* የይዘት ጥራቱን ይጨምራል
* የስርጭትና የቋንቋ ተደራሽነቱን ያሰፋል
አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ማሻሻያ አዋጅ የህትመት ዘርፉ የይዘት ጥራቱ እንዲጨምር፣የስርጭትና የቋንቋ ተደራሽነቱ እንዲሰፋ በማድረግ ለአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያደርጋል ተባለ፡፡
ምክር ቤቱ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳይ እንዲሁም የእርቀ ሰላም ኮሚሽኖች የስራ ኃላፊዎች ሹመት አጽድቋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ትናንት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በህብረተሰቡ መካከል ሀሳቦችና አመለካከቶች ህገ መንግስቱ በደነገገው መሰረት በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ የተቋምና የአሰራር ነጻነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሲሆን፣ ለፖለቲካዊ፣ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ተወዳዳሪ፣ ተደራሽና ብዝኃነትን የሚያስተናግድ አስተማማኝ የፕሬስ አገልግሎት ለመስጠት እና ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት እንዲችል ያደርጋል ተብሎ እንደታመነበትም ተመላክቷል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየተሻሻለ የመጣውን የፕሬስ አገልግሎትና ስርጭት ከዘርፉ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እንዲጓዝ በማድረግም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ተቋሙን በአዲስ መልክ ማዋቀር መታመኑም በማሻሻያ አዋጁ ተጠቅሷል፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ድርጅቱ ቀጥታ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለረጅም ዓመታትም የመንግስትና የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ሆኖ በአንጋፋነት የቆየና በበላይነት የሚመራ ተቋም እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ተቋሙን አሁን ካለው አገራዊና ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በአሰራርና በአደረጃጀት ፈትሾ ማስተካከል ለቀጣይ ሥራ እና እንቅስቃሴ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ተቋሙ የገቢ አቅሙን እንዲያሳድግ ለማስቻል፣ በሁለት መልኩ ማለትም በቦርድ እና በመንግሥት ሰራተኛ አስተዳደር ህግ መሰረት እየተመራ የሚገኘውን የአስተዳደር ስርዓቱን ማስተካከል ማስፈለጉንም ነው የተናገሩት፡፡ የህትመት አገልግሎት በመስጠት የአገሪቱን የሚዲያ ውጤቶች የህትመት ችግርን ለማቃለል እንዲያስችል ለማድረግ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የክልል የህትመት ተቋማትን ለመደገፍ የሚያስችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆምም፤ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ ነስሩ አባጀበል በበኩላቸው ድርጅቱ የአገሪቱ አንጋፋ የመገናኛ ብዙሃን መሆኑን አንስተዋል፡፡ ሆኖም ከዕድሜው ጋር የሚመጣጠን የዕድገት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ነው የተናገሩት፡፡ ብዙ ስራዎችና መሻሻሎች እንደሚቀሩትም አክለዋል፡፡ ማሻሻያ አዋጁ ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡ ከለውጡ በኋላ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር የሚሰጡ ኃላፊዎች ተመድበው ተቋሙን ወደ ለውጥ ጎዳና አስገብተውታል ያሉት የምክር ቤቱ አባል፤ ቀደም ሲል የተቋሙ ባልደረባ እንደነበሩ፣ ስለድርጅቱ በቅርበት እንደሚያውቁና ድጋፍ ለማድረግ ዕድሉ እንደነበራቸውም መስክረዋል፡፡
አዋጁ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረውን ችግር ይፈታል፣ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በመንግሥት ሠራተኛ አስተዳደር ህግና በቦርድ ሲተዳደሩ በመቆየታቸው በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩትን ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ይፈታል ብለዋል፡፡ በደመወዝ እስኬልና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ሠራተኛው ላይ ችግር ተፈጥሮ መቆየቱን በመጠቆምም፤ አዋጁ የተቋሙን ሠራተኞች በአንድ አመራር እንዲመሩ ያደርጋል፣ ተቋሙ የተጣሉበትን ዓላማዎች ለማሳካት ያስችለዋል ብለዋል፡፡ አዋጁ ተገቢ፣ ተቋሙ ኃላፊነቱን ለመወጣት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርለት መሆኑንም አቶ ነስሩ አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ በሙሉ ድምጽ ለሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረቡትን ዶክተር ጣሰው ገብሬን የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አድርጎ ሲሾም፤ ኡስታዝ አቡበከር አህመድን ደግሞ በምክትል ኮሚሽነርነት እንዲሾሙ በ25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡ በተመሳሳይም ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሆኑ በአራት ተቃውሞ፣ በ10 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሹመቱን አጽድቋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011
በዘላለም ግዛው