የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ የእንቁጣጣሽን ዳና ተከትሎ ከአደይ አበባዎቹ መሃል እያሳለጠ በኋላኛዎቹ የዓውዳ ዓመት ትውስታዎች ላይ አርፋል። በተለያዩ መንግሥታት የሥልጣን ዘመን በተለይም ደግሞ በመጀመሪያው የሥራ ዓመታቸው ልክ በዛሬው ቀን ዓውዳ ዓመቱን አስመልክቶ በአዲስ ዘመን ድሮ ምን ምን ጉዳዮች ተካተው ይሆን… እንዴትስ አከበሩት… እድለኛው ትውልድ በሺህ ዓመት አንዴ ሊገጥም የሚችለውን በሚሌኒየም የታጀበውን አዲስ ዓመት ደርሶ ለማክበር በቃ… ሚሌኒየምና እንቁጣጣሽስ እንደምን አሸብርቀው ነበር… ሁሉም የመስከረም 1 ትዝታዎች ናቸው።
የዘመን መለወጫ በዓል ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል
የአዲሱ ዓመት የዘመን መለወጫና ኤርትራ ከእናት ሀገርዋ የተዋሐደችበት ዕለት ዛሬ ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል።
ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዋና የእልፍኝ አስከልካይ ጽሕፈት ቤት ስለ በዓሉ ባወጣው ፕሮግራም፤ መሠረት የዘመን መለወጫን በዓል የሚያበስር መድፍ 21 ጊዜ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ተተኩሷል።
ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑ የውጭ ሀገር መንግሥታት እንደራሴዎችና ታላላቅ የውጭ ሀገር ሰዎች ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሔደው በክብር መዝገብ ላይ ከፈረሙ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።
(አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 1966ዓ.ም)
ዋና አዘጋጅ በዓሉ ግርማ
የአዲሱ ዓመት መንፈስ
ምን ጊዜም ቢሆን አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሲተካ አዲስ መንፈስ ይዞ መምጣቱ አይቀርም ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር ሁሉም በየቤቱ አዲስ ውጥን ያወጣል። ያንን ውጥን ሥራ ላይ ለማዋል እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ቃል ይገባል። ግን ለራሳቸው የገቡትን ቃል ከፍጻሜ የሚያደርሱት ከብዙዎቹ ጥቂቶች የታደሉና መንፈሰ ጠንካራ የሆኑት ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “ይህን እሠራለሁ፤ ይህን አደርጋለሁ” ብሎ ተስፋ ማድረግ ከሰው ልጅ ሊለይ አይችልም። የሰው ልጅ ሕልውና መሠረቱ ተስፋ ነው። ያለ ተስፋ የምትንቀሳቀስ ሕልውና በባዶ ሜዳ ከሚጮህ ናስ ወይም ከሚንሿሿ ጽናጽል አትሻልምና! ስለዚህ አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ እንቀበለው።
(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1966ዓ.ም)
ፕሬዚዳንት መለስ ለኢትዮጵያ ሕዝብች የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ
አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝቦች አዲሱ ዓመት የሰላምና የደስታ ዓመት እንዲሆን በጎ ምኞታቻውን በመግለጽ ባለፈው ረቡዕ መልዕክታቸውን አስተላለፉ።
…..
የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሀገራችንን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምራት፤ ሕዝቦች የመብታቸው ከፍተኛ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ሳያሰልስ እንደሚሰራ አመልክተው፤ በሕዝቦችና በሽግግር መንግሥቱ ትብብር በእርግጥ መጪው ዓመት የበለጠ የሰላምና የተሻለ የደስታ ዓመት እንደሚሆን በጎ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1984ዓ.ም)
ለአዲስ አበባ ሕዝብ የኪነት ዝግጅት ቀረበ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ባለፈው ሐሙስ (ኢሕአዴግ) ሁለት የኪነት ቡድኖች የአዲሱን ዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝግጅቶቻቸውን ለአዲስ አበባ ሕዝብ አቀረቡ።
“የኢሕአዴግና የኢሕአዴግ ሠራዊት” ተብለው የሚጠሩት የባሕል የኪነት ቡድኖች በቀድሞው የጉባኤ አዳራሽ ያቀረቡዋቸው ዝግጅቶች የልዩ ልዩ ብሔረሰቦችን ባሕልና ወግ እንዲሁም የወቅቱን የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ ናቸው።
( አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1984ዓ.ም)
አዲሱን ዓመት የምንቀበለው በመንታ ስሜት ሆነን ነው
እነሆ አዲሱን ዓመት እያከበርን ነው። ሁሉም ባለው አቅም በዓሉን ለማክበር ሲዘጋጅ እንደነበር እሙን ነው። አዲሱ ዓመት የሰላም የብልጽግና እንዲሆን በመመኘት በዓሉ ይከበራል። የጎረቤቶቼን ጤናና ብልጽግና የማይመኝ የለም።
…….
