የብሪክስ አባል መሆናችን ለጀመርነውልማት ተጨማሪ አቅም ነው

 ብሪክስ የኢትዮጵያ የሚዲያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ይፋ ከተደረገበት ቀን አንስቶ ስለብሪክስ ማንነት፣ ለምን እንደተመሰረተ፣ ወዴት እንደሚጓዝ፣ እነማንን እንደአቀፈና በቀጣይም እነማንን እንደሚያቅፍ፤ በምጣኔ ሀብት፣ በጸጥታና ደህንነት፣ ወዘተ ምን አንደሚያከናውን በመንግስት ኃላፊዎች፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በዲፕሎማቶችና በፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፣ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ ወዘተ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፤ አየተሰጠበትም ይገኛል።

አጀንዳው ገና ብዙ ሊጸፍበት፣ ሊነገርበትና ሊሰራበት የሚገባ እንደመሆኑ በቀጣይም ከዚሁ አኳያ ብዙ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ስለተቀላቀለችው ግዙፍ ሕብረት ማንነት ማብራራት ኢትዮጵያ በቀጣይ ከማን ጋር ልትውል እንደሆነ ለማሳየት እንዲሁም ምን እንደሚጠበቅባትም ለማመልከት ማብራሪያዎቹ ፋይዳቸው ከፍተኛ አላቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሕብረቱን የመሰረቱት አምስቱ ሀገሮች/ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ ከዓለም የመሬት ስፋት 27 በመቶውን የሚሸፍኑ ናቸው። ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና ብቻ በህዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋት፣ በአጠቃላይ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ከዓለማችን አስር ግዙፍ ሀገሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና ደግሞ የወቅቱ ኃያላን ሀገሮች ሊባሉ የሚችሉ ወይም በብዙ መልኩ ጎልተው እየወጡ ያሉ ሀገሮች ናቸው።

እስከ አሁን የዓለምን ኢኮኖሚ እየዘወሩ የሚገኙት ያደጉት ሀገሮች በፈጠሩት ኢፍትሃዊነት ሳቢያ ዓለም ወደ አንድ ወገን ባጋደለ መልኩ እየተዳደረች ትገኛለች፤ ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድና ብራዚል ይህን ሁኔታ ሊቀይር ይችላል ያሉት ብሪክስን መሰረቱ። ቆይቶም ደቡብ አፍሪካ ቡድኑን እአአ በ2009 ተቀላቀለች። ሕብረቱ የዓለምን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ጭምር ይለውጣል በሚል ታምኖበታል።

ይህ መቀመጫውን በቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ ያደረገው ሕብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያቸው እያደገና ተጽእኖ ፈጣሪ እየሆነ የመጣ ሀገሮች ስብስብ ነው። በ2021 በወጣ መረጃ መሰረት የጥምረቱ ሕዝብ ብዛት 3 ነጥብ 24 ቢሊየን ነበር። ይህም ከዓለም ህዝብ ከ40 በመቶው በላይ ነው፤ በሀብት በኩልም ሲታይ የጥምረቱ ሀገሮች አጠቃላይ ሀብት ከዓለም ሀብት 31 በመቶውን ይይዛል።

