ያልተፈተሹ የትምህርት ተቋማት ኋላ ቀር አሠራሮች

በአንድ ወቅት በአንድ ስፍራ ነዋሪውን በሁለት ጎራ ከፍሎ ያከራከረ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በወቅቱ የተማሩ የሚባሉ ሰዎች ውሏቸው ከቤተመንግሥት አካባቢ፣ ከዳኝነት ስፍራ፣ ምክርና ውይይት ከሚያስፈልግበት ሆነና አርሰው፣ ነግደውና በእጅ ሥራ ከሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታ ቀረበባቸው፡፡ ከፍ ዝቅ ሳይሉ፣ ሳያርሙ ሳይጎለጉሉ፣ ሳይሸከሙ ጉልበታቸው ሳይደክም… ሁሌም ጥንቅቅ ባለ አለባበስ እንዳማረባቸው ከአደባባይ ውለው ይገባሉ። ታዲያ ይህ ሁኔታ በላባቸው ደክመው ለሚኖሩት እንደ ሥራ ፈትነት ስለታየባቸው ‹‹ትምህርት አይጠቅምም›› ከሚል መደምደሚያ ደረሱ፡፡

ለዓመታት አንገታቸውን ከመጽሐፍት መካከል ቀብረው እውቀትን ያካበቱት ደግሞ ከጥቅሙ ተቋድሰዋልና ‹‹የለም የመማርን ያህል ጥቅም ያለው ነገር አልተፈጠረም›› ሲሉ ሙግት ገጠሙ፡፡ ውሎ ሲያድር ሁኔታው ይበልጥ እያከራከረ ስለመጣም በዕድሜም በዕውቀትም ‹‹አንቱ›› የተባሉ ሊቃውንት ተሰባስበው ለሁለቱ አካላት በቀላሉ መልስ ሊሰጥ የሚችል ፈተና ለማዘጋጀት ተሰየሙ፡፡ ፈተናው በተዘጋጀበት ዕለትም ሁለቱን አካላት የሚወክሉ ሰዎች ተመርጠው ፈተናው ከሚደረግበት የግብር አዳራሽ ተገኙ፡፡ ሕዝቡም ማን ይረታል የሚለውን ለመመልከት በስፍራው ታደመ፡፡

ፈተናው እንዲህ ነው፤ ከግብር አዳራሹ ሁለት ገበታዎች ተዘጋጅተው ሁለቱን አካላት የሚወክሏቸው ሰዎች በየጎራቸው እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ ከገበታው የቀረበውን ገንፎ የሚመገቡበት የቀንድ ማንኪያዎችም ተሰጣቸው። በመጀመሪያ ነገሩ ለሁለቱም አካላት ግራ የሚያጋባ ነበር፤ ምክንያቱም ለመቢያ የቀረቡላቸው ማንኪያዎች ቀድሞ ከሚያውቋቸው ይልቅ የረዘሙ በመሆናቸው ነው። ካልተማሩት ወገን ማንኪያቸውን አንስተው እንጉረስ ቢሉ፤ የማንኪያው እጀታ ርዝመት ወዲያ የሌላኛቸውን ዓይን ሊጠነቁል ሆነ፡፡ አያያዛቸውን አስተካክለው ከጫፍ ቢያደርጉም ከርዝመቱ የተነሳ አፋቸውን የሚያልፍ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ነገሩ አታክቷቸው ገበታውን ጥለው ተነሱ፡፡

ከተማሩት ወገንም ነገሩ ከዚህ ቀደም አይተውት የማያውቁት ሆኖ ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ ጥቂት አሰብ አድርገው ግን መላ መቱ፤ እናም ረጃጅሞቹን ማንኪያዎች አንስተው አንዱ ለሌላው፣ ያኛውም ለዚህኛው በቀላሉ በመጎራረስ የቀረበላቸውን አጣጣሙ፡፡ ታዲያ ይሄ ብልሃታቸው ምላሽ ሆኖ የዕውቀት ምንነትና አስፈላጊነትን በቀላሉ ለሕዝቡ ማስገንዘብ ተቻለ፡፡

መማር ነገሮችን አስፍቶ ለመረዳት፣ ችግሮችን ለመፍታት በጥቅሉ ሕይወትን ለማቅለል ቁልፍ መሣሪያ መሆኑ ለማም ግልፅ ነው፡፡ መቼም በዚህ ዘመን የትምህርት አስፈላጊነት አያጠያይቅም፤ ውዴታም ግዴታም ነው፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የሆነው የመማር ትክክለኛ ጠቀሜታ እና ውጤት ተዘንግቷል፡፡ የበርካቶች መማር ከራሳቸው አልፎ ለዓለም ሕዝብ ብርሃንን አጎናጽፏል፡፡ የምንልቀው ግን የምንማረው ምናልባትም ደመወዝ በማግኘት ራሳችንን ለማስተዳደር ነው፡፡ በአንድ በኩል ከጊዜው አንጻር፣ ካለንበት የአስተሳሰብም ሆነ የአኗኗር ሁኔታ አኳያ ይህ አተያይ ስህተት አይባል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ የተነሳንበትንና መማር ወይም ማወቅ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ የሚያፋልስ ይሆናል፡፡

ለአብነት ያህል ‹‹መማር ሥራ ለማግኘት ብቻ›› የሚለው ሃሳብ በትምህርት ተቋማት ቢንጸባረቅ፤ ሐዲዱን የሳተ ባቡር ዓይነት ሆነ ማለት አይደል? የመማር አንኳር ጠቀሜታ ችግሮችን መፍታት፣ መፍትሔዎችን ለማንጸባረቅ፣ ሳይንሳዊና ተገቢ የሆኑ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ሆኖ ሳለ፤ በእውቀት የካበቱ ምሁራን ባለቤት የሆኑት የትምህርት ተቋማት ከሌሎች ተቋማት ያልተናነሰ ቢሮክራሲና ኋላ ቀር አሠራር ሲያራምዱ አላስተዋላችሁ ይሆን?

በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ የተነሳው ታሪክ የተማሩ ሰዎች አእምሯቸውን ተጠቅመው ዘዴና ብልሃትን ሲወልዱ የተመለከተው ማኅበረሰብ የምሁራኑንና የመማራቸውን ጠቀሜታ ከምንም በላይ ስለመረዳቱ አያጠራጥርም፡፡ እኛስ በሕይወት አጋጣሚ በምንደርስባቸው የትምህርት ተቋማት ቀላሉ ነገር ከብዶ፣ የተወሳሰቡ አሠራሮች ተንሰራፍተው አልገጠመን ይሆን? በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከተመዘገቡበት ጊዜ አንስቶ ተመርቀው እስኪወጡ ባሉት ጊዜያት የሚያሳልፉት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲህ ነው ሊባል የማይችል ነው፡፡

ወቅቱ በርካታ ተቋማቱ አዳዲስ ተማሪዎችን የሚቀበሉበትም አይደል፤ ‹‹ካላየሁ አላምንም›› የሚል አካል ሄዶ ሊታዘባቸው ይችላል፡፡ መንግሥት ከሚመድባቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ውጪ የዕውቀት ጥማታቸውን ለማርካት፣ ራሳቸውን ለማሻሻል እና ሀገራቸውን ለመርዳት ብዙዎች በማታ፣ በሳምንቱ መጨረሻ እና በርቀት ለመማር ወደነዚሁ ተቋማት ያቀናሉ። የምዝገባና ሌሎች ሁኔታዎችን አጠናቀው ከመምህራኑ ጋር በመማሪያ ክፍል ለመገኘት ግን ከተመዘኑበት የመግቢያ ፈተና በላይ የሆኑ ፈተናዎችን ሊያልፉ ይገደዳሉ ብንል ማጋነን አይደለም፡፡

ይህ የሚሆነው እጅግ ረጅም ሂደቶችን በሚጠይቁ፣ በተቆራረጡና ቅንጅት በጎደላቸው አሠራሮች ሲሆን፤ ምሁራን በሞሉበት፣ ሀገራቸውን ሊቀይሩና ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር በሚተጉ የትምህርት ተቋማት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ግራ ያጋባል። በእርግጥ በልፋታቸው ትልልቅ ደረጃ የደረሱና ትውልድን ለመቅረጽ የሚተጉ ምሁራን የተማሪዎችን ምዝገባ የሚመለከቱና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ይግቡ ሊባል አይችልም፡፡

ነገር ግን አፈር ላይ የወደቀ ስጋ አፈር ይዞ መነሳቱ አይቀርምና፤ ዕውቀት በሚሸመትበት ተቋም ኋላቀርነት መንገሡ ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህም አንድም አሠራሩን ማዘመን፣ በተማሪዎች የሚቀርበውን ቅሬታም የሚያርቅ መላ መምታት የእነዚሁ ምሁራን ድርሻ ነው። እንደሚታወቀው የተማረ ሰው ሊሰማራ የሚችለው ማኅበረሰብን እና ሀገርን በማገልገል ዘርፍ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ግለሰቦች(በተለይ እየሠሩ የሚማሩ ሰዎች) ከሚያገኟት ገቢ ቀንሰው፣ ከጊዜያቸውም አጣበው በብዙ ችግሮች መካከል ራሳቸውን በእውቀት ለመገንባት ከእነዚህ የትምህርት ተቋማት ሲገኙ አሠራሮችን ማንዛዛት ሊያርቃቸው እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ ይህ ሁኔታ እየሰፋ ሲሄድ ደግሞ ሀገርን ጉዳት ላይ የሚጥል ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ይህን መሰሉ አሠራር እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ሠራተኞች የትምህርት ደረጃቸውም ይህንን ሊፈጥር እንደሚችልም አይጠየቅም፡፡ በመሆኑም የትምህርት ተቋም ውስጥ እየሠሩ ራስን ለማሻሻልና በትምህርትም ራስን ለማሳደግ ጥረት አለማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ተቋማቱም ሠራተኞቻቸው ከተማሪዎቻቸውና ሌሎች አገልግሎት ፈላጊዎች ጋር በተመጣጣኝ ቋንቋ እንዲግባቡ ማበረታታትና የትምህርት ዕድሎችን ሊያመቻቹላቸው ይገባል፡፡ አሠራራቸውንም ሊፈትሹና እንከን ላለባቸውም መላ ቢሉ መልካም ነው፡፡

የመማርን ውጤት በቅድሚያ የምንመለከተው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ የትምህርት ተቋም ውስጥ የተቀጠረ ሰው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ራሱን በትምህርት ካላበቃ የትምህርት ተቋማት ሚና ምን ሊሆን ይችላል? ‹‹ሳይማሩ ያስተማሩን…›› እንደሚባለው ‹‹ሳይበቁ ለማብቃት›› አያሰኛቸውም? እስኪ አስቡት ዘመናዊና ነገሮችን የሚያቀሉ አሠራሮችና መፍትሄዎችስ ቅድሚያ በምሁራኑ ዘንድ ተግባራዊ ካልሆኑ በእነማን ሊሆኑ ነው?

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You