አምና ለራሳችንና ለሀገራችን ሰላምን ተመኝተን ነበር። ነገር ግን ሰላም በአንድ ወገን ምኞት ብቻ ዕውን አይሆንም። አምና የተመኘነውን ነገር ዘንድሮ ስናስበው ብዙዎቻችን እናዝናለን። ሀገራችንን ካለፉት ዓመታት የበለጠ ከችግር ለመላቀቅ አንድ ርምጃ ወደፊት እንድትል የተመኙ ብዙዎች ቢሆኑም በቅርቡ በተፈጸመብን የእብሪት ወረራ የአምናውን መልካም አስተሳሰባችንን በመጠኑ አሻክሮታል።
የሻዕቢያ መንግሥት የሀገራችንን ሉዓላዊነት በመድፈሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጣቸው ጨምሯል። አምና ዘመኑ የሰላምና የጤና እንዲሆን የተመኙት በጎረቤት አደፍራሽ በመሰናከሉ ሰላማቸውን ለመመለስ የዘንድሮውን ዓመት የሚያከብሩት በምኞት ብቻ ሳይሆን በተባበረ ክንዳቸው ክብራቸውን ለማስጠበቅ ቁርጠኝነታቸውን በማስታወቅ ነው።
የሻዕቢያ መንግሥት በፈጸመው የእብሪት ወረራ በሰላማችን ላይ አፍራሽ ተጽዕኖ አሳድሯል። የስቃይ ሰለባ ሆነው የቆዩትና የሀገራቸውን ምድር የረገጡ በተለያየ የመጠለያ ሠፈሮች ይገኛሉ። እነሱ አምና አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ “በሰላም ለሀገሬ ከበቃሁኝ…” በማለት ነበር። ለሀገራቸው ምድር ቢበቁም ሰላምን አላገኙም። በሻዕቢያ ወታደሮች የእብሪት ተግባር ተሰቃይተዋል።
አምና በዓሉን ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደስታ በቤታቸው ያከብሩ ነበር። ዛሬ ግን ከቤት ንብረታቸው ስለተፈናቀሉ በመጠለያ ሠፈር ውስጥ ለማክበር ተገደዋል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1991ዓ.ም)
ዘመን መለወጫን ከግንባር ሠራዊታችን ጋራ
ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት አዲስ የነበረው 1990 ዓ.ም በአሮጌነት ተፈርጇል። በአሮጌው ዓመት ውስጥ ተጸንሶ አድጎ ለመወለድ የበቃው 1991 ደግሞ አዲስ፣ ለጋ ለግላጋ ተብሏል። የዕድገት ሕግ ሆኖ በአሮጌነት የተፈረጀውን 1990ን ኢትዮጵያዊያን ሲቀበሉት ምኞታቸውንና ተስፋቸውን ለማደናቀፍ ይኖራል ብለው ባለመገመታቸውም ከዚህ የተለየ አጀንዳም አልነበራቸውም።
……
በ1990 ዓ.ም መቋጫ ላይ በሻዕቢያ የተፈጸመው አሳፋሪና ዘግናኝ ድርጊት አሁን ወደተቀበልነው አዲስ ዓመትም ተሸጋግሯል።
……..
የመከላከያ ሠራዊቱ ለሕዝቡ ሰላምና ልማት ሲል በመጀመሪያ ረድፍ ተሰልፎ ወራሪውን በመመከቱና ለሻዕቢያም ፍርሃቱ በመሆኑ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል አዲሱ ዓመት በደስታ እየተከበረ ነው። በእሱ የደምና የሕይወት መስዋዕትነት ሕዝቦች የአዲሱ ዓመት ተቋዳሽ ሆነዋል።
…..
