አንዳንዴ እንዲህ ነው !

ከሰሞኑ በተለያዩ የማኅበራዊ ገፆች አንድ ቪዲዮ ደጋግሞ ሲመላለስ አስተዋልኩ፡፡ አንዳንዴ እንዲህ መሰሉን ጉዳይ መመልከቴ ብርቅ አይደለም፡፡ አሁን ያየሁትን እውነታ ግን እንደዋዛ ጨረፍ አድርጌ ማለፍ አልሆነልኝም፡፡ ደግሜ ደጋግሜ አየሁት፡፡ እናም ከልብ አዘንኩ፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ አንዲት የታክሲ ተሳፋሪ ወጣት በድንገት ከእጇ መጥፋቱን ባወቀችው ስልኳ ምክንያት ክፉኛ ታለቅሳለች፡፡ እንደው ለማለት ያህል ‹‹ታለቅሳለች›› ልበል እንጂ ሁኔታዋ ከሚባለው በላይ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡

ማጋነን ባይሆንብኝ የልጅቷ ሁኔታ በድንገት የቅርብ ቤተሰቡን ሞት የተረዳ ያህል ከባድ ነው። ትጮኻለች፣ ትወድቃለች፣ ትነሳለች፣ በአጠቃላይ የምትይዘው፣ የምትጨብጠው ፣ ጠፍቷታል፡፡ አሁንም ሁኔታዋን ሳስበው ከልብ አዝናለሁ፡፡

እንደሚመስለኝ የእጅ ስልኳ ድንገቴ መጥፋት የተከሰተው በተሳፈረችበት ታክሲ ውስጥ ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው! እሷ የባነነችው ሰዎቹ ጉዳያቸውን ፈጽመው ወንዝ ከተሻገሩ ፣ ሌላውን ከጀመሩ ሆነ እንጂ፡፡

ምንአልባትም ይህች ልጅ ለሀገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ ትሆናለች፣ ምንአልባትም የምትሻውን ሁሉ የምታገኝበት የመክፈጫ ቁልፍ ያለው ከሞባይሏ ሆድ ይሆናል፡፡ ምናልባትም……. ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡

አዎ! በየጊዜው ልክ እንደእሷ ሁሉ ሀሳብ ጉዳያቸው በድንገት የባከነባቸው፣ ሳያስቡት ውጥን ዕቅዳቸው፣ ጭምር አብሮ የተሰረቅባቸው ወገኖች በሽ ናቸው፡፡ በእነ እንቶኔ የስርቆት ዘዴ ተታለው ፈቅዶ የመስጠት ያህል የእጃቸውን ያስረከቡ፣ እየረቀቀ ለመጣው የዝርፊያ ስልት መሞከሪያ የሆኑ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ቤትና ጊዜ ይቁጠራቸው እንጂ በየጊዜው የሚያስገርሙ የስርቆት ታሪኮችን ሰምተናል፣ እየሰማንም ነው ፡፡

ሀቁን ለመናገር እነዚህን እውነታዎች በየአጋ ጣሚው ደጋግመን ሰምተናቸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር በየቀኑ በሌሎች ላይ ሆኑ፣ ተፈጸሙ የሚባሉ የስርቆት ሥልቶችን አሳምረን እናውቃቸዋለን፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ራሳችን ሳንቀር የምናወራቸው፣ በወጉ የምንተርካቸው ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ይህን ስንል ደግሞ ከማወቅም አልፈን ለሚሰሙን ሁሉ ከችግሩ ‹‹ተጠንቀቁ›› ብለን ማሳሰቢያውን በመቸር ነው፡፡ አንዳንዴ ግን በወጉ አውቀናቸዋል፣ በምንላቸው ማታለያዎች ተሸውደን የችግሩ ዋንኛ ሰለባዎች ሆነን እንገኛለን፡፡ ትናንት ማሳሰቢያውን ለሌሎች እንዳልሰጠን፣ እንዳላስጠነቀቅን ሁሉ ‹‹ነቅተንበታል›› ባልነው ወጥመድ እኛው ተጠልፈን እንወድቃለን፡፡

