልተቆጠበችም። ነገር ግን ልጇ የስድስት ወራት እድሜው ላይ ሲደርስ ሰውነቱ ሽፍታ ማውጣት ጀመረ፤ እናት መስከረምም በሁኔታው ግራ ተጋባች የንጽህና ችግር ነው እንዳትል እሷ ተጎድታም ቢሆን ልጇን በንጽህና ነው የያዘችው ፤እሷ አትመገብ ይሆናል እንጂ ልጇ እንዲራብባት ፍጹም አልፈቀደችም፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የልጇ ጤና እያሳሰባት የተለያዩ የህመም አይነቶችና ለውጦችንም እያስተዋለችበት መምጣቷ ግን አልቀረም።

“……ልጄን በምችለው ሁሉ ራሴን ጎድቼ በጥሩ ሁኔታ ከመያዜ የተነሳ የሚያየው ሰው እንኳን ይህማ የአንቺ ልጅ አይደለም ይሉኛል። ጡቴን እያጠባሁት እያዩ ሰርቀሽ ነው ሁሉ የሚሉኝ ነበሩ። ነገር ግን ህመሞቹ እየበዙ ሲሄዱ ወደጤና ተቋም ወሰድኩት እነሱም መርምረውት ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንዳለ ነገሩኝ። ይህንን መስማት ለእኔ ቀላል አልነበረም “ትላለች።

መስከረም ከልጇ አባት ጋር ከተለያየችና ልጇን ይዛ ወጥታ በሰው ቤት በስራ ተጠምዳ ከማሳደግ ውጪ አንድም ቀን ጾታዊ ግንኙነት ከማንም ጋር ኖሯት ስለማያውቅ ይህ በልጇ ላይ የሰማችው በሽታ ምንጩ ከየት እንደሆነ ግራ ገባት። ሀኪሞቹም እሷም ተመርምራ ራሷን ማወቅ እንዳለባት ሲነግሯት አላቅማማችም ውጤቷም ከልጇ ጋር ተመሳሳይ ነበር። ኋላ ላይ ግን የበሽታው ምንጭ አሰሪዋ መሆኑን ቆይታ ተረዳች። ቫይረሱ ደግሞ ወደእሷና ወደልጇ የሄደበት ምክንያት የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑንም አወቀች።

“……ከልጅነቴ ጀምሮ በችግር ባድገም ያን ያህል ግን መጥፎ ተግባራት ላይ አልሄድም ነበር። ሰርቼ ራሴን ለማስተዳደርም ከፍ ያለ ጥረትን ሳደርግ ነው የኖርኩት። ትዳርም መስርቼ ሳይሳካልኝ ሲቀር ልጄን ለማሳደግ የነጻ አገልግሎት ለመስጠት ነው ሰው ቤት የገባሁት እናም ስለ ቫይረሱም ሆነ ስለመምጫ መንገዱ ያን ያህል ግንዛቤ አልነበረኝም። በሌላ በኩል ደግሞ ታሞ ተጎድቶ ያለን ሰው ሳይ ፍጹም አያስችለኝም መጠየፍ ብሎ ነገርም አልፈጠረብኝም። አሰሪዬም በየጊዜው ይታመም ነበርና እሱን ማጠብ መንከባከብ ማጸዳዳት ሁሉ ስራዬ ነበር። ይህንን ሳደርግ ግን አንድም ቀን ጥንቃቄ አድርጌ አላውቅም።ስለ ሁኔታውም የነገረኝ የቤተሰብ አባል የለም ።እናም ከራሴ አልፌ ህመምን በልጄ ላይ አመጣሁ ” በማለት ከፍ ባለ ሀዘን ውስጥ ሆና ሃሳቧን ትገልጻለች።

መስከረም የደረሰባት ችግር ሳታስበው የገባችበት በሽታ በጣም አስደነገጣት። አሰሪዋ ደግሞ ጤና ተቋም ሄዳ እሷም ልጇም ላይ ቫይረሱ መተላለፉን እንደሰሙ ሲያውቅ በጣም ተናደደ በዚህም ከምሽቱ 2 ሰዓት ልጇን አዝላ ከቤቱ እንድትወጣ አደረጋት፤ ልጇ ደግሞ ከኤች አይቪ ቫይረስ በተጨማሪ የነርቭ እንዲሁም የስኳር በሽታ ታማሚ በመሆኑ መስከረም ብዙ ተፈተነች።

“……..ከሁሉም በላይ ልጄ ከፍ ሲል የነርቭ ታማሚ ሆኖ ሳገኘው ደግሞ ነገሮች ይበልጥ ተወሳሰቡብኝ ወገቡ ቀና አይልም እግሩም አይቆምም እጁም አይሰራም ነበር፤ አሁንም ልጄን ማዳን አለብኝ በማለት ደጋግ ሰዎችን በማስቸገር እነሱም ሁኔታችንን አይተው በማዘን አዲስ ሕይወት ሆስፒታል የምሄድበትን መንገድ አመቻቹልኝ እዛም ልጄ ለወር ያህል ተኝቶ ህክምናና ስፖርት እንዲያገኝ ከሆነ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ከችግሩ ዳነልኝ ” ትላለች።