የብሪክስ አባል ሀገሮች በዓለም ለይ ያሉ ሸቀጦችን ወደ ሀገራቸው በማስገባት ረገድ 14 በመቶ ጥቅል ድርሻ አላቸው፤ የቻይናን የገቢ ንግድ ብቻ ብንመለከት እስከ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ሲደርስ፣ በጥቅሉ አምስቱ ሀገሮች ብቻ 3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር የገቢ ንግድ ልውውጥ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጂ 7 በመባል የተሰባሰቡት ሀብታምና ኃያላን ሀገሮች የጋራ ሀብት እዚህ ሀብት ላይ አይደርስም፤ የብሪክስ ስብሰብ ሀገሮች ከጂ 7 ሀገሮች በላይ በፍጥነት እያደጉ ያሉ፣ በቀጣይም ለማደግ ሰፊ ተስፋ ያላቸው ሀገሮች ናቸው፤ ቻይናና ህንድን የመሳሰሉት ሀገሮች ደግሞ የበለጠ ለማደግ ምቹ ሁኔታና ተስፋ እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እነዚሁ መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በሚቀጥሉት ዓመታት እነዚሀ የብሪክስ ሀገሮች ይበልጥ ሲጠናከሩ 60 በመቶ የዓለምን ኢኮኖሚ ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ጥምረቱን ለመቀላቀል ያመለከቱ ሌሎች በኢኮኖሚያቸው ከፍ ያሉ እንደ ቬንዝዌላ ያሉ ሀገሮች ሲቀላቀሉ ኢኮኖሚው 70 እና 80 በመቶ ይደርሳል የሚል ግምትም ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ ይህን ስብስብ እንዴት ልትቀላቀል ቻለች? ይህን ጥያቄ መመለስ ለአሰላለፉ ይጠቅማል። ይህን ስብስብ ለመቀላቀል ከፍተኛ የሀብት መጠን፣ ተስፋ፣ የህዝብ ብዛት፣ የዲፕሎማሲ ስራ፣ ወዘተ ሊያስፈልግ እንደሚችል የጎራው ግዝፈት ብቻ ሳይሆን ጎራውን የመሰረቱት ሀገሮችም አቅም ከፍተኛነት ያመለክታል። አሁን ስብስቡን ከኢትዮጵያ ጋር ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ኤምሬት፣ ግብጽ. ኢራን፣ አውስትራሊያ ተቀላቅለውታል። ሌሎች አርባ ሀገሮችም ስብስቡን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ስብስቡን የመሰረቱትም ሆኑ በቅርቡ የተቀላቀሉት አብዛኞቹ ሀገሮች የምጣኔ ሀብት አቅም ከፍተኛ መሆኑን ማንም ይገነዘበዋል። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገሮች አኳያ ስትታይ የምጣኔ ሀብት አቅሟ ውስንነት ሊኖረው ይችላል። እንዲያም ሆኖ ግን ሀገሪቱ በማደግ ላይ ያለች ሀገር መሆኗን ማንም ጥርጣሬ ውስጥ አያስገባውም፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር በየጊዜው ያረጋገጡት ሀቅ ነውና።

ኢትዮጵያ በተከታታይ የምጣኔ ሀብት እድገቷ ትታወቃለች። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናም ጭምር ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ በቀጣይም ልታድግ እንደምትችል ነው መረጃዎች እያመለከቱ ያሉት። በግብርናው፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በአገልግሎት ዘርፍ ያሉት እምቅ አቅሞችም ሌሎች የሀገሪቱ ተስፋዎች ናቸው።

የልማት አያያዝዋ፣ እምቅ ሀብቶቿ ሂሳብ ውስጥ አልገቡም ማለት አይቻልም። የግብርና ምርትና ምርት

 እድገት በየዓመቱ ሊባል በሚችል መልኩ እየጨመረባት ትገኛለች። ግብርናዋን ከዝናብ ጥገኝነት በማውጣት በመስኖ ጭምር ማልማት ውስጥ ገብታለች። ከፍተኛ መጠን ያለው የግብርና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብም ትታወቃለች።

ሀገሪቱ የኢኮኖሚዋ ዋልታ ሆኖ የኖረውን ግብርናዋን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር መስራት ከጀመረች ቆይታለች፤ ይህን ተከትሎም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጭምር በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት ወደ ሀገሪቱ እየጎረፉ ናቸው። የጸጥታ ችግር በሚኖርባቸው ሀገሮች ዝር ማለት የማይፈልገው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በሀገሪቱ የታዩ ግጭቶች ብዙም አላስበረገጉትም፤ ይህ በራሱ ትልቅ አቅም ነው።

በወጪ ምርቶችም ቡና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ያለ የሀገሪቱ ሀብት ቢሆንም፣ አሁንም ገና ያልተነካና ብዙ ሊሰራበት የሚችል እምቅ ሀብት ነው ብሎ መናገር ይቻላል፤ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ቀጥለዋል። ስንዴንና አቮካዶን ለውጭ ገበያ መላክ ተጀምሯል፤ ልማቱም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ብዙም ያልተሰራበት፣ የኮንትሮባንዲስቶች ሲሳይ የሆነው የቁም እንስሳት ሀብት ከአፍሪካም ከዓለምም ከፍተኛው እምቅ ሀብት ነው።

በማዕድን ዘርፍም ሀገሪቱ ከፍተኛ እምቅ አቅም አላት፤ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ የኖረው ወርቅን በባህላዊ መንገድ የሚመረትበትን አጠናክሮ ከመቀጠል ባሻገር በኩባንያ ጭምር በስፋት ማምረት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በኩባንያዎች የሚደረገው የማምረት ስራ ሲጀመር በባህላዊ መንገድ ከሚመረተው ወርቅ አምስት እጥፍ በላይ የወርቅ ምርት ሊገኝ እንደሚችል እየተጠቆመ ይገኛል። የድንጋይ ከሰል ለሀገር ገበያ መመረት ጀምሯል፤ የብረት ማዕድን፣ የተፈጥሮ ጋዝ እምቅ አቅም እንዲሁም ሌሎች የከበሩ ማዕድናትም በሀገሪቱ ይገኛሉ።

በልማቱ በስፋት ሊሰማራ የሚችል የሰው ሀብት፣ ለየትኛውም ኢንቨስትመንት መሰማራት የሚያስችል ምቹ የአየር ንብረት፣ የወደብ ቅርበት አላት። በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥም ቢሆን ብሪክስን በመሰረቱት ሀገሮች መካከል ነው ሀገሪቱ የምትገኘው። እናም ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት ይዛ ነው ይህን ታላቅ ህብረት የተቀላቀለችው። አያሌ ሀገሮች ቋምጠውለት ያልተሳካላቸውን ይህን ሕብረት መቀላቀሏ አንድ ትልቅ ስኬት ነው፤ ብቻውን ግን ትርጉም አይኖረውም፤ ብሪክስን መቀላቀሉ ለሀገሪቱ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱ እንድ ትልቅ ነገር ሆኖ፣ ቀጣዩ ትልቅ ድል ሊሆን የሚችለው ሀገሪቱ ሕብረቱን በመቀላቀሏ ያገኘችውን እድል በሚገባ በመጠቀም የምታስመዘግበው ስኬት ይሆናል።

ሀገሪቱ በገቢና በወጪ ንግዱ፣ በኢንቨስትመንቱ፣ በቱሪዝሙ፣ በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግሩ፣ ወዘተ ከሕብረቱ ጋር በመስራት ልታገኛቸው የምትላቸው ቱሩፋቶች አያሌ ናቸው። እዚህ ሁሉ ላይ ለመስራት ግን ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግና ወደ ስራ መግባት ይጠበቅባታል።

የብሪክስ አባል ሀገሮችም ሆኑ በአጠቃላይ የሕብረቱ የገቢ ንግድ 3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በእነዚህ ሀገሮች ትልቅ የውጪ ንግድ ገበያ እንዳለ ከመረጃው መረዳት ይቻላል። ይህ በራሱ የወጪ ንግዷ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ይሆናል። በወጪ ንግድ ላይ በስፋት በመስራት የሀገሪቱ የግብርና ምርቶች ሰፊ የገበያ እድል እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። ቡና ፣ ስንዴ፣ የቅባት እህሎች፤ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳትና ስጋ ላይ ከተለመደው መንገድ ወጣ ባለ መልኩ በመሰራት የገበያ መዳረሻን በማስፋት፣ ጥራትን ያማከለ ስራ በመስራት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማስፋት ያስፈልጋል።

በተለይ የግብርናው ዘርፍ ምርቶች ሰፊ ገበያ የሚፈልጉ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ቡና አንዳንዴ እያጋጠመው ያለውን የገበያ ክፍተት ለመሙላትም ሆነ ሌላ ተጨማሪ ገበያ እንዲኖረው ለማድረግ ብሪክስ መልካም አጋጣሚ ነው።

ሀገሪቱ ከቁም እንስሳት ሀብት እየተጠቀመች ነው ማለት አይቻልም፤ ተጠቃሚዎቹ ኮንትሮባንዲስቶችና ጎረቤት ሀገሮች መሆናቸው እየተጠቆመ ነው፤ በቡናም ሆነ በቁም እንስሳት ምርቶቿ ከሀገሪቱ ይልቅ ገዝተዋት ወደ ተለያዩ ሀገሮች የሚልኩት፣ ለተለያዩ ኩባንያዎችና መደብሮች የሚያደርሱት ናቸው የበለጠ ተጠቃሚ እየሆኑ የሚገኙት።

