የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተከናወኑ የብሔራዊ ደህንነት ስኬታማ ስራዎችን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች የገመገመ ሲሆን የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡
ኮሚቴው የሀገራችንን ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎችን በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን ለአብነትም በውጭ ሀገራት የነበሩ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የነበረው ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ግንኙነት መስተካከሉ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን ግምግሟል፡፡ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች መካሄድ መጀመራቸው፤ የደህንነት ተቋም አመራሮች ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ የሚያስችል የአመራር ለውጥ መደረጉን በጠንካራ ጎን የገመገመው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመከላከያ ሠራዊት ባለፈው አንድ ዓመት ጠንካራ ሪፎርም ካደረጉ ግንባር ቀደም ተቋማት አንዱ እንደሆነና ከአደረጃጀቱ ጀምሮ አጠቃላይ የመከላከያ መዋቅሩን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንም አይቷል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት በአጠቃላይ በጸጥታው ዘርፍ ጠንካራ ስራዎች ቢከናወኑም በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸው ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ተግዳሮቶቹ በዋናነት ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከኢ- መደበኛ አደረጃጀቶች ወይም ደቦዎች፤ ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ከማህበራዊ ሚድያ ሀሰተኛ ዜናዎች ተጽዕኖ ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ተመልክቷል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የደህንነት ስጋት ምክንያት መሆናቸውንም አስምሮበታል፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
በዚህም ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን አፅንኦት በመስጠት የዜጎችን የሠላም ዋስትና የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ መረባረብ እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፏል። ለደህንነት ተግዳሮቶች መነሻ ወይም ችግሩን በአጭር ጊዜ እንዳይቀረፍ ከማድረግ አንጻር ዋነኛው ችግር ያለው ከፖለቲካ ሥራ ጋር የተተያያዘ እንደሆነ በመለየት የደህንነት ሥራው ከፖለቲካ ሥራው ጋር ጎን ለጎን ተያይዞ እንዲሰራና በአንዱ የጎደለው በሌላው እየተሞላ አስተማማኝ ሰላም በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲከናወን አቅጣጫ አስቀምጧል።
ከአንዳንድ የአስተዳደር ወሰኖች ጋር በተያያዘ ሲስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች ያሳዩ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ክልሎች ከክልሎች እና ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ሃይሎች ቅኝትና አወቃቀር በሚመለከት የሚስተዋሉ ችግሮች በህገ መንግስቱ መሰረት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እንዲሰራ ኮሚቴው ወስኗል። የጸጥታ ኃይሎች ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ የዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ለማስከበር በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የየአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር እንዲሰሩ ያሳሰበው ኮሚቴው ሰላም ወዳዱ ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በንቃት እንዲረባረብ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ሁለንተናዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስምሮበታል፡፡
ኮሚቴው የደህንነት ስጋት ምንጮችን በዝርዝር በመለየት ተግዳሮቶቹን በአጭር ጊዜ በመፍታት የተሟላ ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ዝርዝር ተግባራት ላይ ተወያይቶ የአፈጻጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የኢህአዴግ ም/ ቤት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011
በአስቴር ኤልያስ