ፍሬያማነታቸው የታየው አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶች

ቱሪዝም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በጎ ተፅእኖ ከሚያሳድሩ አምስት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል ተመድቦ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል የማሳተፍ አቅም ያለው ከመሆኑም በላይ የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሌሎች ዘርፎች ተደምረው 90 በመቶ የሚሆነውን የሰው ኃይል ሲያሳትፉ፣ ቱሪዝም ብቻውን 10 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ነው።

የዘርፉ ተፅእኖ በዚህ ሳያበቃ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከመቅረፍ፣ የሀገር ገፅታን ከመገንባት አንፃር ድርሻው ግዙፍ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ውብ ተፈጥሮ፣ ምድረ ቀደምትነት፣ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ የመስህብ ሥፍራዎችን በማስተዋወቅ የራሷ ብዝሀ ባህል፣ ቋንቋ፣ ፊደል፣ ቀደምት የሥነ ጽሑፍ እና የሕንፃ ጥበብ ባለቤት እንደሆነች የማሳየትና ከዚያም ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑንም በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ከላይ ለማንሳት በሞከርናቸው ምክንያቶች መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ራሱን በቻለ መልኩ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ እንዲዋቀር አድርጎ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል። በተለይ በዘርፉ አዲስ እሳቤ በማምጣት የመዳረሻ ልማት ግንባታዎችን በማከናወን ላይም ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያና በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተተገበሩና እየተተገበሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ለእዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። ፕሮጀክቶቹ ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

እነዚህ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ፍሬያቸው የታየ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ የገነቡ፣ ሙያና ሙያተኛን ያገናኙ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የቱሪዝም እሳቤን በፍጥነት እየቀየሩ የመጡ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራንም ይናገራሉ። ወደ ሥራ የገቡት የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች፣ ግንባታቸው እየተካሄደ ያለው የገበታ ለሀገር /የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ፣ የጎርጎራ የባህር ዳርቻ ፕሮጀክት፣ የኮይሻ/ ፕሮጀክቶችን የመሳሰሉ ማራኪ ገፅታ ያላቸው መዳረሻዎች እንዲሁም በገበታ ለትውልድ በቀጣይ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ በዘርፉ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚኖር ምሁራኑ ይጠቁማሉ። ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገቡት በአዲስ አበባ የሚገኙት እንጦጦ፣ አንድነት፣ ወንድማማቾች አደባባይ እና በዳውሮ ዞን የሚገኘው ሃላላ ኬላ የመሳሰሉት የመስህብ ሥፍራዎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ በገቢ፣ በሥራ ፈጠራ፣ የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመርና ረገድ ተፅኗቸው ጉልህ እንደሆነ ይነገራል።

አቶ ይታሰብ ስዩም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው ኢትዮጵያ በጣም በርካታ የቱሪዝም ሀብት ያላት ሀገር እንደሆነች ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ መዳረሻዎች ደግሞ ተጨማሪ እሴት እንደሆኑና ዘርፉን እንዳነቃቁት ይገልፃሉ። በተለይ ኬንያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመዝናናት፣ ለሠርግና ልዩ በዓላትን ለማክበር ምርጫ አድርገው የሚሄዱ ቱሪስቶችን የሚስብና አዲስ እይታን ለኢትዮጵያ የሚያጎናፅፍ ልማት እየተከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ አካሄድ ቀደም ካለው የቱሪዝም እሳቤ የወጣና ተጨማሪ አማራጭን የሚያስቀምጥ እንደሆነም ይገልፃሉ።

“በቅርቡ ግንባታው የተጠናቀቀው የሀላላ ኬላ ሪዞርትን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ጎብኚዎች ለሠርግ ‘ሀኒሙን’ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም ምርጫቸው ሊያደርጉት የሚያስችል አቅም ያለው ነው” የሚሉት አቶ ይታሰብ፤ የጎርጎራ፣ ወንጪና መሰል ፕሮጀክቶችም ይህንን የመሰለ አቅም በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እንደሚፈጥሩ ይናገራሉ። በተለይ በአዲስ አበባ ሥራቸውን የጀመሩት ፓርኮች በዚህ ረገድ መልካም ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ይገልፃሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደሚያጓጉዝ የሚገልፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በትራንዚት ወይም “በስቶፕ ኦቨር” ቱሪዝም ከተማ ውስጥ የሚገኙ መስህቦችን ፓርኮችን የመጎብኘት እድሉን እንደሚፈጥር ያነሳሉ። ከዚህ አኳያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት መዳረሻዎች ግዙፍ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው እና ለጎብኚዎች አገልግሎት ምቹ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። እንጦጦ፣ አንድነት፣ የቤተ መንግሥት ታሪካዊ ቅርሶች እና መሰል መዳረሻዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑም ይናገራሉ።

ቱሪዝም በባህሪው ከፍተኛ የሥራ እድል የሚፈጥር ዘርፍ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ይታሰብ፣ እነዚህ ተገንብተው ሥራ የጀመሩ የቱሪዝም ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከሥራ እድል ፈጠራ አንፃር አዎንታዊ ተፅእኖ መፍጠር መቻላቸውንም ይገልፃሉ። በቀጣይ ወደ ሥራ የሚገቡት እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻና መሰል የቱሪዝሙ ዘርፍ አዳዲስ መዳረሻዎች በተመሳሳይ ለበርካታ ሰዎች በተጨባጭ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ያስረዳሉ።

“ወዳጅነት ፓርክን በምሳሌነት ብንወስድ በር ላይ ትኬት ከሚቆርጡት ጀምሮ በመስተንግዶ፣ በምግብና መጠጥ፣ በፎቶና በሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ሰዎች አሉ” የሚሉት አቶ ይታሰብ፣ እነዚህም አዳዲስ የተገነቡት የቱሪዝም ዘርፍ ፕሮጀክቶች ያመጡት ለውጥ ማሳያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልፃሉ። በተለይ በአዲስ አበባ አዳዲስ የመዝናኛና የጉብኝት ባህል እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።

አቶ ይታሰብ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻ ከመገንባት ባሻገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ሰዓት በተለይ ከአገልግሎት ሰጪዎች የላቀ ሥነ ምግባር እንደሚጠበቅ ይናገራሉ። ይህ ሲሆን ከተገነቡት የመዳረሻ ልማቶች ጋር ተደምሮ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምትፈልገውን ስኬት እንድታስመዘግብ እንደሚረዳት ይናገራሉ። አንድ ጎብኚ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚሄድበት ወቅት ኢትዮጵያዊ የሆነና ወጥነት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ለማምጣት ተከታታይነት ያለው የማሻሻል ሥራዎች እንደሚጠብቁም ይጠቁማሉ።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊና መምህር የሆነው አቶ ዐብይ ንጉሴ፣ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ አድርጎ በነበረበት ወቅት አዳዲስ ተገንብተው ሥራ የጀመሩ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች ፈጣን ለውጥ የታየባቸውና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ መሆኑን ገልጿል።

“በእንጦጦ የመዝናኛ ፓርክ ውስጥ አዲስ የመስህብና የቱሪዝም መዳረሻ ከመፈጠሩም በተጨማሪ ለሥራ እድል ፈጠራው ትልቅ ድርሻ ወስዷል” ያለው የቱሪዝም መምህሩ ዐብይ፤ በተመሳሳይ በከተማዋ የተገነቡትና ታድሰው ለእይታ የበቁት የቱሪዝም መዳረሻዎች ቱሪዝም ለኢኮኖሚው ያለውን ጉልህ አበርክቶ በምሳሌነት ማሳየት የቻሉ መሆናቸውን ይገልፃል። ይህም የመስህብ ሥፍራዎች፣ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ቅርሶችና መሰል መዳረሻዎች የቱሪዝም ምርት መሆን ሲችሉና በገበያው ላይ ሲቀርቡ በማህበረሰቡ ላይ በቀጥታ የሚፈጥሩትን በጎ ውጤት ማየት እንድንችል ያደርገናል ይላል።

 “የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎችን ስንሰራ የምናወጣውን ከፍተኛ ወጪ መመልከት የለብንም” የሚለው ዐብይ ንጉሴ፤ ከፍተኛ ወጪም ቢሆን ትክክለኛው ልማት ላይ ካዋልነው የቱሪዝም ዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጪዎችን የሚመልስና ተጨማሪ የሀገር ሃብትን መፍጠር እንደሚችልም ይናገራል። እንደ ምሳሌም ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው የተሰሩት የወዳጅነት ፓርክ፣ ቤተመንግሥት፣ እንጦጦ ፓርክና መሰል የቅርብ ጊዜ መዳረሻዎች በፍጥነት በብዙ ሕዝብ እየተጎበኙና ገቢ እያስገቡ እንደሆነ በምሳሌነት ይጠቅሳል።

ሥራ የጀመሩ መዳረሻዎች

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በገበታ ለሸገር የተገነቡና በገበታ ለሀገር ስር እየተገነቡ ካሉ መዳረሻዎች ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ወደ ሥራ የገቡ ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ በታሪካዊው እንጦጦ ተራራ ላይ የሚገኘው ፓርክ አንዱ ሲሆን በውስጡም ከሥነ ምህዳር ጋር የተዋሀዱ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይገኙበታል። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች በሥፍራው ሲገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን የመመልከት እድሉን ከማግኘታቸውም ባሻገር ዘመኑ የሚፈቅደውን አገልግሎትና የመዝናኛ ምርጫ ይቀርብላቸዋል።

