አዲስ ዓመት መጣ፡፡ እንደተለመደውም በአዲስ መልክ አዲስ ተስፋ ልንሰንቅ ተዘጋጅተናል። መቼም የሰው ልጅን የሚያኖረው ተስፋ ነውና ተስፋ ማድረግ መልካም ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከተስፋም አልፈው እቅድ ማቀድ ሁሉ ከጀመሩ ሰንብተዋል። እሱም መልካም ነው፡፡ ማቀድ የመሰልጠን ምልክት ነው፡፡ በጨበጣ ከመወዛወዝ ማቀድ የተሻለ ነው፡፡ ስለዚህም የዛሬው ጉዳያችን በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡
የመጀመሪያው ጉዳይ ማቀድ ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ ለማቀድ ብቻ ስለሚያቅዱ ሰዎች እንነጋገር። አንዳንድ ሰው የሚያቅደው ለማቀድ ያህል ነው፡፡ በቃ አለ አይደል የሆነ በሕይወቱ ላይ ቀልድ የማያውቅ ቆፍጣና ሰው ለመመምሰል፡፡ ከዚያ ውጭ ለምን እንዳቀዱ ፤ ምን እንዳቀዱ ፤ እንዴት እንደሚያሳኩት ምናምን አያውቁትም፡፡ ተገድደው ያቀዱት ነው የሚመስሉት፡፡ እቅዳቸውን አያውቁትም፤ አይፈ ልጉትም ፤ አያምኑበትም ፤ ሊያሳኩት አይተጉም ፤ ግን ያቅዳሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች ከአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ጋር ይመሳሰላሉ፡፡
ከዚያ ደግሞ አሉ የተለጠጠ እቅድ በማቀድ ራሳቸውን የሚያጽናኑ፡፡ ከአቅማቸው በላይ የሆነ እቅድ ያቅዳሉ፡፡ ለምሳሌ ገና የሴት ጓደኛ እንኳ ሳይኖራቸው በዚህ ዓመት ትዳር እይዛለሁ ብለው የሚያቅዱ፤ ፓስፖርት ሳይኖራቸው ከሀገር እወጣለሁ ብለው የሚያቅዱ፤ የባንክ ደብተራቸው ገና ባለ አራት አሀዝ ቁጥር እያሳየ ቤት እና መኪና እገዛለሁ ምናምን የሚሉ፡፡ የአብዛኞቹ እቅድ ከማለት ይልቅ ወደ ምኞት የተቃረበ ነው፡፡ አትኩረን ብናያቸው ብዙዎቹ አነቃቂ ንግግር አብዝተው የሚሰሙ እና የንግግሩ ሞቅታ አልለቅ ያላቸው ናቸው፡፡ አነቃቂ ንግግር መስማት መጥፎ ባይሆንም ወደ እቅድ ሲገባ ግን ንግግሩ እቅድ ተደርጎ አይጻፍም፡፡ መሬት ላይ የወረደ እና የሚጨበጥ ነገር ማቀድ ያስፈልጋል፡፡
ቀጥሎ ደግሞ በጣም ደካማ እቅድ የማቀድ ልምድ ያላቸው ሰዎችን እናየለን፡፡ እነዚህ ደግሞ የሚያቅዱት የአዘቦት ውላቸውን ነው። መድከም አይፈልጉም፡፡ መታገል አይፈልጉም፡፡ እንዲሳካላቸው ግን ይመኛሉ፡፡ ስለዚህ የሆነች እቅድ ቢጤ ያቅዳሉ፡፡ ከዛ እቅዷን ቅልብጭ ያለች ናት ብለው ያደንቋታል፡፡ አትኩረን ስናየው ግን እቅዱ የሰነፍ እቅድ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ምንም አዲስ የስኬት አቅጣጫ የሌለው፤ ድካም የማያስከትል፤ የአምናው ምኞታቸው ሌላ ኮፒ ሆኖ ይመጣል። እንዲህ አድርገው የሚያቅዱት በሕይወታቸው ውስጥ የሚታቀድ ነገር ጠፍቶ ሳይሆን እቅዳቸውን ለማሳካት የሚያስፈልገውን ድካም መድከም ስለማይፈልጉ ነው፡፡
ከዚያ ደግሞ አሉ አማራጭ የሌለው እቅድ የሚያቅዱ፡፡ እንግዲህ ሁላችንም እንደምናውቀው ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ለእቅድ የማይመች ነው። ነገሮች ቶሎ ቶሎ ይቀያየራሉ፡፡ አብዛኛው ለውጥ ደግሞ በጎ የሚባለው አይነት አይደለም፡፡ ሌላ ሌላውን ትተነው አሳካዋለሁ ብለህ ያቀድከውን እቅድ ለማቀድ መስከረም ላይ ሶስት መቶ ሺ ብር ይዘህ እንደሆነ አንተ እቅዱን ለማስፈጸም ጥር ላይ ስትነሳ ዋጋው ሰባት መቶ ሺ ደርሶ ታገኘዋለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ የማይገመቱ ሁኔታዎችን ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ሀገሪቱ እንዲህ የማይገመት ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳ የሚያቅዱት እቅድ አንድ ነገር ላይ ብቻ ሙጭጭ ያለ ነው፡፡ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ እቅዳቸው ሲከሽፍ ምን አማራጭ እንዳስቀመጡ ስለማያውቁት እጅ ለመስጠት ፈጣን ናቸው፡፡
ከዚያ ደግሞ ጭራሽ እቅድ የሚባል ነገር የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ምነው ስትላቸው ፈጣሪን ይጠቅሱብሃል፡፡ እጣ ፈንታቸው በፈጣሪ እጅ የተጻፈ መሆኑን እና የእነሱ ማቀድ ብዙም ፋይዳ እንደሌለው ይነግሩሃል፡፡ ሰው ሲያቅድ ፈጣሪ ፈገግ ይላል ምናምን ይሉህና ማቀድ አላስፈለጊ እንደሆነ ይሰብኩሃል። ፈጣሪ ራሱ የልባችንን መሻት አይቶ አይደል ወይ የሚያግዘን ስትላቸው ሌላ ጥቅስ ያመጡና ክርክሩን ያሰፉታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመከራከር የሚያወጡትን ጉልበት እና ጊዜ ለማቀድ ቢያወጡት ይሻላቸው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ የማያቅዱት ልምዱ ስለሌላቸው ነው፡፡ በቃ ዝም ብለው ይኖራሉ፡፡ በእነሱ ዓለም ውስጥ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም አዲስ ነገር እንዲኖርም አይፈልጉም፡፡ የሚፈልጉት ዝም ብሎ መኖር ነው፡፡ በጳጉሜን 6 እና በመስከረም 1 መካከል ምን ልዩነት አለ ይሉሃል፡፡ ነገሮች በራሳቸው ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ እንዲከሰቱ ይፈልጋሉ እንጂ እነሱ ለዚያ ምንም ጥረት ማድረግ አይፈልጉም፡፡
ለማንኛውም ይህን ሁሉ አየንና ተቸን፡፡ ከዚያ መፍትሔው ምን ይሁን ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ መፍትሔው ከላይ የጠቀስናቸውን ተቃራኒ ማድረግ ነው፡፡ በቃ በልካችሁ አቅዱ፡፡ ያልተለጠጠ፤ ስንፍናን የማያበረታ፤ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ የከተተ፤ እንዲሁ ለማቀድ ሳይሆን ለመፈጸም የሚሆን እቅድ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ አላቅድም ማለት አግባብ አይደለም፤ መብትም አይደለም፡፡ አንተ የራስህን እቅድ ካላቀድክ የሌላ ሰው እቅድ አስፈጻሚ ትሆናለህ፡፡ ቁጭ ብለህ ነገር እስኪከናወን ከጠበቅክ የሚከናወነው ያንተ ሳይሆን የሌላ ሰው ምኞት ነው፡፡ የሚያቅድ ሰው ነገሮች እሱ በሚፈልገው መልኩ እንዲሄዱ ማድረግ ይችላል፡፡ የማያቅዱ ሰዎች ግን እንኳን ነገሮችን ለእነሱ ወደሚመች አቅጣጫ ማዞር ቀርቶ እነሱን ብሎ የመጣውን እድልም ያሳልፉታል፡፡ ቢያንስ ለእኛ የሚጠቅመንን ነገር እንድናገኝ ጥቂት ነገር እንኳ ማቀድ ይጠቅመናል፡፡
እዚህ ጋር አንድ ነገር ልጨምርና እቅድ ስናቅድ ሁሉን ነገር በእኔ፤ ለእኔ ተብሎ መታቀድ የለበትም። እድገት የሚመጣው ብዙውን ጊዜ በመተባበር ነው። እኛ በሌሎች ሰዎች እቅድ ውስጥ ቦታ አለን። ሌሎችም በእኛ እቅድ ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ብዙ እቅዶችም ተሳትፎን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አገባለሁ የሚል ሰው እጮኛውን የእቅዱ አካል ማድረግ አለበት፡፡ ሀብታም እሆናለሁ የሚል ሰው የሀብት መንገዱ በሥራም ይገኝ በውርስ ወይም በሌላ መንገድ፤ ያኛውን ወገን ታሳቢ ያደረገ እቅድ ማቀድ አለበት፡፡ ሰው ማህበራዊ ፍጡር ነው። ስለዚህም ስኬቱም ሆነ ውድቀቱ ከሌሎች ሰዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን በማወቅ እቅዱ ውስጥ ሌሎችን ታሳቢ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
በመጨረሻም መልእክታችን፤ እናቅድ፤ ከማቀድ የሚጎድልብን ነገር የለም፡፡ ከዚያ ደግሞ እቅዳችንን ለማሳካት እንሞክር፡፡ መሞከር አይጎዳንም፡፡ አቅደን ሞክረን ከተሳካልን እሰየው፤ ካልተሳካልን ደግሞ ያን አጋጣሚ እንደ መማሪያ እንጠቀምበት እና ለከርሞው እንሻሻልበታለን፡፡ ይሄው ነው፡፡
ሚዛን
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም