አዲስ አበባ፡-
ዘጠኙ የኢትዮጵያ ብሄ ራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት በአዲስ አባላት እስካልተተኩ ድረስ ኃላፊነታቸውን የመወጣት ግዴታ አለባቸው ብሎ እንደሚያምን የሕግ፣ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት የቦርዱን የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባደመጠበትና ግብረ መልስ በሰጠበት ወቅት በቋሚ ኮሚቴው የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ እንደተናገሩት፤ ነባሩ የቦርድ አባላት በአዲስ እስካልተተኩ ድረስ ሥራቸውን በኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው ያምናል።በቀጣይ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊና በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ታማኝ የሆነ ቦርድ እንዲቋቋም የምክር ቤቱም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው።
የቦርዱ ጠንካራ ጎን ተብለው ከተለዩ መካ ከል አሰራሩን በማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ መንቀሳቀሱ፣ የቦርዱን ሠራተኞች አቅም ለመገንባት የተደረገው፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱ፣ የቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ፓርቲዎች እንዲፈርሙ ማድረጉ ተጠቃሽ መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ገልፀዋል።
ሰብሳቢዋ፣ እጥረት ካሏቸው መካከል የስነ ዜጋና የመራጮች ግንዛቤ ማጎልበት ሥራ ዝቅተኛ መሆን፣ የውስጥና የውጭ ተገልጋዮችን ቅሬታ ከመፍታት አንፃር በሪፖርት አለመገለፁ፣ህጋዊ ሆነው ከተመዘገቡ 16 ፓርቲዎች ውጭ ሌሎች መስፈርት አሟልተው እንዲመዘገቡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ሥራ አለመሰራቱ፣ የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አኳያ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰዋል።
ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ከተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች መካከልም የሲዳማ ህዝብ ውሳኔ ለምን ተጓተተ? የሚለው አንዱ ሲሆን፣ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከቦርዱ ዋና ዋና ተግባራትና ኃላፊነቶች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም መገንባት፣ ተሳትፎ ማሳደግና ማስተዳደር ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በፓርቲዎች መካከልም ውይይት ተከናውኗል። የጋራ ሰነድም ፀድቋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ሂደት ለማሳለጥም የህግ ማሻሻያ በመደረግ ላይ ሲሆን፣ ምዝገባው በሚደረግበት ጊዜ ሳንካ እንዳያጋጥም ሥራ ሲሰራ ቆይቷል።
‹‹ሌላው ዋና ተግባር የሥነ ዜጋ ትምህርት መስጠት ሲሆን፣ እዚህ ላይ አዲስ የትምህርት ይዘት በባለሙያ እንዲዘጋጅ አድርገናል። ውይይትም እንዲካሄድበት አድርገን ግብዓት አግኝተናል። የተቋሙን ሪፎርም የሚመራው መሰረታዊ የሆነ የህግ ማሻሻያ ሥራው በመሰራት ላይ ሲሆን፣ የህግ ማርቀቁን ሥራ የሚሰራው በጠቅላይ ዓቃቤ በኩል የሚመራው አካል ነው። በዚህ ጉዳይ ቦርዱም ጥሩ ግብዓት እንዲኖር አድርገናል። ፓርቲዎቹም በህጉ ላይ እንዲወያዩ በርካታ መድረኮችን አዘጋጅተናል።››ሲሉም ገልጸዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎችም ምላሽ ሲሰጡ እንደገለፁት፤ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን በተመለከተ ቦርድ በርካታ ማሻሻያ በማድረግ ላይ በመሆኑ በተሟላ የቦርድ አባልና አደረጃጀት ልክ ይከናወናል።የምርጫ ዝግጅት ሁሉ የሚሰራ ይሆናል።
በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን የማሻሻያ ሐሳብ ቦርዱ እንደሚወስድ ወይዘሪት ብርቱካን ገልፀው፤ ፓርላማውም ድጋፉን በማድረግ በኩል እንደሚተባበረው እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፣ቦርዱ በተደጋጋሚ በቋሚ ኮሚቴው ጥሪ ተደርጎለት እንደነበር ገልፀው፤ ምክር ቤቱን መፈለግ ያለበት በጀት አሊያም አዋጅ ለማፅደቅ ብቻ ሳይሆን ምክር ቤቱም ለመገምገም ሲጠራው ቦርዱ የመገኘት፣ ህግን የማክበር ግዴታ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
በአስቴር ኤልያስ