ከዚህ በፊት ለሠራዊታችን ምግብ፣ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ ከማቅረብ አልፎ ምሽግ በመቆፈር የተሳተፉት የሽራሮ አካባቢ ነዋሪዎችም ቢሆኑ ማልደው በመነሳት ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ከሠራዊቱ ጋር በዓሉን ለማክበር ታድመዋል። ከሠራዊቱ ጋር ያላቸውን አንድነት ለመግለጽም ተቀላቅለው ተቀምጠዋል። ነጫጭ የሀገር ልብስ ለብሰው ከሠራዊቱ ጎን የተቀመጡት የአካባቢው ሴቶችም ነጫጭ እርግቦች ይመስላሉ።
……..
ከአዲግራት እስከ ዛላአንበሳ ባሉት መንደሮች በዋሻውና በየዋርካው ቄጤማ ተጎዝጉዞ፣ ዳቦ(ሕብስት) ቆርሶ አውዳ ዓመቱን አውዳ ዓመት አስመስሎታል። በየቤቱ ዞሮ ባይጠራም ነዋሪው ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆኗል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1991ዓ.ም)
ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች! እንኳን ለሚሌኒየሙ በዓል በሰላም አደራሳችሁ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አሸጋገራችሁ!
በሺህ ዓመት አንድ ጊዜ የሚገኝ በዓል ለማክበር መቻል በጣም የተለየ ዕድል ነው። እናም ይህን ታሪካዊ በዓል ለማክበር የታደለውን ይህን ትውልድ በድጋሚ እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ። እንኳን አብሮ ደስ አለን።
የሺህ ዓመታትን የታሪክ ምዕራፍ ዘግተን አዲስ የሺህ ዓመት ምዕራፍ ለመጀመር እነሆ የሰዓታት ዕድሜ ብቻ ቀርተውናል። በዚህ ታሪካዊ ሽግግር ላይ ሆኜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለማስተላለፍ በመቻሌ ትልቅ ኩራት የሚሰማኝ መሆኑን አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ።
…….
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአዲሱ ሚሌኒየም ክብረ በዓል በደማቅ ሥነ ሥርዓትና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ማክበር ከጀመርን ወራት ተቆጥረዋል። ሁሉም እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ከአሁን በኋላ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያህል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2000ዓ.ም)
ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሚሌኒየም በዓልን አስመልክተው ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው
የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓልን አስመልክቶ የሚያቀርቡዋቸው ዘገባዎች እንደቀጠለ ነው።
የቢቢሲ ዘጋቢ ኤልሳቤት ብላንት ከአዲስ አበባ ከትላንት በስቲያ ባስተላለፈችው ዘገባ፤ የራሳቸውን የጊዜ አቆጣጠር ባለቤት ከሆኑት ኢትዮጵያውያን ጋር የሀገሬውን ሚሌኒየም በማክበሬ እጅግ የወጣትነት ስሜት እየተሰማኝ ነው።
በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አቅራቢያ በተገነባው ግዙፍ አዳራሽ በሚካሄደው የሙዚቃ ትርዒት ላይ ብላክ አይስ ፒስ የተሰኙት ታዋቂ የሙዚቃ ቡድን አባላት ይገኛሉ በማለት የቢቢሲ ዘጋቢ ባስተላለፈችው ዘገባ አመልክታለች።
( አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2000ዓ.ም)
ዓይን ልመና
“እኔ ተናግሬያለሁ…ብትሰጡኝ ይሻላችኋል። አምስትም አስርም ያላችሁን ጣሉልኝ! ተናግሬያለሁ የቀረው ጊዜ አጭር ነው” መሸት ሲል ፌርማታ ጥግ ተቀምጦ አላፊ አግዳሚውን የሚለምነው የኔ ቢጤ ድምጹን ከፍ አድርጎ ይጮሀል። የሰሞኑ አለማመኑ ለየት ያለ መሆኑን ሰምቻለሁ። ራቅ ብዬ ቆሜ የሚለምነውን ማዳመጥ ቀጠልኩ።
“በኋላ ይጨንቃችኋል! ከቀናት በኋላ እያንዳንድሽ ሳንቲምሽን ዘርዝረሽ ተመጽዋች ፍለጋ ትዞሪያለሽ። እዚህ ቁጭ ብዬ ያንቺን አስር አምስት አለቅምም። ጊዜው አጭር ነው። በዕድሉ ተጠቀሚ። ይሄኔ ስጪኝና ልመርቅሽ። ተመራርቀን እንሰነባበት። ደርሷል። ሚሌኒየም ደርሷል። ያን ጊዜ ሳንቲምሽን ዘርዝረሽ ብትመጪ አታገኚኝም ተናግሬያለሁ። ልመና ሊያበቃ ነው በሚሌኒየሙ አታገኚኝም” አላፊ አግዳሚውን እያየ የሚያነበንበው የኔ ቢጤ ውስጥ አንድ የተስፋ ቅላጼ አደመጥኩ። መጪው ሚሌኒየም በኔ ቢጤው ልብ ውስጥ የፈጠረው ስሜት ልብ የሚስብ ሆኖ አገኘሁት።
በሚሌኒየሙ የመጀመሪያ ቀን 469 የሚሆኑ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን አገኙ
በሚሌኒየሙ የመጀመሪያ ቀን በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳርና በመቀሌ በተደረገ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ሕክምና 469 የሚሆኑ ማየት የተሳናቸው ወገኖች የዓይን ብርሃናቸው እንዲገለጥ መደረጉን የላየንስ ክለብ አስታወቀ።
…..
በዕለቱ በአዲስ አበባ በራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረገላቸው ወገኖች ከሕክምናው በኋላ የችግኝ ተከላ ማካሔዳቸውን ጠቁመዋል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2000ዓ.ም)
ከዲያስፖራው አንደበት
“ከ17 ዓመታት የአሜሪካን ቆይታ በኋላ ወደ እናት ሀገሬ ምድር ተመልሻለሁ። የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን አፈርዋንም እወደዋለሁ። አዲሱንም ሚሌኒየም በምወደው አፈር ከምወደው ሕዝብ ጋር ለማክበር መጥቻለሁ። ”
አቶ ሱፌ ሙሳ አደም
ከአሜሪካ-ሚኒሶታ
“አሜሪካ ለእረፍት ነበር የሄድኩት። ሚሌኒየሙን ለማክበር ከልጆቼ ጋር ወደ ሀገሬ ተመልሻለሁ። ሀገሬ ሰላም ሁና ስላገኘኋት በጣም ደስ ብሎኛል። ”
ወ/ሮ ላቀች ፈራጋ
ከአሜሪካ
“በአሜሪካ እያለሁ ነበር ስለ አዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የሰማሁት። አጋጣሚውን በመጠቀም የሚሊኒየም አከባበሩን ለማየትና በወላጅ አልባ ሕጻናት ዙሪያ የዕርዳታ ሥራ ለመሥራት ነው የመጣሁት። በዚህ ሰዓት እየተደረገ ያለው አቀባበለም በጣም ደስ ብሎኛል። ኢትዮጵያዊያን እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ። ”
ጄሲካ
ከኖርዝ ካሮሊና
( አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2000ዓ.ም)
የእንቁጣጣሽ መልካም ምኞት መግለጫ
አሮጌ ዓመት አልቆ አዲስ መጣላችሁ፣
ማመስገነን ይገባል ለዚህ ላበቃችሁ።
መንስዔ በማድረግ ይህን አጋጣሚ፣
ዓመቱም እንዲሆን በጣሙን ተስማሚ።
ስናቀርብላችሁ መልካሙን ምኞት፣
እናንተም እንካችሁ የባንክን መልእክት።
አዲስ አበባ
በአዲስ አበባችን በአፍሪቃ መዲና
ኑሮን እያሻሻልኩ ምጣኔን እማስጠና
አዲስ አበባ ባንክ ነኝ የዕድገት ሁሉ ፋና።
………
አሥመራ
ባለኝ ሰፊ እቅድ ለወገን ልሠራ
ውጤቱ ያበራል ከመሐል አሥመራ
ንግድና ቁጠባም አርጎ ግሥጋሴ
በፈጸምኩት ድርሻ ረክቷል መንፈሴ።
ከረን
ሁሉን ለማዳረስ ታጥቄ በቅን
ደግሞም እገኛለሁ ከመሐል ከረን
የሕዝቡ አቆጣጠብ የኑሮው ዕድገት
በውድድር አንጻር ወደር ታጣለት።
አሰብ
ሙቀት ሳይበግረኝ ወርጄ አሰብ
አገለግላለሁ ሳላስገባ አሳብ።
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1984ዓ.ም
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም