አዲስ አበባ፤ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራር ለነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አጽበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሹሻይ ልዑል ፌዴራል ፖሊስ በድጋሚ መጥሪያ በአድራሻቸው እንዲያደርስ ፍርድ ቤት አዘዘ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት በእነ አቶ አሰፋ ጌታቸው መዝገብ ትናንት ቀጥሮ ከነበረበት ጉዳይ መካከል በችሎት ላልቀረቡ አራቱ ተጠርጣሪዎች መጥሪያ እንዲያደርስና ውጤቱ እንዲገለጽለት አዝዞ የነበረ ሲሆን፤ መጥሪያ እንዲደርሳቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በችሎት አለመቅረባቸውን ያጣራው ችሎቱ ፌዴራል ፖሊስ በድጋሚ መጥሪያ በአድራሻቸው እንዲያደርስ አዝዟል፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾችን የማቅረብ ጉዳይ የፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ቢያመለክትም፤ ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ተብሏል፡፡
በቀጣይ ቀጠሮ ለተከሳሾች በቂ የሲዲ ኮፒ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ያዘዘው ፍርድ ቤቱ፤ አቶ ሰይፈ በላይ በጽሁፍ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ተመልክቶ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምላሽ እንዲሰጥ አዟል፡፡ በምስክሮች ጥበቃ ላይ ፈዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቤቱታ ማቅረቡን ያመለከተው ችሎቱ ተከሳሾች ጉዳዩን ተመልክተው ምላሽ እንዲሰጡም አዝዟል፡፡ በተከራካሪ ወገኖች የዋስትና ጥያቄ አስመልክቶ ተደርጎ በነበረው ጉዳይ ብይን የሰጠው ችሎቱ ባሉ ድንጋጌዎች ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ የተመሰረተባቸው ክስ ከ10 ዓመታት በላይ ሊያስቀጣቸው እንደሚችል አመልክቷል፡፡
በህግ ክልከላ ገደብ ያለበት በመሆኑ የዋስትና ጥያቄያቸውንም ውድቅ አድርጓል፡፡ ተከሳሾች ነጻ ሆነው የመገመት ህገ መንግስታዊ መብት አላቸው ያለው ችሎቱ፤ ዋስትና ተከልክለው ሲቆዩም ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ ሊቆዩ ይገባቸዋል ብሏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ‹‹የአካል ጉዳት ሊደርስብን ይችላል›› በማለት በችሎት ያመለከቱትን በመቀበልም ጉዳያቸውን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ አዝዟል፡፡
በተጨማሪም ችሎቱ ያልገለጸውን ሀሰተኛ መግለጫ ወይም ዜና ያሰራጩ የሚዲያ ተቋማት ናቸው ያላቸውን ጉዳይ በተመለከተ ችሎቱ የፌዴራል ፖሊስ እነ አቶ አሰፋ ጌታቸው መጥሪያ በአድራሻቸው እንዲያደርስ የሰጠውን ትዕዛዝ ወደ ጎን በመተው ‹‹ታስረው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት አዘዘ›› የሚል ሀሰተኛ ዘገባ ያቀረቡ ችሎት ቀርበው ማረማቸውንና ያስተላለፉበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ዝናቡ ቱኑ፤ ፍርድ ቤቱ ያልገለጸውን ዘገባ ያስተላለፉት በመረጃ አቀባበል ሂደት በተፈጠረ ስህተት መሆኑን በመግለጽ፤ ዳግመኛ ተመሳሳይ ስህተት ላለመፈጸም ቃል ገብተዋል፡፡ አቶ እሸቴ አሰፋም ሸገር ኤፍኤም 102 ነጥብ 1 ሬዲዮ ጣቢያን ወክለው ስህተቱ ሊፈጸም የቻለው ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወስደው በመዘገባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትለው ማረማቸውን በመጠቆም ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን በመወከል ጋዜጠኛ አወል አበራ ትክክለኛ የችሎቱን ውሎ በሬዲዮ እንደዘገበና ስህተት የተፈጠረው በድረ ገጽ የተጫነው ዜና መሆኑን አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በችሎት ያልተገለጸ ዘገባ መተላለፉ ስህተት መሆኑን ጠቅሶ፤ ምርመራ ተጣርቶ በወንጀል ተጠያቂ ከመሆን አስቀድመው ማረሚያ መስጠታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በብርቱ ተግሳጽና ምክር አልፏል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011
በዘላለም ግዛው