ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በበሬ በላችነት

 ለዓውድ ዓመት ሰው እንደቤቱና እደአቅሙ እርድ ያደርጋል፡፡ የቻለም ቅርጫ ይጨምራል። ታዲያ ሴቶች የዶሮ ብልት በማውጣት እንደሚፈተኑት ሁሉ ወንዶችም በጉን በሬውን በመበለት ይፈተናሉ፡፡ በተለይ የበሬውን ዳቢት ከሻኛ መለየቱ ላይ እውቀት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው በሬ በላች ተፈልጎ እርዱ የሚከናወነው፡፡

በሬ በላቹ ቅርጫ ለገቡት ሰዎች ፍትሐዊ ክፍፍል በማድረጉ ላይም ሚና አለው፡፡ እያንዳንዱ የሥጋ ክፍል በቢለዋ እየተመተረ በመደብ ከተቀመጠ በኋላ ነው ቅርጫ የገቡት ድርሻቸውን የሚወስዱት፡፡

ከእርዱ ጀምሮ በመደብ እስኪከፋፈል ድረስ የቅርጫ ቡድኑ ከበላቹ አይለዩም፡፡ አብረው መሆናቸውም ብርታት ይሰጠዋል፡፡ ቅርጫ በዚህ በኩል ጥሩ የማህበራዊ መተሳሰሪያ ተደርጎም ስለሚወሰድ ብዙዎች ይወዱታል፡፡ ይናፍቁታል። በዚህ መንገድ በመሰባሰብ ረጅም ዓመት አብረው የዘለቁ እንዳሉም በየአካባቢያችን እንታዘባለን፡፡

በቅርጫ ላይ ሚጥሚጣ አይጠፋም፡፡ ቅርጫው ወደቤት ከመወሰዱ በፊት፤ በላቹን ጨምሮ ቅርጫውን ለመውሰድ የተሰባሰበው ሁሉ ስለሚቀምስ ነው ሚጥሚጣው አብሮ የማይጠፋው። በአንዳንድ አካባቢ ማወራረጃም አብሮ ይቀርባል። ጨዋታው ደምቆ የተከፋፈሉትን ስጋ በእቃቸው ይዘው በቅርጫው ቦታ እንደሚያረፋፍዱ አንዳንዶች ተሞክሮአቸውን ሲያካፍሉ ይሰማል፡፡

በሬ ለመበለት በእውቅ የሚፈለጉ ሰዎች የኑሮ መተዳደሪያቸው በማድረግ በበዓላት፣ በሰርግ፣ በተለያየ ድግሥ እየተፈለጉ ይሰራሉ፡፡ ኑሮ መተዳደሪያቸው አድርገው በዚህ ሥራ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱትም በአንድ ቀን በቁጥር በዛ ያለ እርድ በማከናወን ገቢ ያገኛሉ፡፡

እኛም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በሬ በመበለት ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ፣ በቆይታቸውም ገጠመኛቸውን እንዲያጫውቱን ለሕይወት ገጽ እንግዳ ጋብዘናል፡፡

እንግዳችን ለቤተሰባቸው ሶስተኛ ልጅ ናቸው። በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን እነሞር ወረዳ ነው የተወለዱት። የገበሬ ልጅ ናቸው። አቶ ሰይፉ ሃይሌ ይባላሉ፡፡ የኑሮ ውጣ ውረድ የገጠማቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ነው፡፡ መራብን መታረዝን ያሳለፉ ናቸው፡፡ ይህን ሁሉ ፈተና ያዩት ቤተሰባቸው ዓመቱን ሙሉ ሊያጠግብ፤ መጥገብ ባይቻል እንኳ ቀምሰው እንዲያድሩ የሚያስችል በቂ የሚታረስ መሬት ስላልነበራቸው ነው፡፡ እንደ ልጅ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሳያገኙ፣ በቂ ልብስም ሳይኖራቸው ነው እየተንገላቱ በገጠር ለ 17 ዓመታት የኖሩት፡፡