ይህን ሥፍራ ልዩ የሚያደርገው በአካባቢው ዝቅተኛ ገቢ ባለው ሥራ ላይ ረዘም ላለ ዓመት የቆዩ እናቶች ፕሮጀክቱ መምጣቱን ተከትሎ ሕይወታቸውን የሚቀይር የሥራ እድል መፍጠሩ ነው። ሌላው በከተማዋ አሉ የሚባሉ ሪዞርቶች፣ እና ታዋቂ አገልግሎት ሰጪዎች በአንድነት በሥፍራው ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ። እንጦጦ ፓርክም በፍጥነት ለምተው ወደ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከገቡ ፕሮጀክቶች ውስጥ ቀዳሚው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሌላው በአዲስ አበባ የሚገኘውና ”የገበታ ለሸገር” ፕሮጀክት አካል የሆነው የወዳጅነት አደባባይ ነው። በዚህ ሥፍራ ተፈጥሮ፣ ልዩ ልዩ የመዝናኛ አገልግሎቶች፣ ለእይታ ምቹ የሆነ መልክአ ምድር በአንድነት ይገኛል። በፓርኩ በርካታ ጎብኚዎች የሚገኙበት ከመሆኑ ባሻገር ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ሠርጋቸውን ለማከናወን የፎቶ ፕሮግራም በቦታው የሚያደርጉበት ሆኗል። በጊዜያዊና በቋሚነት በወዳጅነት ፓርክ ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአዲስ አበባ ከተገነቡት እንጦጦ፣ ወዳጅነት ፓርክ ብሎም ከአንድነት ፓርክ ቀጥሎ በተለይም ለታዳጊዎችና ልጆች ትኩረት ሰጥቶ የተገነባው የወዳጅነት ፓርክ ሁለተኛው ፕሮጀክት የሚጠቀስ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ ከመሆኗ አኳያ ሁሉንም ያካተተ የመዝናኛ ሥፍራ ትሻለች። ይህ የወዳጅነት ቁጥር ሁለት ፓርክ ታዳጊዎችን መሠረት አድርጎ መሠራቱ ይህንኑ የሚያሳይ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ ፓርኩ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት ከሆነበት እለት አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ሥፍራውን እየጎበኙት ናቸው። ፓርኩ ሕፃናት በአንድ ቦታ ሁሉንም ዓይነት መጫወቻዎች የሚያገኙበት ጥሩ የመዝናኛ አማራጭ ነው። ሥፍራው ቱሪዝም የሚጠይቀውን አካታችነት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ የሚያመላክቱ በርካታ ይዘቶች አሉት።

ሃላላ ኬላ ሪዞርት በገበታ ለሀገር በኮይሻ ፕሮጀክት ውስጥ እንዲገነቡ እቅድ ከተያዘላቸው መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በፍጥነት ግንባታቸው ተጠናቆ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከተቀላቀሉት ሪዞርቶች መካከልም ነው። ይህ ሥፍራ ከማራኪነቱና ለእይታ አስደናቂ ከመሆኑ አንፃር ወደ ሥፍራው ለማቅናት ከውጭም ይሁን ከሀገር ውስጥ ለጉብኝት በሚሄዱ ጎብኚዎች ተመራጭ እየሆነ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥም የቱሪስት ፍሰቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ተወዳጅነት በማትረፍም የኢትዮጵያን የሆስፒታሊቲ ዘርፍ ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በጥቅሉ በገበታ ለሸገር መርሃ ግብር አንድነት፣ ወዳጅነትና እንጦጦ ፓርክ ቱሪስቶችን በከፍተኛ መጠን እያስተናገዱ ይገኛሉ። ከገበታ ለሀገር ወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሀላላ ኬላ ሪዞርት ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ገብቷል። የጎርጎራ ፕሮጀክትም በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያም የቱሪዝም ብዝሀ ሃብት መገኛ፤ የተፈጥሮ፣ የባህልና ታሪክ ባለቤት ከመሆኗ ባሻገር በአዳዲስ የቱሪዝም እሳቤዎችና እሴቶች እመርታ እያሳየች እንደሆነ የሚያመለክቱ ናቸው። በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ፍሬ ማሳየት የቻሉ ፕሮጀክቶች ባለቤት እንደሆነች መገንዘብ የሚያስችል ነው።

ዳግም ከበደ

 አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You