መስከረም ከምትሰራበት ቤት ከወጣች በኋላ ኑሮዋን ለመግፋት የተሻለ ነገርን ለማግኘት ብሎም ልጇን ለማሳደግ ስትል ሌላ ትዳር መሰረተች ።ባለቤቷም የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል የነበረ ሲሆን ሁለተኛ ልጇን እንደወለደች ለሰላም ማስከበር ወደላይቤሪያ እንደሄደ ሳይመለስ ቀረ።የእድል ጉዳይ ሆኖ ደግሞ እድሜው ለጡረታ ባለመድረሱ ልጇን የምታሳድግበት ነገር አጣች።ይህ ሁኔታ ለመስከረም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሉት አይነት ሆነባት።

መስከረም በሕይወቷ ብዙ ያገዟት ሰዎች ያሉ ቢሆንም ስሟን፣ ስራዋን፣አድራሻዋን የማታውቃት ሴት ግን ልጇን ከማሳከም ጀምሮ እስከ አሁንም በሕይወት እንዲቆዩ ብዙ ነገሮችን እንደምታደርግላቸው ትናገራለች።ለዚህ ደግነቷም ፈጣሪ ዋጋዋን እንዳይነሳት እጸልያለሁ ትላለች።

ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል አካባቢ መኖር ጀመረች፤ ነገር ግን አካባቢው ላይ ትንሽ ጊዜ ከቆየች በኋላ በቀጥታ አዋሬ አካባቢ ለስሙ ቤት የሆነ ማደሪያ ቀበሌው ሰጥቷት መኖር ቀጠለች ።የምትኖርበት ቤት ግን ከደጅ ያልተናነሰ የመጸዳጃ ቤት ትቦ በውስጡ የሚያልፍ ለመኖር አይደለም በአካባቢው ላይ ለማለፍ እጅን አፍንጫ ላይ ለመጫን የሚያስገድድ እንደነበር ትናገራለች ።

ቤቱ ስሙ ቤት ይሁን እንጂ በውስጡ የሚያልፈው የመጸዳጃ ፍሳሽ ጠዋት የታጠበን ልብስ ለማታ የሚያሸት፣ምንም እሳት በቤት ውስጥ ሳይነድ እንደ ወይራና እጣን የመሳሰሉ ነገሮች ሳይጨሱ 30 ደቂቃ ከተቆየ ሽታው አፍኖ ሊገድል የሚደርስ፤ እንደ ቤት ደጃፉ ላይ ወጣ ብሎ መቆምም ሆነ መቀመጥ የማይታሰብበት ማታ ሲተኙ ልክ አንደ ቀኑ ሁሉ እሳት አያይዘው እጣንና ወይራ እያጨሱ መተኛትን ግድ የሚል ነበር። ዝናብ ጠብ ሲልም በየአቅጣጫው የሚወርደው ውሃ ላስቲክ የሚያስለብስ ከመሆኑ የተነሳ ጎዳና ከማደር ይሻላል በሚል የሚኖርበት አንጂ ቤት የሚለውን መጠሪያ ስም የሚያሟላም አልነበረም ትላለች።

ይህም ቢሆን ግን መጠጊያ የሌላቸው መስከረምና ሁለት ልጆቿ ለሰባት ዓመታት ኖረውበታል።ችግሩን ሁሉ ተቋቁመው አልፈውም እዚህ ደርሰዋል። መስከረም ሁሌም ቢሆን ቤቷ ሰው ገብቶ ቡና የሚጠጣበት የሚጨዋወትበት አለመሆኑ፤ ከምንም በላይ ልቧን ይነካው ነበር። አብዝታም ወደፈጣሪዋ ትጣራ ነበር፤ መቼ ነው ያጠብኩትን ልብስ ለብሼ ከሰው የምቀላቀለው ብላም ታዝን ነበር፤ ከሀዘኗ የተነሳም ተስፋ በመቁረጥ በምድር ላይ ይገላል ብላ ያሰበችውን ነገር ሁሉ አድርጋለች።አደንዛዥ እጾችን ተጠቅማለች። ጠጥታለች ፤ ጫት ቅማለች ፤ ብቻ ብዙ ነገሮችን አድርጋለች።ድብድብም ስራዋ ነበር። የልጆች እናት ብትሆንም ኖሬም ምንም የተለየ ነገር አላደርግላቸውም ስለዚህ ብሞት ይሻላል በማለት ያልተገቡ ነገሮችን ሁሉ አድርጋለች።

ሀዘኗ ግን በዛው ይቀጥል ዘንድ ፈጣሪ አልፈቀደም፤ ልመናዋም ከዳመና በታች አልሆነም። ይልቁንም ጩኸቷ ተሰምቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ልኮም ኑሮዋን ቀየረው፤ ዛሬ መስከረም በቤት በኩል የነበረባት ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል፤ ዛሬ ቤቷ ጽዱ ነው፤ ዛሬ ቤቷ ማንም ቢመጣ አትሳቀቅም፤ እሳት አንድዶ ወይራ እያጨሱ መተኛት ታሪክ ሆኗል፤ ልጆቿም በጣም ደስተኛ ሆነውላታል።

መስከረም ስሙ ቤት ይባል እንጂ ብዙ ጉድ ከተሸከመው የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በውስጡ ከሚያልፈው፤ ጣሪያው ወንፊት ሆኖ ኮከብ ከሚያስቆጥረው ቤት ወጥታለች ።ዛሬ ዝናብ ሲጥል ላስቲክ ለብሳ አትተኛም። በጠቅላላው ታሪኳ ተቀይሯል።

መስከረም ቤቱ ፈርሶ በአዲስ መልክ ይሰራል የሚል ዜናን ስትሰማ ከመደሰቷ የተነሳ ጭንቀት ሁሉ ይዟት እንደነበር ታስታውሳለች ፤ ዳግመኛ መወለድ እኮ ነው የምትለው መስከረም “…… ሰው እንኳን ቤቴ ገብቶ እንደምንአደርሽ ሊለኝ በበሬ ላይ እንኳን ሲያልፍ አፍና አፍንጫውን ሸፍኖ ነበር። እኔ ግን እኖርበታለሁ ፤ ዛሬ ማንም ቤቴ መጥቶ እንዴት ነሽ ይሉኛል፤ ከእንዴት ነሽ አልፈውም ለልጆችሽ ላንቺ ምን እናድርግ ብለውም ይጠይቁኛል፤ አሁን ቤት ከሰው እኩል አድርጎኛል” በማለት ትናጋራለች።

“……እኔ ከእናቴ ሆድ ከወጣሁ ጀምሮ ምቾትን አላውቀውም ዛሬ ላይ ግን ታሪክ ተቀየረ ዛሬ ቤት አለኝ ልጆቼ ጥሩ ቤት ውስጥ ያድራሉ፤ አይሸታቸውም ጉንፋን የለም ብቻ በአጠቃላይ እኛን ያየ ፈጣሪ ሌሎቹንም ይይልኝ” በማለት ትናገራለች።

መስከረም ከቫይረሱ ጋር አብራ እንደምትኖር የማትደብቅ በመሆኗ አሁን ላይ ቤት ውስጥ ቀጥሮ በተመላላሽ እንኳን የሚያሰራት ሰው ባለማግኘቷ ከወንዶቹ እኩል እየተሸከመች ከሰልና አንዳንድ ነገሮችን እየሸጠች ነው ልጆቿን የምታስተዳድረው።

“……እኔ ራሴን አልደብቅም፤ ከቫይረሱ ጋር እንደምትኖር እናገራለሁ ፤ ይህ ግን በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን አሳጥቶኛል፤ እኔን ቀጥሮ በቤቱ በተመላላሽነት ማሰራት ቀርቶ አብሬያቸው ቡና እንድጠጣ እንኳን የሚፈልጉ ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ ወንዶች የሚሰሩትን ሸክም እየሰራሁ እኖራለሁ ።ፈጣሪም አግዞኝ መድሃኒቴን እየወሰድኩ ፍጹም ጤነኛ ነኝ ” በማለት ትናገራለች።

መስከረም በዚህን ያህል ደረጃ ሰዎች ቢያገላትም እሷ ግን በሚያመቻት ቀንና ሰዓት በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ በመሄድ እሷን መሰል ታመው የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሰዎችን በበጎ ፍቃደኝነት ታግዛለች፣ ትረዳለች፣ ልምዷን ታካፍላለች፤ በዚህ ተግባሯም ብዙ ወዳጆችን አፍርታለች።በርካቶችም ለመልካምነቷ ሲሉ ብዙ ነገሮችን እንደሚያግዟትም ታብራራለች።

መልዕክት

መስከረም ዛሬ ላይ ከወደቀችበት ተነስታለች ዛሬ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደረገ ድጋፍ ቤት ተሰርቶላት ደስተኛ ሆናለች።ነገር ግን ታማሚ ልጅ ይዛ እሷም ታማሚ ሆና ያሰበችውን ሰርታ እየኖረች ባለመሆኑ የእለት ጉርሱም ያስጨንቃታል። በዚህ ልክ ብትጨነቅም የሰውን እጅ መጠበቅ ደግሞ አትፈልግም። ከዛ ይልቅ ዘላቂ እርዳታን በተለይም የልብስ ማጠቢያ ማሽን አግኝታ ቤቷ ቁጭ ብላ ብትሰራ ምኞቷ ነው።።

ፈጣሪ ይመስገን እስከ አሁን ከልጄ ህመም በቀር እኔ ምንም የሚያመኝ ነገር የለም። መድሃኒቴንም በአግባቡ እየወሰድኩ ነው የምትለው መስከረም ሁሌ የሰው እጅ ጠባቂ ከመሆን ሰርቼ ለልጆቼና ለእኔ የእለት ጉርሳችንን የማገኝባትን መንገድ ቢፈጠርልኝ ስትልም ወደ ደጋግ ኢትዮጵያውያን እጆቿን ትዘረጋለች።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You