አቶ ሰይፉ በገጠር የነበራቸውን ኑሮ እንደገለጹልን እርሻ ሥራ የጀመሩት በታዳጊነት እድሜያቸው ነው። የእርሻ መሬቱ አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በቂ ምርትም ስለማይሰጥ፣ እርሳቸው ጨምሮ ለነበሩት አራት ልጆችና ወላጆቻቸው የሚሆን ቀለብ ማግኘት ይቸገሩ ነበር፡፡ በዓመት የሚሰበሰበው ምርት ለቀለብ ውሎ ከላዩ ላይ ተሸጦ ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ለማዋል እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ አቶ ሰይፉ ገና አካላቸው ሳይጠና ነበር ለኑሮ መጨነቅ የጀመሩት፡፡ የእለት ተእለት ኑሮአቸውም ቁጭት ውስጥ ነበር የከተታቸው።

እንደሌሎች እኩዮቻቸው ተምረው መሻሻል ትልቅ ደረጃ የመድረስ ፍላጎት ኖራቸውም የነበሩበት ኑሮ የሚፈልጉትን ለማድረግ የሚያስችላቸው አልነበረም። ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ከኑሮ ጋር እየታገሉ እስከስድስተኛ ክፍል ተምረዋል።

 በኑሮ ትግል ውስጥ ሆነው በታዳጊነት ዕድሜያቸው ቤተሰብ ስለመርዳት በማሰላሰል፤ ባያድጉም አድጌያለሁ ብለው በማመን የጀመሩትን ትምህርት ሳያጠናቅቁ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ሥራ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡

ገቢ አግኝተው ቤተሰቦቻቸውን ስለመርዳትም ሆነ ቤተሰብ ስለማስተዳደር ማሰባቸው መነሻው ከእርሳቸው መራብ እና መታረዝ በላይ የእናት እና የአባታቸው በችግር መሰቃየት ነበር የበለጠ ቁጭት ውስጥ የከተታቸው። የኑሮ ቁጭታቸውን ለመወጣት ግን ውጣ ውረዱ ቀላል አልነበረም፡፡ ከገጠሩ ኑሮ ባልተናነሰ ነበር የተፈተኑት፡፡ ሥራ ማፈላለጉ ቀላል አልነበረም፡፡

ገጠር እየኖሩ እንደቀልድ ሥራ ማግኘት አይቻልም። ገና እድሜው ከፍ ያላለ እና ያልጠነከረ ሰው ቀርቶ አቅም ያለውም ቢሆን፤ ሥራ ለመቅጠር ፍቃደኛ የሆነ ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ የማያውቁት አካባቢ ያውም ከተማ መግባት ከባድ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ወደ ከተማ መግባትን ሲያስቡ በቅርብ ርቀት ላይ ያለችው ወልቂጤ የሚወስዳቸውን አማራጭ አሰላሰሉ ሆኖም ወልቂጤም በቂ ሥራ ላይገኝባት ይችላል ብለው ገመቱ፡፡ ስለዚህ ሰፊ የሥራ ዕድል ይገኛባታል ብለው ወደአሰቡት፤ ለሁሉም አማራጭ የተባለችው የኢትዮጵያ ተመራጭ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ትሻለኛለች ብለው በመወሰን ወደ አዲስ አበባ ከተማ አቀኑ፡፡

ከእነሞር ወደ አዲስ አበባ

አቶ ሰይፉ እራሳቸውን በኑሮ ለውጠው ቤተሰባቸውንም በገንዘብ ለማገዝ ሳያቅማሙ በስም ብቻ ወደሚያውቋት አዲስ አበባ ከተማ ለመምጣት ወሰኑ፡፡ የትውልድ ቀዬያቸውን ለቀው ሲወጡ የ 17 ዓመት ታዳጊ ነበሩ፡፡ አዲስ አበባ ለመግባት መክፈል ያለባቸውን መስዋትነት በሙሉ ለመክፈልም ዝግጁ ስለነበሩ ቆርጠው ነው አካባቢያቸውን ለቀው የወጡት። አቶ ሰይፉ አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት ወሰኑ እንጂ በወቅቱ ለሚጓዙበት የሚከፍሉት ገንዘብ አላሰቡም፡፡ የአካባቢያቸውን ሰዎችና ዘመድ ማስቸገር ግድ ስለነበር እጁን ከዘረጋላቸው ያሰባሰቡትን ገንዘብ ይዘው ባገኙት ትራንስፖርት ተሳፍረው አዲስ አበባ ገቡ፡፡ አዲስ አበባ ሲደርሱም ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራ ለማግኘት ነው። እቅዳቸው ከሚያገኙት ገቢ ለቤተሰባቸው ገበሬ በመቅጠር ድካማቸውን ለመቀነስ ነበር፡፡

ሰው የሃሳቡ ምርኮኛ ነውና አዲስ አበባ እንደገቡ ሥራ ማፈላለግ ቢጀምሩም፤ እንዳሰቡት ወዲያው ሥራ አግኝቶ ቤተሰባቸውን መርዳት አልቻሉም። ቀድሞም ሥራ ያለማግኘት ስጋት ነበራቸውና እንደፈሩት የሚቀጥራቸው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ሥራ መፈለጉ ተስፋ አስቆራጭ ነበር። የሚረዳቸው ሰው አፈላልገው ወደ ንግዱም ለመግባት ፈልገው ነበር፡፡ ለንግድ መነሻ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ዳገት ሆነባቸው። ለነገሩ ቢጨንቃቸው እንጂ የንግድ ክህሎቱ የላቸውም፡፡ ልጅም ስለሆኑ ሰፋ ያለ ሃሳብ አልነበራቸውም፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ገብተው ለመለወጥ የነበራቸው ፍላጎት እየጨለመ መጣ፡፡ ውለው ሲያድሩ አዲስ አበባ ከተማ እንዳሰቧት የተፈለገው የሚሰራባት እና በቀላሉ ገንዘብ የሚገኝባት እንዳልሆነች ተገነዘቡ፡፡ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ገጠር ለመመለስ ወሰኑ። በገጠር ያሳለፉት የጉስቁልና ኑሮ እና የቤተሰባቸው ችግር በዓይነ ህሊናቸው እየመጣ ተረበሹ፡፡ ተስፋ አጥተው ግራ ተጋብተው በአዲስ አበባ ጎዳና አዲሱ ገበያ አካባቢ ከወዲያ ወዲህ እያሉ ያላሰቡት ነገር ገጠማቸው፡፡ በሬ የገዙ ሰዎች አራጅ ሲፈልጉ አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም በሬ የመበለት ችሎታቸው እንዳላቸው ለሰዎቹ ይግሯቸውና ይስማማሉ። ከዚህ እለት ጀምሮ ነው እንግዲህ አቶ ሰይፉ ሳያስቡት ወደ ገቡበት በሬ በላችነት ሥራ ግብተው የቀሩት፡፡

በሬ አራጅነት

ምን እንደሚሠሩ ተጨንቀው በአጋጣሚ በሬ ማረድ ሥራ ሆኖ ከፊት ለፊታቸው ቀረበ፡፡ በሬ ማሳረድ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ተጋግዘው እየሠሩ የተሰጣቸውን አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም እና ሁለት ብር እየተቀበሉ መተዳደሪያቸው አደረጉት፡፡ በሬውን ሲበልቱ ታላቅ፣ ታናሽ፣ ሳልገኝ፣ ዳቢት፣ ሽንጥ፣ ፍርንቢያ፣ ሻኛ፣ ምላስ እና ሰምር እያሉ እያንዳንዱ የበሬውን የስጋ ክፍል ለይተው ማወቅ ቻሉ፡፡ በዓል ሲመጣ ገበያው ደራ፤ በሬ አርደው ለማከፋፈል ግፋ ቢል የሚወስድባቸው አንድ ሰዓት ብቻ ሆነ፡፡ የበሬ ቅርጫ ሲከናወን ክፍፍሉን አይናቸውን ጨፍነው ቢያከናውኑ እንኳ ልዩነት እንደሌለው ይነገርላቸው ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ቤተሰብን ማገዝ ብዙ ከባድ አልሆነም፡፡ እንደፈለጉት ለአባታቸው አራሽ ሠራተኛ ቀጥረው ማሳረስ ጀመሩ፡፡

ጉዳይ ያለበት ሰው ሰርግ ደጋሽ፣ ተስካር የሚያወጣ ወይም ቤተሰብ ሞቶበት ለቀብር ከብት የሚያርድ እና የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያከናውን በሙሉ አቶ ሰይፉን ፈላጊ ሆነ፡፡ ደንበኛ ማፍራት

 ጀመሩ፤ በሂደት አቅማቸው እየጠነከረ ሲመጣ በቀን ሁለት እና ሶስት በሬ በማረድ ደህና ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ እንደውም ከራሳቸው አልፈው ረዳት ቀጥረው ለሌላ ሰውም የሥራ ዕድል አመቻቹ። ሲገኝ ሥራ ሲሰሩ እያጠራቀሙ እንዳሰቡት ለአባታቸው ረዳት ቀጥረው ለቤተሰባቸው አለሁ ከማለት ባሻገር የሕይወት አጋር፤ ችግርን ተካፋይ እጮኛ ፈለጉ፡፡ በሥራው ላይ ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ትዳር መሠረቱ፡፡

የቤተሰብ ሁኔታ

መለሎ የተባለለት ቁመት ከሰውነት ውፍረታቸው ጋር ተዳምሮ ዕድሜያቸን ትልቅ ሲያስመስለው አቶ ሰይፉ ራሳቸውን እንደትልቅ ሰው አዩ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ትዳር መመስረታቸውን ተከትሎ አንድ ሁለት እያሉ በጊዜ ልጆች አፈሩ። ከተማ ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር በተጨማሪ የገጠሩንም ቤተሰብ በሚችሉት አቅም መርዳታቸውን ቀጠሉ፡፡ ይህንኑ ሥራ እየሠሩ ቤተሰብ መስርተው ሶስት ልጆች አፈሩ። አሁን የመጀመሪያው ልጃቸው 23 ዓመቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው 18 ዓመቱ ነው። የመጨረሻው እና ሶስተኛው ልጅ ደግሞ 13 ዓመቱ ነው፡፡ አንደኛው ልጅ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ባለማምጣቱ በር፣ መስኮት እና ቁምሳጥን የመሳሰሉትን የእንጨት ሥራዎች ተቀጥሮ ይሠራል፡፡ ሌሎቹ ይማራሉ፡፡

ሆኖም በሬ የማረድ ሥራ ገቢው ከእጅ ወደ አፍ ነውና፤ ፈተናቸው ቀጠለ፡፡ አንዳንዴ ሥራ ይገኛል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሥራ ይጠፋል፡፡ ለበዓል ሥራው ሞቅ ብሎ አራት እና አምስት በሬ የሚያርዱበት ጊዜ አለ። በተቃራኒው ደግሞ ወሩን ሙሉ አንድም በሬ ሳያርዱ እና ገቢ ሳያገኙ የሚያሳልፉበት ጊዜም ቀላል አይደለም። ሱሉልታ ልዩ ስሙ አሸዋ በሚባል አካባቢ ቤት ተከራይተው ሲኖሩ፤ ብዙ ችግር አይተዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ሰይፉ ምንም ያህል ቢቸገሩ ብዙ አያማርሩም። እንደማንኛውም ሰው በተለይ አሁን እየተቸገሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን ደግሞ በፈጣሪ ርዳታ ከነቤተሰባቸው ቀምሰው እያደሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹አንድ ኪሎ ጤፍ ስንት ብር እንደደረሰ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የቤት ኪራይ ተከፍሎ፤ የትራንስፖርት ገንዘብ ተችሎ በዚህ ሥራ ብቻ መውጣት እና መግባት ሲታሰብ ከባድ ነው፡፤ ነገር ግን እንደኑሮ ውድነት አይደለም፤ ክብር ለፈጣሪ የምንቀምሰው አናጣም፤ በልተን ጠጥተን እየኖርን ነው፡፡›› ይላሉ፡፡

የበሬ ማረድ ሥራቸው

በ25 ዓመት የበሬ ማረድ ቆይታቸው የተለያዩ አጋጣሚዎችን አስተናግደዋል፡፡ ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝተው ተመሰጋግነው ተለያይተዋል፡፡ ሥራ በማጣት እና ተደራራቢ ሥራ በማግኘት ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል፡፡ ሥራውን ሲጀምሩ አንድ በሬ ሲያርዱ የሚከፈላቸው አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ብቻ ነበር፡፡ ሁለት ብር ሲከፈላቸው ደስታቸው ወደር አልነበረውም። እንደጊዜው ሁኔታ የበሬ ማረጃ ዋጋ እየጨመረ አሁን እንደበሬው እና እንደሰዎቹ ሁኔታ ከአንድ ሺ አምስት መቶ ጀምሮ ከሁለት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር ይከፈላቸዋል። እዚህ ላይ አሁን ሌሎች በሬ አራጆች ግን እስከ አስር ሺህ ብር ማ ስከፈል ጀምረዋል፡፡

አቶ ሰይፉ እንደሚገልፁት፤ በተለይ ለዓመት በዓላት የቅርጫ ሥነሥርዓቱ ላይ ተደስተው ከተነጋገሩት ገንዘብ በላይ ጨምረው የሚሰጡ፤ መርቀው የሚያስደስቱ ብዙ ናቸው፡፡ በተቃራኒው አንዳንዶች በተገቢው መልኩ ስለተሠራ ብቻ የሚደሰቱ እንዳሉ ሁሉ፤ ምንም ያህል ጥረት አድርገው በደንብ ቢሠሩም ሰበብ ፈልገው የሚቆጡ እና በንግግር የሚስቀይምም አይጠፋም፡፡

‹‹እኔ ሰው ከሚቀየም እራሴ ብጎዳ እመርጣለሁ፤ ሰው ቅር ካለው እና ከተቆጣ በጣም እከፋለሁ። ምክንያቱም የምፈልገው ሰው በእኔ ሥራ ረክቶ ተደስቶ እንዲያመሰግነኝ እንጂ ተከፍቶ እንዲያማርር አይደለም። ሥራዬን ስሠራ ቅር ያለው ካለ ይናገር፤ በተለይ የበዓል ቅርጫ ላይ እኔ ስሠራ ይሄ መደብ አንሷል የሚል ካለ አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ እላለሁ፡፡ ነገር ግን አንድም ቀን ይህ ትክክል አይደለም፤ ክፍፍሉ ላይ አድሎ ተፈፅሟል የሚል ጭቅጭቅ ገጥሞኝ አያውቅም። ንትርክ በፍፁም አልፈልግም፡፡

እንደውም ብዙዎች ሰይፉ በሔደበት ቦታ አስደስቶ እና ተደስቶ የሚመጣ ነው ይሉኛል፡፡ ቋሚ የበዓል ደንበኞች አሉኝ፡፡ አንዳንዴ እነኚሁ ሰዎች ጉዳይ ሲገጥማቸው እየጠሩ ያሰሩኛል፡፡ ከአንዳንዶቹ ጋር ቤተሰብ እስከ መሆን ተቀራርበናል፡፡›› ይላሉ፡፡

አቶ ሰይፉ ከደንበኞቻቸው ጋር ከብት ከመግዛት ጀምሮ አብረው የሚዞሩበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፤ ጥሩ የተባለውን በሬ በተመጣጣኝ ዋጋ አጋዝተው ለደንበኞቻቸው ያርዱላቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ግን በፍፁም ድለላ የተባለ ነገር ውስጥ አይገቡም፡ ድለላን አጥብቀው በጣም ይጠላሉ፡፡ ድለላን የሚጠሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ‹‹ሲበላ የሚጣፍጠው እና ልጆችም እንዲበሉ ሲደረግ የሚስማማው የሚያስደስተው በላብ በተገኘ ገንዘብ ነው፡፡ ድለላ ግን ሥራው ማወናበድ እና የሰው ላብ መብላት ነው። ምንም ያህል ብቸገር ደልዬ በሬ አሻሽጬ ከምበላ ጦሜን ባድር እመርጣለሁ። ቤተሰቦቼም እንዲበሉ የምፈልገው በላቤ ሠርቼ ባገኘሁት ገንዘብ ብቻ ነው›› ይላሉ፡፡

