በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሳለን ብዙ በጎዎችን ተስፋ እናደርጋለን። ዲግሪ ስላለን ብቻ ህይወት ቀላል እንደሆነች ይሰማናል። ከዩኒቨርሲቲ እንደወጣን ወዲያው በከፍተኛ ደሞዝ ጥሩ ሥራ አግኝተን፤ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ለቤተሰቦቻችን ቤትና መኪና መግዛትን እናስባለን። ታናናሾቻችንን ጥሩ ትምህርት ቤት እያስተማርን ስናቀማጥል ይታየናል።እውነት ነው አብዛኞቻችን ከቤተሰቦቻችን ጫንቃ ወርደን የራሳችን ቤትና ቆንጆ መኪና መያዝን ወጥነነናል፣ አልመናል።
ከዩኒቨርሲቲ ከወጣን በኋላ ግን ህይወት እንዳሰብነው ቀላል አልሆነም። ስራ የለም፤ በየቦታው ለፈተና እንጠራለን መልስ የለም። በዚህ ፍለጋ ውስጥ እየኳተንበት ጫማ ቢንሻፈፍ፣ በየማስታወቂያ ሰሌዳው ያንጋጠጥንበት የሸሚዛችን ኮሊታ ቢያልቅ አይገርምም፡፡
የመጀመሪያ ሰሞን ከቤት ለስራ ፍለጋ ስንወጣ እጩ አምባሳደር መስለን፣ ከላይ እስከ ታች ዘንጠን ነው።በሂደትም በምረቃችን ቀን የተበረከቱልንን ሸሚዞችና ጥቂት የስራ መፈለጊያ የገንዘብ ኖቶች መመንዘር እንጀ ምራለን። የኮፒ ቤቱ ነገር ደግሞ አይወራ፤ ያልታወቀበት ስር ነቃይ ወጭ አለው፡፡
እናም በምረቃህ ማግስት ማስረጃህን በደርዘን በደርዘን ኮፒ አድርገህ ይዘህ መዞር ትጀምራለህ።ስትንከራተት መዋልህን የማያስተውሉት ቤተሰቦችህ ወጥተህ ስትመለስ ̋እህ እንዴት ነው ዛሬ?” በጥያቄ ይቀበሉሃል።አንተም ትደናበርና ምኑ ትላለህ። ̋ስራ ፍለጋው?̋ በቀናነት አስበው የጠየቁህ ጥያቄ ያናድድሀል፣ያበሳጭሀል፡፡
አንተ በአናትህ የዋለው ፀሐይ፤ ትራንስፖርት ማጣቱ፤ የየመስሪያ ቤቱ ጥበቃዎች ማመናጨቅ፤ ውል ይልሀል። ከኪስህ ገንዘብ አጥተህ ቤተሰብ ለመጠየቅ ከመሳቀቁ ጋር ተደማምሮ ሆድ ይብስሃል፡፡
ወዲያው ውስጥህ ‹‹ተናገር፣ ተናገር፣›› ይልሀል። ወላጅ አባትህን ለመዳፈር ታስባለህ። ‹‹እና ‘ምንድነው? የሄድኩት እኮ አንተ አቋቁመኸው የረሳኸውን ድርጅት ላስተዳድር አይደለም፤’ ለማለት ያምርሃል። ነገር ግን ፈጽሞ አትለውም። ጥገኛ ነህና ትውጠዋለህ። እየተቅለሰለስክ ‹‹ምንም አዲስ ነገር የለም፤ ብዙ ቦታ አመልክቻለሁ ››ትላለህ።‘ ማመልከት ብቻ ምን ያደርጋል፤ መቼ ነው የሚቀጥሩህ?’ ይሉሃል።
‹‹ኧረ ተረዱኝ ወገን አሁን አመለከትኩ ማለት ይቀጥሩኛል ማለት አይደለም።‹‹ገና የጽሁፍ፣ የቃል ፈተና አለ›› እያልክ ልታስረዳ ስታስብ ይደክምሃል።ስንቱን አስረድተህስ ትዘልቀዋለህ!፤ በየቦታው ያሉ ጥበቃዎች እንደሚገላምጡህ፤ ከእግር እስከ ራስህ እያዩ ወዴት ነው?̋ እንደሚሉህ አትናገርም።አንዳንዴ አዲስ ስራ ፈላጊ ስትሆን ከጽሁፍ ፈተናው ሳትደርስ ሊጥልህ የሚችለውን መመዘኛ ልብ አትልም። ጥበቃውን ኮራ ብለህ ‹‹ወደ ውስጥ ነዋ!›› ልትለው ትችላለህ፡፡
እንደዛ ካልከው እመነኝ አልቆልሃል። በያዘው ሽመል ወገብህን ሊልህ ይችላል።እና ልምከርህ ወዳጄ! ዋናው ፈተና የሚጀምረው ከጥበቃው በር ነው፡፡
‹‹ይቅርታ የኔ ጌታ›› ብለህ ንግግርህን ትጀምርና ‹‹እንደው የስራ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር፤ ለማመልከት መግቢያው በየት ይሆን?›› ትለዋለህ።ያኔ የልቡ ደጅ ወለል ይላል። በሩን ከፍቶ ቦታውን ጠቁሞ፣ እዛው አድርሶህ ይመለሳል። አንተም አባቴ ያራዳ ልጅ ከሆንክ አመስግነህ ዘው ነው፡፡
ውስጥ ከገባህም በኋላ ሁለተኛው ፈተና ይቀጥላል። የስራ ፈላጊዎችን ግለ መረጃ (ሲቪ) የምትሰበስበው ሰራተኛ ተጨንቀህ፣ ተጠበህ ‹‹ስለ ፈጣሪ፤ ለነብስ ይሆናችኋል ቅጠሩኝ›› ይል ይመስለውን ማመልከቻህን እያገላበጠችው ትቆያለች። ይህን ስታይ የተመራጭነት ስሜት ይሞላህና ትደሰታለህ፡፡
ወዲያው ግን እዚያ አስቀምጠውና ፎርም ሞልተህ ውጣ ትልሃለች። ማስረጃህን አንተ አሽሞንሙነህ እንዳመጣኸው ክብር የሚሰጠው ሰው የለም። ዞር ስትል ጦጣ አትዝለውም የሚያስብል፣ እንደ ጤፍ ክምር የተቆለለ ማስረጃ ታይና እንባህ ይቀራል፤ ግን አታለቅስም፡፡
የዛሬው ትዝብቴም ይህንን ሁሉ ውጣ ውረድ ታልፎ ስራው ተገኝቶ ‹‹እፎይ!›› ሲባል የሚከተለውን ሌላ ፈተና ያስቃኛል። በተለይ በባንክ ቤቶች ስለተቀጠሩ ጀማሪ ሰራተኞች።
አሁን አሁን የአብዛኞቹ ባንክ ቤቶች የገበያ ፉክክር ብልጠት ከተሞላበት የንግድ ስልት በፈረንጅኛው አፍ ‹‹strategic marketing›› መመራቱን የተወ ይመስላል። በየሱቁ፣ በየመንገዱ ከልመና ያልተናነሰ ድርጊትን ማየት ከተለመደ ሰነባብቷልና፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ፈር የለቀቀ ይመስላል፤ የባንክ ባለሙያዎች በደቦ መንገድ ይዞ የአነጋግሩን ልማድ። ይህ የቁጠባ ሂሳብ ‹‹ክፈቱልን›› ልመና ህብረተሰቡን ከማሰልቸት አልፏል። የባንክ ቤት ሰራተኞቹንም ላልተገባ ጫና ብሎም ማሸማቀቅ እየዳረገ ነው። ይህን ደግሞ በየአጋጣሚው መታዘብ ችለናል።
ይህን ተከትሎ በትላልቅ ህንጻዎች ላይ አስገራሚ ማስታወቂያዎች መነበብ ጀምረዋል።“የባንክ ቤት ሰራተኞች እና የኔ ቢጤዎች መግባት ክልክል ነው፣” በሚል። ሰራተኞቹን ያዩ ጥበቃዎችም ዝም አይሉም። ከዱላ ባልተናነሰ ቁጣ ፊት ነስተው እያመናጨቁ ያስወጧቸዋል።
