መቼም ይሁን የት በምንም አጋጣሚ አይቶ መታዘብ ፣ ታዝቦ ማስተማር ከተቻለ እሰዬው ነው። አንዳንዴ የትዝብቱ ዓላማ ነቀፌታ ብቻ ከሆነ ግን ለማንም አይበጅም። ይህ አይነቱ ልማድ ከተራ ሀሜት አይዘልምና ለአስተማሪነቱ ሚዛን አይደፋም ።
ዛሬ ዓለማችን በቴክኖሎጂ ልቃለች ። የአንድ መስኮት የመረጃ ልውውጥ ተደራሽነት የብርሃን ፍጥነት ያህል የላቀ ሆኗል። እንዲህ መሆኑ ኋላቀርነት በነበር እንዲታወስ፣ የኋሊቱ ጊዜ በዘመን ስልጣኔ እንዲሰላ ያስችላል። ይህ አጋጣሚ ሀገራት በንግድ ልውውጥ ኢኮኖሚያቸውን እንዲያልቁ አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
የንግድ ልውውጥን ካወሳን ዘንድ የምርትና አምራቾችን ሚና ልናነሳው ግድ ይለናል። ይዘቱ ካለ የመገኛው ምንጭ መጠቀሱ አይቀሬ ነው። አንድ ምርት የራሱን ስያሜና መለያ ይዞ ለገበያ እንዲበቃ የአምራቹ እጆች ያርፉበታል። በእኔ ዕምነት ዓመታትን ተወዳጅ ፣ ተመራጭ ሆኖ እንዲዘልቅ ስሙን እንዲመጥን ደግሞ ‹‹ታማኝነት›› መርህ ሊሆነው ግድ ይላል።
ዛሬ ዕለቱን በአምራችነት ቀን አስበነዋልና ከስራው ሊነጣጠል ስለማይገባው የታማኝነት ጉዳይ እንታዘባለን። ‹‹እነሆ!›› ከጥቂት ቀናቶች በኋላ አዲሱን ዓመት ልንቀበል ነው ። እንዲህ እንደአሁኑ ዓውደ ዓመት በመጣ በዓል በደረሰ ጊዜ ሸመታው ፣ የምርት ውድድሩ ይደራል። አምራቾች በተለየ ትኩረት ምርቶቻቸውን ይዘው ለገበያ ይቀርባሉ ። ሸማቹም ያሻውን መርጦ የሚበጀውን ይገበያል ።
ይህ አይነቱ እውነታ ዓመታትን በዚህ መልኩ ቀጥሏል። ገበያና ገበያተኛው ሲገናኝ ግን ጉዳዩ ገንዘብና ግብይት ብቻ አይሆንም። ስለዕቃዎቹ ምንነት ዓይኖች በጥንቃቄ ያማትራሉ። እጆች ጥራትን እየለዩ ይዳስሳሉ፣ ልቦናም ሁሉን ከሚዛን አስቀምጦ የተሻለውን ያወዳድራል።
ነጋዴው ደንበኞችን የሚቀርብበት አግባብ በራሱ ስልት ይሁን እንጂ ገበያተኛው ስለግዥው የሚያማትርበት ዓይን ለየት ይላል። እንዲያም ሆኖ ስለዕቃዎቹ ምንነት ማረጋገጫን መሻቱ አይቀርም። ለዚህ እውነታ የመጀመሪያው እማኝ ምርቱን ይዞ ለገበያው የሚቀርበው አካል ይሆናል። ስለያዛቸው ዕቃዎች ጥራት፣ ጥንካሬና ተመራጭነት ፣ በአግባቡ ማረጋገጡ የተለመደ ነው።
አቅራቢው ምርቱን ለገበያ አውጥቶ ‹‹እነሆኝ!›› ሲል ትኩረቱ ገንዘብ ማግኘቱ ላይ ብቻ አይሆንም። ከምንም በላይ ስያሜውን የሚሸከም ስሙን እንደያዘ ያለስብራት፣ ዕንቅፋት መራመድን ይሻል። ስለሚሸጠው ዕቃ ተመራጭነት በዝርዝር ሲያስረዳም ቢፈተን የማይወድቅበትትን ፣ ቢፈተሸ የማያፍርበትን እርግጠኝነት አስከትሎ ነው።
በእርግጥ ሁሉም የንግድ ሰው በዚህ ማንነት ይገለፃል ማለት አይደለም። እንዲህ አይነቱ ነጋዴ በአቋሙ ለመጽናት የታማኝነቱ ሌላ እማኝ ይኖረዋል። ዕቃውን ለሽያጭ ሲያቀርብ አምኖ የተቀበለውን አምራች እሱም በተራው ያምነዋል ። የምርቱን ጥራት፣ የዕድሜና ጥንካሬውን እውነታ በማሳያነት ማረጋገጡ አይቀሬ ነውና።
ይህ አይነቱ የታማኝነት መሰረት እየጸና ከሄደ ነጋዴው ለሸማቹ አምኖ፣ ተማምኖ ይሸጣል። ገዢው የግል ተጠቃሚ ከሆነ በእጁ የገባውን ዕቃ ውሎ አድሮ ያየዋል ። በሌላ ጎን ዕቃውን የወሰደው አካል አትራፊ ነጋዴ ከሆነ ስለ ዕቃው ምንነት ተማምኖ ለሌሎች በዕምነት ይሸጣል።
እንዲህ አይነቱ ጥብቅ ሰንሰለት ገበያውን በአመኔታ የሚመራ በመሆኑ ጤነኛ መሰረት አለው። ምርቶች ስያሜቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ያስችላል። በዚህ ሂደት ሸማቾች በገንዘባቸው ጥራትን ከእርካታ ይገዛሉ። በዚህ መስመርም ታማኝነት ይጎለብታል። ምርትና አምራቹ፣ ሻጭና ገዢው በወጉ ይገናኛል። ይህኔ የሀገርና ወገን ተጠቃሚነት ጎልቶ ይወጣል።
አንዳንዴ ግን በገበያው መስመር ታማኝነት ይሉት እውነታ ቃሉ ይሰበራል። ከአምራቹ ጀምሮ እስከተረካቢ ነጋዴው ያለው ሂደት በሀሰተኛነት ይነግሳል፤ ምርት በተመሳስሎ ተለውሶ ገበያውን ሲመራ ለሽያጭ የሚቀርቡ ግብዓቶች ስያሜያቸው ብቻ ይቀራል።
ብዙ ጊዜ የታዋቂ ምርቶች ስምን የያዙ ሸቀጦች ገበያውን ሲቆጣጠሩት ይስተዋላል። እነዚህ ይዘቶች ምንአልባትም የሀገር ውስጥ ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያገኙና ተመራጭነታቸው የጎላ ምርቶች ጭምር እንጂ።
በዚህ አጋጣሚ ገበያ ላይ የሚውሉ ምርቶች የሚዘጋጁት በተለየ ጥንቃቄና ስልት ነው ። ዕቃዎቹ ታይተው፣ ተዳሰው እንዳይለዩ የፈጠራ እጆች ይጠበቡባቸዋል። ማሸጊያዎቸው ፣ ፍጹም በሚባል ዘዴ ከዋናው ምርት እንዲመሳሰሉ ይሆናል።
ምርቶቹ በዓይነት ፣ በይዘት መንትያ እስኪመስሉ ተዋደው ለገበያ ይቀርባሉ። ይህ ከመሆኑ በፊት በላያቸው የሚለጠፈው የስያሜ መለያ ገበያውን በእጥፍ የሚማርክ ይሆናል። የቻይናውን ለአሜሪካ፣ የአሜሪካውን ለጣሊያን፣ ለሚክሲኮ ወዘተ እያሉ መሰየም የምርጫ ሁኔታ ብቻ ነው።
በሰዎች ዘንድ እውቅና የተሰጣቸው ዝነኛ ምርቶች በገፍ ሲገኙ ከዚሁ ተያይዞ የሚሰጣቸው አነስተኛ የዋጋ መጠን ገበያውን ፈጥኖ ለመቆጣጠርና እጥፉን ትርፍ ለማጋበስ አይነተኛ መንገድ ነው።
ሁሌም በገበያው ሂደት አመኔታ ከተጣሰ የማይሆን፣ የማይደረግ የለም። ዕውቀታቸውን ላልተገባ ዓላማ የሚጠቀሙ አንዳንዶች ስለገንዘብና ጥቅም ብዙ ይሆናሉ። እጅግ አስከፊው ጉዳይ ግን እንዲህ አይነቱ እጅ ከዚህ አልፎ ወደ ምግብ ሸቀጥ የተሻገረ ጊዜ ነው።
ብዙ ጊዜ በታዋቂ ምርቶች ስያሜ ገበያውን የሚሞሉ ሸቀጦች የሸማቹን ደካማ ጎኖች ግብ የሚያደርጉ ናቸው። የሚፈለገው ዕቃ ከገበያ በጠፋበት አጋጣሚ ዋጋቸውን በማይታመን ዝቅታ አስቀምጠው በድንገት ይከሰታሉ። ይህ አጋጣሚ ታዲያ ዓይንና ጆሮ ለመሳብ ጊዜ አይፈጅበትም። ከግብአቱ መጥፋት ጋር ተያይዞ የዋጋው አነስተኛ መሆን ገበያውን ፈጥኖ ያሸንፋል።
በማይታመን ስልት ምርትን አመሳስለው የሚሸጡ አንዳንዶች ህሊና ይሉትን አያውቁም። የሚያቀርቡት ምርት ገበያውን እስከያዘ ድረስ ያሻቸው ድረሰ ይጓዛሉ። ጊዜያቸው ያለፈባቸው ፣ የህጻናት ምግቦችና የወተት ዱቄት ለዚህ ድርጊታቸው ዋንኛ መሳሪያ የሚሆንበት አጋጣሚ የሰፋ ነው።
ይህ ምግብና ወተት ጊዜን ካስቆጠረበት ማሸጊያ ተገልብጦ ምርትና የአገልግሎት ማብቂያው በጥንቃቄ ወደተዘጋጀለት ተመሳሳይ ቁስ ተዛውሮ ለገበያ ይዘጋጃል። ሽያጩ የሚከወነው ቀድሞ ከነበረው እውነተኛው ምርት ባነሰ ዋጋ ነውና ፈላጊው በእጅጉ ይበረክታል።
‹‹ወዳጆቼ!›› እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ስለገንዘብ ሲባል የሚከተለውን የሕይወት ጥፋት ነው። ባብዛኛው ይህ አይነቱ ድርጊት የሚፈጸመው በመንደር ውስጥ በሚዘጋጅ ድብቅ ስፍራ ነው ሊባል ይችላል ። ይሁን እንጂ በተመሳሳይ በፋብሪካዎች ደረጃ ጭምር እንደሚከውን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ ስልት በአብዛኛው፣ ዘይት፣ ብስኩት ፣ ዱቄትና የመሳሳሉ ግብዓቶች ላይ የሚከወን ነው። አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ገበያውን ለመሻማት ደብቀው የሚከዝኗቸው ምርቶችም ጊዜ አልፎባቸዋል ተብለው አይወገዱም። እያንዳንዱ ሸቀጥ በራሱ ባህርይና ይዘት እየተለየ ከሌሎች በመዋሀድ ለገበያ ይቀርባል።
ምግብ ነክ የሆኑ ሸቀጦች ወደ ገበያው ሲገቡ የተለመደው የማሳሳቻ ስልት ተለጥፎባቸው ነው። ራስ ወዳድነት ሆኖ እንጂ አምራቾችም ይሁኑ አትራፊ ነጋዴዎች በታማኝነት ገበያውን ቢመሩ ወረታቸው አይጎድልም። ላልተገባ ትርፍ ሲባል የሚደረግ ስግብግብነት ለግለሰቡ ትርፍ ለአሀገርና ወገን ኪሳራን ያስከትላል።
ታማኝት የታከለበት ግብይት ሁሌም ጤናማ ነው። ይህ እሳቤ ዕውን ሲሆን አገር በሥርዓት ታድጋለች። ሸማቹ ያሻውን ያገኛል። ያልታመመ ምርት በወጉ ይደርሳል። አለመታመን፣ ከራስ አልፎ ሀገር ፣ወገንን አህጉር ዓለምን የሚጎዳ ነው ። መታመን፣ መተማመን ግን ፣ ትውልድ ያስቀጥላል። ከማንነት ህሊና ያሳድራል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም