. ያለ ደረሰኝ ግብይት የፈፀሙ አራት አከፋፋዮች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ያለ ደረሰኝ የሚካሄዱት ህገ ወጥ ግብይቶች እየተስፋፋ መምጣታቸውን የከተማዋ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ በቅርቡ ባደረገው ምርመራ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የሆኑ አራት ድርጅቶች ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ይዟቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን የታክስ ህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ንጉሴ ትናንት በሰጡት መግለጫ በከተማዋ ያለ ደረሰኝ የሚደረጉ ግብይቶች በስፋት መኖራቸው፤ ይህንን ለመቆጣጠርና ለመከላከልም የሚያስችሉ ሥራዎች በባለሥጣን መስሪያ ቤቱ በኩል በየዕለቱ እየተከናወኑ እንደሚገኙ፣ በዚህም ለግብር አሰባሰቡና ለግብይት ሥርዓቱ ትልቅ ተጸእኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉና በግንባታ እቃዎች አቅርቦት የተሰማሩ አራት ድርጅቶች በተደረገባቸው ምርመራ ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ታምራት ንጉሴ ገለጻ፤ ባለሥልጣኑ ኡራኤልና ሲግናል አካባቢ የሚገኙ አራት አከፋፋዮችን ማለትም የአብስራ ሴራሚክስ በአቶ ቢኒያም ሽብሩ ስም የተመዘገበ፣ ልዩ አጨራረስ በአቶ አመርጋ ወልፃዲቅ ስም የተመዘገበ፣ ሳባ ግራናይትና ሴራሚክስ በወይዘሮ ሳባ ጥላሁን ስም የተመዘገበ እና ፎዚያ ሴራሚክስ በአቶ እስማኤል ነስሩ ስም የተመዘገቡት ላይ ምርመራ በማድረግ ያለ ደረሰኝ ሽያጭ ያካሄዱ ሁለት ባለቤቶችና ስምንት የሽያጭ ሰራተኞችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
ድርጅቶቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካሳወቁት የገቢ መጠን የግብር ክፍያ አኳያ ከ3 እስከ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዓመታዊ ሽያጭ እንደሚያከናውኑ ሲታወቅ፤ባለሥልጣኑ ለምርመራ ሂደቱ ከ100ሺ ብር በላይ በሆነ ወጭ እቃዎችን በመግዛት ካለደረሰኝ እንደሚሸጡ ለማረጋገጥ መቻሉን አቶ ታምራት ጠቁመዋል፡፡ አቶ ታምራት ያለ ደረሰኝ ግብይት በመፈጸም ለመንግስት የሚገባውን ግብር ባለመክፈልና ለግል በማዋል፤ ገቢን በመሰወርና ዓመታዊ የንግድ ሥራ ግብርን በማሳነስ፣ ባለሥልጣኑም በኦዲት እንዳያገኘው ተጽእኖ በማሳረፍ ትልልቅ ግብሮች እንዳይሰበሰቡ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ በታክስ አሰባሰብ ሂደት በዝቅተኛው የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉት ወደ ሥርዓቱ እንዳይገቡ እንደሚያደርግና የግብር አካፋፈል መዝገብንም ሊያዛባ የሚችል ተግባር መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡
ትልልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑት ግብር ከፋዮች ላይ በጥናት በማስደገፍ የምርመራ ሥራ በማከናወን የማረጋገጫ ሥራ እየተሰራ መሆኑንና ቅንጅታዊ ሥራው ተግባሩን ለመከላከል እንደሚያስችል አቶ ታምራት ገልፀው፤ ድርጊቱን ሁሉም ግብር ከፋዮች እንዳልፈጸሙ፣አብዛኛው ሰው ህጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ እየሰራ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉት ግን ያለ ደረሰኝ ግብይት እየፈጸሙ መሆናቸውን ባለሥልጣኑም በምርመራ ስራው ማረጋገጥ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡
ከምርመራው በተጨማሪ ቤት ለቤት በተደረገው የመስክ ቁጥጥር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በከተማዋ 1ሺ 439 ግብር ከፋዮች ያለ ደረሰኝ ግብይት መፈጸማቸውንና 71 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚደርስ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደተወሰነባቸው አቶ ታምራት ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011
በአዲሱ ገረመው