ከዚህ መረዳት የሚቻለው ምርቶቹ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበትን መንገድ ማስፋት ላይም በትኩረት መስረት የሚያስፈልግ መሆኑን ነው። ምርቶቹን እንደ ወረዱ ከመላክ ባሻገር እሴት ጨምሮ መላክ የሚቻልበት መንገድ ላይ አተኩሮ መስራት ይኖርባታል። የኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ሀገር ቡና አዘጋጆች ቅመም መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም፣ ቡና ቆልተውና አሽገው የሚልኩ ኢትዮጵያውያን እንዲበራከቱ ማድረግ ላይ መሰራት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ስጋና የስጋ ውጤቶች፣ የቁም እንስሳት በመካከለኛው ምስራቅ ትልቅ ገበያ እንዳላቸው ይታወቃል። ገበያውን በመጠቀም በኩል ግን የሚፈለገውን ያህል ተሰርቷል አይባልም። የቁም እንስሳት ሀብቷ ለውጭ ገበያ ሲላክ የኖረው ተዟዙሮ ነው፤ ለእዚህ ደግሞ የኳረንቲን አለመኖር ይጠቀሳል። በዚህ የተነሳ ከብቶቹ ግብጽ ወይም ሌለ ጎረቤት ሀገር እንዲገቡ ተደርጎ ነው ለመካከለኛው ምስራቅ ገበያ ሲቀርቡ የኖሩት። አሁን በቀጥታ የምትልክበትን መንገድ ለመፍጠር መስራት የስራዎች ሁሉ ቅድሚያ ማድረግን ግዴታ ማድረግ ይገባል።

የወጪ ምርቶቿ የውጭ ምንዛሬ ምንጮቿ ናቸው። ለግብርናው ምርትና ምርታማነት ማደግ፣ ለኢንዱስትሪው ልማት እርሾም ግብአትም፣ ለመሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦች የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ለግብርናው ዘርፍ የወጪ ምርት ትኩረት መስጠት የግድ ይሆናል። ግብርናውን ለማዘመንና ትራንስፎርም ለማድረግ ለሚከናወነው ተግባር የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ላይ እንደሚሰራ መንግስት በተደጋጋሚ አረጋግጧል፤ ማዳበሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ይጠይቃል፤ ለእዚህ ሁሉ ደግሞ እንደ ግብርና ምርቶች ባሉ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ምርቶች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

ግብርናን ለአብነት አነሳን እንጂ በማዕድን ሀብት ላይም በትኩረት መስራትም ሌላው ጉዳይ ነው። የማዕድን ሀብቱን ከማልማት ባሻገር ከህገወጦች መዳፍ እንዲላቀቅ ማድረግ ላይ የተጀመሩ ጥረቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ማድረግም ይገባል። ሀገር ለልማቷ የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ እያስፈለጋት ባለበት በዚህ ወቅት ማዕድንን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች በኮንትሮባድ ወደ ውጭ መውሰድ ተገቢነት የሌለው ድርጊት ነው። ይህ ድርጊት እንዲቆም ማድረግና ግብይቱ ህጋዊ መንገድን እንዲከተል በማድረግ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ማዋል ላይ መሰራት ይኖርበታል።

ሀገሪቱ ብዙ ለማደግ ራዕይ የሰነቀች ናት፤ ለእዚህ ራዕይዋ እውን መሆን ያደጉት ሀገሮች ልምድና ተሞክሮ በእጅጉ ያስፈልጋታል፤ በተለይ የብሪክስ ሀገሮች እና የተለያዩ ድርጅቶቻቸው ፋይናንስና ባለሙያዎችም በእጅጉ ያስፈልጓታል። የእነዚህ ሀገሮች ባለሀብቶች በቀጥታ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰሩ ማድረግ ላይ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል። እነዚህ ኢንቨስተሮች ሲመጡ ቴክኖሎጂ፣ የውጭ ምንዛሬ፣ ገበያ ይዘው ነው የሚመጡት። ይህን አሟጦ ለመጠቀም መዘጋጀት የግድ ይሆናል።

ለእዚህ ሁሉ ደግሞ ከሀገሮች በተለይም ከበለጸጉትና በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ማስፋት፣ ማጠናከር፣ ከዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ እንዲሁም አካባቢያዊ ተቋማት ጋርም እንዲሁ የተጠናከረ ግንኙነት ማድረግ ይኖርባታል። ሀገሪቱ ለመልማት ያላት ጽኑ ፍላጎት ይህን ሁሉ ማድረግን ይጠይቃልና።