እስከዛሬ በርካቶች ፍጹም ሊያስነቁ በማይችሉ የማታለያ ዘዴዎች ተጭበርብረዋል፡፡ የዝርፊያው ከዋኞች በጉዳዩ ሰፊ ጥናት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውም አብዛኞችን ለችግር ዳርጓል። ብዙዎቻችን እንደምንገምተው ደግሞ የጉዳዩ ተዋናዮች በቆሸሸ ልብስ የሚታዩ፣ የተጎሳቆሉና አፍላ የሚባሉ ወጣቶች አይደሉም፡፡ በተቃራኒው ጨዋታውን የሚዘውሩት ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ነፍሰጡር መሳይ እናቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እነዚህ የቡድን አባላት የዝርፊያውን ሂደት በማህበር ተደራጅተው ከያዙት በአንድም በሌላም የራሳቸው ተግባርና የሥራ ክፍፍል ይኖራቸዋል። ብዙ ጊዜ ዝርፊያውን በማታለል አስልተው ሲፈጽሙት በሌሎች ዘንድ ፍጹም ጥርጣሬን በማያሳድሩ ሰዎች እንደመሆኑ ድርጊቱም ተጠንቶበት የሚሠራ ይሆናል።

ብዙ ጊዜ እነዚህ የተደራጁ ቡድኖች ጥናታቸውን የሚተገብሩት በታክሲ ውስጥ ነው፡፡ በስፍራው ሲገኙ ደግሞ ከተሳፋሪዎቹ አብዛኞቹ እራሳቸው ይሆናሉ፡፡ ጥቂት ሰለባዎቻቸው ወንበር ይዘው ጉዞ በጀመሩበት አጋጣሚ ታዲያ ገንዘብ፣ ጌጣጌጥና ሞባይሎቻቸውን ከእጃቸው ለማስገባት የትወናው መድረክ ለእነሱ ቀላል የሚባል ነው፡፡

የፈረደበት በሰዓትና በቦታው አይገኝ እንጂ በመረባቸው የገባ ተሳፋሪ ብዙ ይደርስበታል። ሽማግሌዎች ብለን የምናከብራቸው፣ የዝርፊያው ቡድን መሪዎች ይሆናሉ፡፡ ነፍሰጡር መስለውን የምንንከባከባቸው ኪስ ለማጠብ እጃቸውን ያሰላሉ።ለምቾቷ አስበን ወንበር ያጋራናት ወጣት አሳልፋ ትሰጠናለች፡፡ ትወናው ተጀምሮ እስከሚያልቅ አንዳች ያልጠረጠረ ያለውን አስረክቦ፣ ኪሱን አሳጥቦ ይወርዳል፡፡

አንዳንዴ ነገሮች በዚህ ብቻ ላያልፉ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ዘራፊዎች እጅ የገባ ሁሉ በዝምታ ያለውን አስረክቦ የማይወጣበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ ባስ ባለ ጊዜ ዘራፊዎቹ ጥቃት አድራሺዎች ናቸው። ከኪስ ያገኙትን ኪሳቸው ካኖሩ በኋላ አሳቻ ቦታ ገፍትሮ ለመጣል ልባቸው ይጨክናል፡፡ ዝርፊያውን እየፈጸሙ የነቃባቸው ተሳፋሪ ካለ ደግሞ ውሳኔያቸው ከዚህ ሊከፋ ይችላል፡፡

እስከዛሬ በርካቶች በተለያዩ የማጭበርበር ስልቶች ጉድ ሆነዋል፡፡ ከዘመነኞቹ ‹‹ሿሿ›› ተብዬዎች ልማድ መለስ ስንል የቀደሙትን የማጭበር በር ስልቶች እናስታውሳለን፡፡ እነዚህኞቹ ብዙ ጊዜ የሰዎችን ሥነልቦና ተጠቅመው በደካማ ጎን የሚፈጸሙ ናቸው።

ይህ ዓይነቱ ስልት በአብዛኛው የሰዎችን ውሰጠት የሚቆጣጠር ከመሆኑ ጋር በርካቶች ሲታለሉና ሲዘረፉበት ቆይተዋል፡፡ ይህን ርዕሰ ጉዳይ ስናነሳ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውል የሚልብን የሎተሪ ደርሶኛልና የ‹‹መታወቂያ የለኝም›› ጉዳይ ነው፡፡

ልክ እንደሱ ሁሉ በተለምዶ ‹‹ቁጭ በሉ›› በሚል ስልት ሰዎችን ከአንድ ቦታ ጎልተው ገንዘብና ወርቆቻቸውን በመያዝ ዝርፊያ ስለሚፈጽሙ አታላዮች አንድ ሺህ አንድ ጊዜ የሰማን አንታጣም። ይህ የማጭበር ስልትም ካላጋነንኩት ዓመታትን ያስቆጠረ ዘዴ ነው፡፡

ችግሩ ይህን ጉዳይ ጠንቅቀን ማወቁ ላይ አይደለም፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ዓመታትን ስንሰማው በኖርነውና እኛም ሌሎችን ባስገነዘብንበት ስልት መልሰን መታለላችን እንጂ። ለዚህም ይመስላል ዛሬም በርካቶች ከዓመታት በፊት ‹‹አውቀነዋል፣ በልተነዋል›› ባሉት የዝርፊያ ስልት የሚሸወዱት። ለዚህም ነው አሁንም ድረስ የእነ ‹‹ቁጭበሉ›› እና ‹‹የሎተሪ ደርሶኛል›› ጉዳይ ያልደበዘዘው ፡፡

ለነገሩ የጉዳዩ ፈጻሚዎች የየጊዜው ስልት እንደየዘመኑ ይለያያል፡፡ ዛሬ ‹‹አወቅንባቸው›› ብለን ብንጠነቀቅ ነገ መልኩን ቀይረው ጉድ ይሠሩናል፡፡ አሁን ‹‹አንሸወድም›› ብለን ብንጀግን ቆይተው አቅም ዕውቀታችንን ያስጥሉናል፡፡

ትናንት የታክሲ መስኮትን ‹‹ዝጉልን›› በሚል ስልት ገንዘብ ሞባይል የተላፉ ተሳፋሪዎችን ታሪክ አሳምረን ሰምተነዋል፡፡ ነገ ተመሳሳዩ ሙከራ በእኛ ሲደገም ግን እንደነበረን መረጃ አስቀድመን አንጠረጥርም። እንደተባልነው ጥግ ተቀምጠን መስኮት ልንከፍት እንጠራራለን፡፡ በሽተኛ ለመምሰል የተወነችውን ሴት ልናግዝ እንጎነበሳለን፡፡

ምንአልባትም በጽሑፌ መግቢያ ላይ የጠቀስኩላችሁ ሴት ጉዳይ ከዚሁ ሀሳብ የተዛመደ ሊሆን ይችላል፡፡ በታክሲ ጉዟችን ለብዙ የዝርፊያ አጋጣሚዎች ሰለባ የምንሆንባቸው ጉዳዮች የሰፉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹን የስማችን ያህል እናውቃቸዋለን። ሌሎቹም ቢሆን ከጆሯችን የዕለት ወሬ የራቁ አይደሉም፡፡ ነገርግን እንደ አዲስ በነዚህ ድርጊቶች ስንጠለፍ እንውላለን፡፡

መቼም የሰው ልጅ በተፈጥሮው በማንነቱ ጉዳይ ሙሉ ሆኖ አያውቅም፡፡ ምን ጀግና፣ ‹‹ጠንቃቃ ነኝ›› ቢል በአንዳች አጋጣሚ ጎድሎ መገኘቱ አይቀሬ ነው ፡፡ ለዚህም ይመስላል አብሮት ባለው ጉዳይ ባዕድ መሆኑ፡፡ አይቶ ማስተዋል፣ አስተውሎ መጠንቀቅ ሲችል መዘናጋቱ፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ነው፡፡ ‹‹የፈሩት ይደርሳል፣ የተጠነቀቁለት ይሰበራል›› እንዲሉ፡፡

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You