አዲስ አበባ፡- ዛሬ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በይፋ የሚከፈተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሳምንትና ፎረም የአገሪቱ ከተሞች ራሳቸውን ለኢንቨስትመንት ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተገለፀ፡፡
አዘጋጁ የኢትዮጵያ ሲቲ ማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም የዝግጅቱ ስፖንሰር ከሆነው ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሳምንትና ፎረም ዝግጅትን አስመልክቶ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኩባንያው ጀነራል ማናጀር አቶ ኦሃድ ቤናሚ እንደተናገሩት፤የፎረሙ መሰረታዊ ዓላማ በአገሪቱ ውስጥ እያደገ የመጣውን ኢንቨስትመንት ዘርፍ የበለጠ ለማበረታታት ነው፡፡
በፎረሙ ውስጥ ደግሞ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ አማራጮችን፣ መፍትሄዎችንና እንዲሁም በአዳዲስ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ህብረተሰቡም ግንዛቤ የሚጨብጥበት መድረክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ በበኩላቸው የኢንቨስትመንት ፎረሙ ለኢንቨስትመንቱ ማደግ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረው የወጪ ምርትና ምርማነትን በአይነትም ሆነ በመጠን ለማሳደግ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥም ድርሻው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ የውጭ ምንዛሪ ከማሳደግና የአገራትን የንግድ ሚዛን የተሻለ በማድረጉ በኩልም ከፍ ያለ አስተዋፅኦው እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ ያለው ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ትኩረትን በመሳብዋ በቅርብ ጊዜ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ አምስት የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና በተለይም በቅርቡ እንደ እነ ቮልክስዋገን እና ሌሎችም ኩባንያች በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተው፤ እንደ ዛሬ አይነቱ ፎረም ደግሞ ኢንቨስትመንቱን በማስተዋወቁ ረገድ ሰፊ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታመን ገልፀዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ፎረም ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ሆነ አዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጋራ በመሆን ከአዘጋጆቹ ጋር እንደሚሰሩ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ እንዲህ አይነት ለአገር ጠቃሚ ጉዳዮች መደረጋቸውም ለገጽታ ግንባታ መልካም መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ሃያ ያህል ከተሞችና 14 ያህል ኢንቨስተሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011
በአስቴር ኤልያስ