ሀገሪቱ ለመልማት ጽኑ ፍላጎትና መነሳሳት ያላት ብትሆንም በዓለም አቀፍና በአንዳንድ ወገኖች ጫናዎች ሳቢያ ወደፊት መራመድ ተቸግራ ቆይታለች። ያለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ እውነታዎች አንዳመለከቱት ኢንዱስትሪዎቿ፣ የግብርናው ዘርፏ ወዘተ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ፈተና ሆኖባታል።

ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከአደጉት ሀገሮች ብድርና እርዳታ ማግኘት መስፈርቱ ብዙ ነው፤ ምርቶቿን የምትሸጥበትን ገበያ የተከለከለችበት ሁኔታም አጋጥሟል፤ በገዛ ገንዘቧ ከዓለም አቀፉ ገበያ እንዳትገበይም ተደርጋ ነበር። ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገሮች ጋር በደጉ ቀን የመሰረተችው ግንኙነት ባያሻግራት ኖሮ ሊደርስባት ይችል የነበረው ስብራት በቀላሉ የሚጠገን ባልሆነ ነበር።

ጫናዎቹ እየቀነሱ ቢመጡም ትምህርት ሰጥተው ያለፉ ናቸው። ሀገሪቱ ወዳጆቿንና የልማት አጋሮቿን እንድታበረክትና አጠናክራ እንድትይዝ፣ ገበያዎቿን እንድታሰፋ የሚያስገድዱ ናቸው፤ ከዚህ አኳያ ብሪከስ ለኢትዮጵያ የደረሰ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል።

ሀገር አይደለችም ማንኛውም ሰው መውጫ ያስፈልገዋል፤ ሀገርም ወዳጆቿንና አጋሮቿን ብታሰፋና ብታበረክት መውጫዋን ነው የምታሰፋው። ብሪክስን መቀላቀሏ ሌላ ሰፊ መውጫ እንድታገኝ ያስችላታል። ሀገሪቱ ከብሪክስ መስራቾቹ ከቻይና፣ ከሩሲያና ከህንድ ጋር በተለያዩ መስኮች ግንኙነቶች አሏት፤ በቅርቡ አብረዋት ብሪክስን ከተቀላቀሉት ከተባበሩት አረብ ኤምሮቶችና ከሳውዲ አረቢያም ጋርም እንዲሁ ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት አላት። አዲሱ ግንኙነት ደግሞ የራሱን መንገድ ይዞ ይመጣልና በሚገባ መጠቀም ይገባል።

ሀገሪቱ ለመልማት እየታተረች የምትገኝ ናት። ልማቷ ገና በጅማሬ ላይ ያለ እንደመሆኑ ብዙ ኢንቨስትመንትና የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ ያስፈልጋታል። ለመልማት ብድርና እርዳታ ወሳኝ ግብአቶች መሆናቸው እሙን ነው። ለእዚህ ደግሞ የብሪክስ አባል ሀገሮች እንዲሁም የብሪክሱ አዲስ የልማት ባንክ ወሳኝ አጋር ሊሆኗት ይችላሉ።

ሀገሪቱ ጉዞዋ ወደ ኢንዱስትሪ መሆኑን አስመራ አስቀምጣለች፤ ኢንዱስትሪ ደግሞ የቴክኖሎጂና እውቀት እርሾን በእጅጉ ይፈልጋል። እነዚህ ሀገሮች ደግሞ በኢንዱስትሪው እንዴት እየጎለበቱ እንደመጡ ይታወቃሉ፤ ይህ ለሀገራችን ኢንዱስትሪ ትምህርት ቤት ይሆናል፤ ለኢንዱስትሪ የሚሆን ብዙ ቴክኖሎጂና እውቀት ያላቸው እንደመሆናቸውም፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የትም ሄደው መስራት የሚፈልጉ/በተለይ ቻይናውያንና ህንዶች/ ባለሀብቶችም ያሏቸው እንደመሆናቸው ኢትዮጵያ ይህን ሀብት ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ ይሆንላታል።

ሀገሪቱ ህብረቱን መቀላቀል መቻሏ በብዙ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተገኘ መሆኑ አንድ ትልቅ ስኬት ነው፤ ዋናው ስኬት ከዚህ ሕብረት ተጠቃሚ ለመሆን የሚከናነው ተግባርና የሚገኘው ውጤት ይሆናል። ይህን ለማድረግ ስራዎች አሁን መጀመር አለባቸው።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You