የሀገር ባሕል አልባሳትን ለአዘቦት ቀናት ጭምር

 ኢትዮጵያውያንን ልብን ለሁለት ስንጥቅ የሚያደርጉ ውብና ማራኪ የሀገር ባሕል አልባሳት ባለቤቶች ናቸው።ይህም በተለይ በበዓላት ወቅት የምንመለከተው ሀቅ ነው።ከበአላት ውጪም የእነዚህ የባህል አልባሳት ተፈላጊነት በተለይ በሰርግ ላይ እየተፈለጉ ያለበት ሁኔታ አልባሳቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ እንዲመጣ እያደረገ ይገኛል።

ምክንያቱ ደግሞ የልብሶቹ ዲዛይን፣ ቀለም፣ ውበታቸው እና ለለባሽ ምቹ ተደርገው እየተዘጋጁ ያለበት ሁኔታ ነው።ቀልብን የሚስቡት እነኝህ አልባሳት ቀደም ሲል በባሕላዊ ዘዴ ብቻ ተሰርተው ሲለበሱ የኖሩ ቢሆንም፣ ለዲዛይነሮቻችን ምስጋና ይግባቸውና አሁን ባሕላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ እየዘመኑ የዘወትር ልብስ እንዲሆኑ ጭምር ተደርገው እየተመረቱ ይገኛሉ።

አልባሳቱ የሀገራችን ቱባ ባህል በቀላሉ ተመንዝሮ የማያልቅ ለመሆኑ ነጋሪ የማይሻው ሕያው ምስክሮች ናቸውም።እንዲህ ከዘመኑ ጋር አብረው የሚሄዱትን ልብሶች የሚያዘምኑትም የሀገራችን ዲዛይነሮች እየተበራከቱ መጥተዋል። ከዲዛይነሮቹ መካከል አንዷ ደግሞ የዛሬው ባለታሪካችን ዲዛይነር ደስታ እሸቱ ናት። ዲዛይነሯ ወደ ዲዛይን ሙያ ከገባች 14 ዓመታትን አስቆጥራለች።

ዲዛይነር ደስታ እንደምትለው፤ ቀደም ሲል ወደዚህ ሙያ ከመግባቷ በፊት በጸጉር ሙያ ላይ ትስራ ነበር።የዲዛይኒንግ ሙያ ውስጣዊ ፍላጎቷ ስለነበረ ሙያውን ለመማር ወስና የዲዛይኒንግ ትምህርቷን በቴክኒክና ሙያ ተቋማትም ተከታትላለች።ትምህርቷንም እንዳጠናቀቀች ነው በቀጥታ ወደ ሥራ የተሰማራችው።

ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመደራጀት ነው በተሰ ጣቸው መስሪያ ቦታ (ሼድ) ውስጥ ሥራዋን አሃዱ ብላ የጀመረችው።በጊዜው ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሆነውባት ነበር። በዚህ መልኩ መስራት ውጤታማ እንደማያደርጋትም ውስጧ ያሳምናታል።እናም ጥቂት ጊዜያትን ከሰራች በኋላ ለሥራዋ አመቺ የሆነ ቦታ ቀየረች።በራሷ ጥልፍ፣ ስፌትና ዲዛይን መሥራትም ጀመረች።የሀገር ባሕል ልብሶችን ዲዛይን ወደማድረጉም ገባች።

በራሷ ፍላጎት የምታሸምናቸው ልብሶች እንዳሏት ሁሉ ከሸማኔዎችና አንዳንዴም ከገበያ የምትገዛቸው ልብሶች መኖራቸውንም ትናገራለች። በእንዲህ አይነት መንገድ የምታገኘውን ልብስ ዲዛይን በማድረግ፣ ስፌትና ጥልፉን በመስራት ለተጠቃሚዎች ታቀርባለች። በዚህ ሁኔታ መስራት ከጀመረች ስምንት ዓመታት አስቆጥራለች። አሁን ላይ የሽመናው ሥራውን ብቻ ለሸማኔዎች ሰጥታ የተቀሩትን ስራዎች ራሷ ናት የምትሰራቸው።

ባህላዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ለሥራ የሚለበሱ፤ ለአለባበስ የሚመቹ ልብሶችን ዲዛይን አድርጋ ትሰራለች። እነዚህ አልባሳት ሲሰሩ ውብና ማራኪ እንዲሆኑ ታስቦባቸው ዲዛይን የሚደረጉ ናቸውም።ልብሶቹን ለመስራት ምንም አይነት የፋብሪካ ምርቶች አትጠቀምም።ለባሹ ፈልጎትና ወዶት የሚለብሰው አይነት ልብስ ለመስራት ጥረት ታደርጋለች።

የልብሶቹን ሽመና በተመለከተ ስትናገር ልብሶቹ የተለያዩ ዲዛይኖችን በመጠቀም እንዲያምሩ ተደርገው ይሰራሉ። እነዚህ ልብሶች ሲሰሩ ዘወትር እንዲለበሱ ተደርጎ ለአረማመድ፣ ለአለባበስ ፣ ለሥራ እንዲለበሱና እንዳያስቸግሩ ሆነው ነውም ስትል ታብራራለች። ልብሶቹ በተመሳሳይ ለሰርግ፣ ለተለያዩ ዝግጅቶች እና ፕሮግራሞች እንዲለበሱም ተደርገው የሚሰሩበት አጋጣሚ እንዳለም ታነሳለች። ሰዎች እንደ ፕሮግራሞቻቸው አይነት በሚፈልጉት ዲዛይን እንዲሰራላቸው ይደረጋልም ነው ያለችው።

ዲዛይነር ደስታ እንደምትለው፤ ቀደም ብላ ውስጧ የነገራትንና ያምራሉ ብላ ያሰበቻቸውን ልብሶች ዲዛይን አድርጋ ታስቀምጣለች። በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸውን ልብሶች ዲዛይን እያደረገች ለተጠቃሚው ታቀርባለች። ተጠቃሚው ቀደም ሲል ዲዛይን የተደረጉ ልብሶችን ከመረጠ በኋላ የሚፈልገው ካለ ይወስዳል። ካልሆነም በፍላጎቱ መሠረት ተሰርቶ ይሰጠዋል፡፡

የምትሰራቸው ልብሶች በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።አብዛኛዎቹ ልብሶች ለሁሉም ሰው የሚሆኑ (free size) የሚባሉ አይነቶች ሲሆኑ፤ ለምሳሌ፡- ለሴት ቁመት ይሆናሉ የሚባሉ ተመጣጣኝ የተባሉ ልብሶች በተለያዩ ዲዛይኖች ተሰርተው ይቀመጣሉ።ይህን ልብስ አይታ ለመግዛት የፈለገች ሴት አጋጣሚ ቁመቷ አጭር ሆኖ ቀሚሱ ቢረዝማት ወዲያወኑ እንዲያጥርላት ይደረጋልም ትላለች።

ልብሶችን ዲዛይን ስታደርግ በተለየ መልኩ የራሷን አዳዲስ ፈጠራ ለመጠቀም ጥረት እንደምታደርግ የምታስረዳው ዲዛይነሯ፤ እነዚህን ሥራዎቿን በቴሌግራም፣ በሚሴንጀር እና በመሳሳሉት ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች በማስተዋወቅ ገበያ ትስባለች። በዚህም በተለያዩ ውጭ ሀገራት የሚኖሩት ደንበኞችን ማፍራት ችላለች።ሥራዎቿን እያዩ የሚፈልጉትን ልብስ እየወሰዱላት፤ ትዕዛዝ እንደሚሰጧትና ልብሶቹ ሰርታ በዲኤችኤል ኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ፖስታ በኩል እንደምትልክላቸው ትገልጻለች።

‹‹በሀገር ባሕል ልብስ በፈለግነው መልኩ ብዙ ነገር መስራት ይቻላል።ቀደም ሲል ያሉ ዲዛይነሮችን ልብሱ ብዙ ነገር መሆን እንደሚችል ሠርተው አሳይተውናል።ልብሱ በጣም ያምራል፤ ሥራውም የሚወደድ ነው›› የምትለው ዲዛይነር ደስታ፤ ለባሹም የሚያምርበትና ወዶት የሚለብሰው እንደሆነ ትናገራለች።አሁን ላይ ብዙ ሰው ወደ ሀገር ባሕል አልባሳት እየተመለሰ በመሆኑ ውስጡ የወደደውንና ያማረው ልብስ መልበስ የሚችልበት እድል ተፈጥሯልም ብላ ታምናለች።

የልብሶቹ ዋጋ እንደልብሱ፣ እንደ ጥልፉና እንደ ጥበቡ አይነት ይለያያል የምትለው ዲዛይነሯ፤ ዋጋው ልዩ ልዩ ቢሆንም ልብሶቹ ግን ሁሉም ሰው ሊገዛቸው የሚችላቸው አይነት ናቸው።በተጨማሪም በትዕዛዝ ለማሰራት የሚፈልጉ ደንበኞች የልብሱን ዋጋ አይተው ነው ወደ ማሰራቱ የሚገቡት።ስለዚህም የባህል አልባሳት ዋጋ እንደፈላጊው የተመጣጠነ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላልም ትላለች።

‹‹ አሁን ባለው የልብስ ገበያ ሁኔታ ሥራው አንድ አይነት ሆኖ ዋጋ ግን እንደ መሸጫ ቦታው ይለያያል፤ በሙያ ላይ ያለ ሰው ሁሉ በተለይ ህዝቡ የራሱን ልብስ እንዲለብስ ለማድረግ ለልብሶቹ የተጋነነ ዋጋ ባያስቀምጥ ጥሩ ነው።እኛ ዲዛይን የምናደርጋቸውን ልብሶች ሁሉም ሰው ገዝቶ እንዲለብሳቸውና እንዲያምርባቸው ጥረት ማድረግ አለብን።የለባሹን የመግዛት አቅም ያላገናዘበ ዋጋ በማቅረብ ህብረተሰቡ ማማረር ተገቢ አይደለም፡፡›› ስትል ታስገነዝባለች።ልብሶቻችን ባሕላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ዘምነው እንዲለበሱ በማድረግ ኢትዮጵያዊ አለባበሳችንን ማቆየት ይጠበቅብናል።በዘመነ መልኩ ሰርተንና ዋጋውን ተመጣጣኝ አድርገንም በአለባበስ ትውልዱን መስራት ይኖርብናል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

አሁን ላይ ለአራት ሰዎች ሥራ እድል የፈጠረችው ዲዛይነር ደስታ፤ ይህንን ሥራ ሰፋ አድርጎ ለመስራት ገንዘብና መስሪያ ቦታ ግን ፈትኗታል።እነዚህ ሁሉ ከተመቻቹላት ከዚህም በላይ ሰዎችን መጥቀም እንደምትችል ጠቅሳ፣ ይህ ሲሆን ሥራዎቿን በስፋት ሰርታ ለተጠቃሚው ለማድረስ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጠርላት ታምናለች።በቀጣይም የሀገር ባሕል ልብስን ባህላዊ ይዘቱን ሳይቀይር ማዘመንና ሥራዎቿን ሰፋ አድርጋ ለመስራት ሀሳቡ አላት። እቅዷ ምርቶቿን ለሀገር ውስጥ ገቢ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግም ነው።ሥራዎቿን በማስፋት የተለያዩ ቅርንጫፎችን በመክፈት በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ መሆንንም ትሻለች።በዚህ ሥራዋ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሀገሩ ምርት እንዲኮራ እንደምታደርግበትም እምነቷ ነው።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 29/2015

Recommended For You