ነገሩ በዚህ ብቻ አይቀርም፤ እነዚህ የባንክ ሰራተኞች ቀደም ሲል በማህበረሰቡ ዘንድ የነበራቸው ክብር አብሯቸው የለም። በየአጋጣሚውና በየማህበራዊ ሚዲያው እጅግ የሚያሸማቅቁ ተረቦችን ሲያስተናግዱ ማየት ተለምዷል።
ከሰራተኞቹ ከፍ ሲል ባንኮቹ በዚህ ልክ ህብረተሰቡን እስከማሰልቸት የደረሰ የገበያ ስልት መምረጣቸው ያስገርማል። ሂደቱን ረዘም ላለ ጊዜ መከተላቸው ደግሞ አግራሞትን ያጭራል፡፡
ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂና ፈጠራ በመነሳት በየእለቱ እንደማህበረሰብ የሚያስደንቁ ጊዜ ወለድ አገልግሎቶችን እንጠብቃለን። ይህ አይነቱ አካሄድ በዚህ ከቀጠለ ግን የኢንዱስትሪውን የለውጥ ጊዜ እንደ ሚያረ ዝመው ጥርጥር የለውም፡፡
ሁሌም ቢሆን ማህበረሰቡ ከአገልግሎት ሰጪ አካላት አዳዲስ የገበያ ስልቶችን ይጠብቃል። ሂደቱ አስተማማኝና ማራኪ ቢሆን ደግሞ ለሁሉም ይበጃል። ከዚህ ረገድ አንዳንድ ባንኮች እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። ዓለማችን መሽቶ ሲነጋ አፍ የሚያሲይዙ አዳዲስ ፈጠራዎችን ማየት ትሻለች። ይህን አይነቱ የተሰላቸ አሰራር ደግሞ የባንክ ኢንዱስትሪውን የገበያ ስልት የዳዴ ጉዞ አመላካች ነው ፡፡
ከሚሰማው መረጃ ማወቅ እንደሚቻለው በአንዳንድ ባንኮች አንድ የባንክ ሰራተኛ ከደንበኞች በወር በአማካኝ ከ40 እስከ 70 ደብተሮችን የማስከፈት ግደታ አለበት። እዚህ ላይ ለአንባብያን አንድ ጥያቄ ላንሳ፤ ምን ያህል የባንክ ደብተር ኖሯችሁ ምን ያህሉን ትጠቀሙበታላችሁ?
እንደ እኔ ፈልጌም ይሁን ለአሳዛኝ ፊቶች ስል ከከፈትኳቸው በርካታ ደብተሮች ከሁለቱ ውጭ ተጠቅሜ አላውቅም። እንደኔ የሰራተኞቹ መንከራተት እና እንድከፍትላቸው የሚያደረጉት የበዛ ጥረት መና መቅረቱ ሁሌም ያሳዝነኛል
ቁጠባ እጅግ አስፈላጊና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች እንዲቆጥቡ ሲባል ደብተር ማስከፈት ብቻውን ሚና አይኖረውም።
የባንክ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ያልተሰላቹና በስራቸው ደስተኛ የሆኑ የባንክ ቤት ሰራተኞች፤ ሊኖሩ ያስፈልጋል። አዳዲስ የገበያ ስልቶችና ልዩ የአገልግሎት አሰጣጦች መዘርጋታቸው ደግሞ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።እንዲህ መሆኑ ሥራ ይዘው ሥራ ፍለጋን ለሚንከራተቱ የባንክ ሰራተኞች አይነተኛ መፍትሄ ይሆናልና።ትዝብቴን ቋጨሁ!
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2015