አጋጣሚዎች

በተደጋጋሚ አስቸጋሪ በሬ ያጋጥማል፡፡ ገና ከበረት ሲወጣ ጀምሮ ሰው አይንካኝ የሚል በጥባጭ በሬን ማየት የተለመደ ነው፤ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ይኖራል፡፡ በጥባጭ ከብት ከፈረጠጠ ማንም አይዘውም፤ ምናልባት የሚይዘው ሞተረኛ ብቻ ነው፡፡ ይሔ በተደጋጋሚ የሚታይ አጋጣሚ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡ ሞተረኛ ከያዘው ከብቱ የፈረጠጠበት ሰው ያለውን ያህል ከብቱን ለያዘለት ሰው ሰጥቶ ይዞ ይሔዳል። ከሁለት እና ከሶስት ሺህ ብር ያላነሰ ይከፈላል። ካልተያዘ እና ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ በብዙ ርቀት ካመለጠ አደጋው እና የሚያስከፍለው ዋጋም ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡

እንደ አቶ ሰይፉ ገለፃ፤ በሬ የፈረጠጠበት ሰው ቶሎ እንዲያዝለት ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንድም ብዙ ብር አውጥቶ የገዛው ከብት በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ በሬው ይጠፋል ብሎ ስለሚሰጋ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፈረጠጠ ከብት ሰው የሚገድልበት አጋጣሚም ስለሚኖር ያ እንዳይሆን ርቆ እንዳያመልጥ በፍጥነት ትልቅ ጥረት ይደረጋል፡፤

ብዙ ሰው የሚፈረጥጥ ከብት ሲያጋጥም እንደሚደናገጥ እና በሬውን ለመቆጣጠር ከመክፈል ወደ ኋላ እንደማይል አስታውሰው፤ ከአጋጣሚዎች መሃል የማይረሱትን ያስታውሳሉ፡፡ ሱሉልታ 10 ኪሎ የሚባል አካባቢ አይናቸው እያየ ፊጋ በሬ የመኪና ስፖኪዮ ሰብሮ ሲሮጥ ሰዎች በባጃጅ ቢከተሉትም ደርሰው ሊይዙት አልቻሉም ነበር። የፈረጠጠው ከብት አንድ መንገደኛን በቀንዱ ከመሬት አንስቶ ከመኪና ጋር አጋጨው፤ ሰውየው ጭንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ በበሬው መወጋቱን ተከትሎ ወዲያው ሕይወቱ አለፈ፡፡ በሬን በተመለከተ ለማሰብ የሚከብዱ እንዲህ አይነት የተለያዩ አጋጣሚዎች አሉ ይላሉ፡፡

አቶ ሰይፉ ሲናገሩ፤ እርሳቸውም በተደጋጋሚ ሰው አይንካኝ የሚል ፊጋ በሬ ያጋጥማቸዋል፡፤ ነገር ግን እርሳቸው ፊጋ በሬ ሲያጋጥም በዘዴ ሳይጠጉ እንዴት ቁጥጥራቸው ስር ማድረግ እንደሚችሉ ተለማምደዋል። ገመድ ጠልፈው ከሩቅ ወርውረው በመያዝ ከእንጨት ጋር አንገቱን እና እግሩን አስረው ጠልፈው በቁጥጥራቸው ሥር ያውሉታል። ለማረድ ከተፈለገም ለመጣል ብዙ አይቸገሩም በዘዴ ምቹ ሁኔታ ፈጥረው ያርዱታል፤ ወይም ሌሎች እንዲያርዱ ያመቻቻሉ፡፡

የሚሠሩት ከረዳት ጋር ሲሆን፤ ከበረት የተገዙትን በሬዎች ወደ መኪና ሲያወጡም ሆነ ከመኪና ሲያወርዱ በዘዴ መሆኑን ያስረዳሉ። ከረዳታቸው ጋር አብረው ሲሠሩ በሬውን ላረዱበት እና ለበለቱበት አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ሲከፈላቸው ለረዳታቸው አምስት መቶ ብሩን ሰጥተው ለእርሳቸው አንድ ሺህ ብሩን እንደሚወስዱ ይገልፃሉ፡፡

ብዙ ጊዜ እርዱ ሲከናወን በተለይ የቅርጫ ሲሆን፤ ሰዎች እንደሚያግዙዋቸው አንዳንዶቹ ቁጭ ብለው ሲያዩ አንዳንዶቹ አካባቢውን በማፅዳት እና ስጋ በመያዝ አቶ ሰይፉ የቆራረጡትን ሥጋ በየመደቡ በማስቀመጥ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በማከፋፈል የሚያግዟቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አቶ ሰይፉ በሌላ በኩል ከሚያጋጥማቸው ቀላል አጋጣሚዎች መካከል አልፎ አልፎ ሥራ ሲሰሩ በተወሰነ መልኩ ቢላዋ እጃቸውን ይቆርጣቸዋል። በዋናነት ግን በሬ ሲታረድ እርሳቸው የበሬውን አንገት ሲይዙ፤ በሬውን የሚያርደው ሰው ቢላዋውን አቶ ሰይፉ እጅ ላይ በማሳረፉ የቀኝ እጃቸው አውራ ጣት ክፉኛ የተጎዳ ከመሆኑ ውጪ በአካላቸው ላይ ግን ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡

የቅምሻ ጉዳይ

በኢትዮጵያውያን ባህል በሬ ታርዶ ከአናቱ ጥሬ እና ጥብስ እያሉ መቅመስ የተለመደ ነው፡፡ ‹‹ ታርዶ ከአናቱ ካልተቀመሰ እና ካልተበላ ምን ዋጋ አለው? ከታረደ በኋላ ያረዱትን መቅመስ ያለ ነው።›› ይላሉ። በዓል ላይም ሆነ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲኖሩ፤ በሬ አርደው ከበለቱ በኋላ ቅርጫ ከሆነ እና ለአራትም ሆነ ለስድስት እንዲሁም ለስምንት የሚካፈል ሲሆን፤ ቀድሞ ወዲያው ለሚበላ ይቀነሳል፡፡

በሬ እንዲታረድላቸው ያዘዙት ሰዎች ስጋውን ከትፈው ማባያ ሚጥሚጣ እና እንጀራ ወይም ዳቦ አዘጋጅተው ሥራው ሲያልቅ ያዘጋጁትን ለሁሉም ያቀርባሉ፡፡ ስጋው ሲቀርብ በጥሬ መልክ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ምቹ ሁኔታ ሲያጋጥም ጠባብሰውም ያቀርባሉ። በተለይ ጉበት በጥሬው የሚቀርብ ሲሆን፤ ሰዎች ባህላቸው የተለያየ በመሆኑ ጉበት የማይበሉ ሰዎች ያጋጥማሉ። ከጉበት ይልቅ አንጀት ይሻለኛል የሚሉ አሉ። አንጀት የሚሉት ጉበት መብላት የሚዘገንናቸው ሲሆን፤ ጉበት የሚበሉት ደግሞ ሰው እንዴት አንጀት ይበላል? ብለው እንደሚገረሙ አቶ ሰይፉ ይናገራሉ፡፤

በበዓል ቀን እርሳቸው ሲሰሩ ሌሎች ሲዝናኑ ብዙም እንደማይከፋቸው የሚናገሩት በሬ በላቹ አቶ ሰይፉ፤ ሰዎች ሲጠጡ እና ሲደሰቱ እርሳቸውም ደስ እንደሚላቸው፤ ከሰዎች ጋርም በተደጋጋሚ የሚመገቡበት ሁኔታ መኖሩን ይገልፃሉ፡፡ በበዓል በጋራ መብላ እና በጋራ መደሰት እንዲሁም አንዱ ለሌላው ማቅመስ መቀጠል አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን     ጳጉሜን  5 ቀን  2015 ዓ.ም

Recommended For You