ጉዳፍ ፀጋይ ከወዲሁ በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አተኩራለች

 ባለፈው የካቲት በፈረንሳይ ሌቪን የቤት ውስጥ ውድድር የአንድ ማይል የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር በጥቂት ሰከንዶች ብቻ በመዘግየቷ ሳይሳካላት ቀርቷል። በዚያው ወር በበርሚንግሃም በተካሄደው የቤት ውስጥ የ3ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ በተመሳሳይ 0 ነጥብ 09 ሰከንዶችን ብቻ ዘግይታ በሀገሯ ልጅ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን ክብረወሰን ሳትሰብር ቀረች፡፡ ጠንካራዋ አትሌት ዝግጅቷን ቀጥላ በ10ሺ ሜትር የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በኢትዮጵያውያን ማጣሪያ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ሮጣ በርቀቱ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ቻለች፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቃቷን እያሳደገች የምትገኘው ታታሪዋ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ከአጭር እስከ ረጅም ርቀቶች ድንቅ ብቃት እያሳየች በምትገኝበት የዘንድሮው የውድድር አመት ከሳምንት በፊት በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። በዚሁ ቻምፒዮና በ5ሺ ሜትርም ተጨማሪ ወርቅ ለማስመዝገብ ትልቅ ጥረት አድርጋ በመጀመሪያው ውድድር በገጠማት መጠነኛ ጉዳት ሜዳሊያ ውስጥ መግባት አልቻለችም።

ገና በታዳጊነት ዕድሜዋ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለችው ፈጣኗ ጀግና አትሌት ጉዳፍ፣ ከቡዳፔስት ስኬቷ በኋላ ፊቷን ወደ ኦሊምፒክ አዙራለች። ‹‹እንዳደረኩት ዝግጅት እቅዴ በሁለቱ ርቀት ሜዳሊያ ማስመዝገብ ነበር፡፡ ከነበርኩበት ወቅታዊ አቋም አንጻር ከሁለት በላይ ርቀት ላይ መሳተፍ እችል ነበር፤ ነገር ግን ውጤቱ ካቀድኩት ውጪ ሊሆን ቻለ፡፡ በእርግጥ ሩጫ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ያጋጥማል፤ በተለይ ሙቀት ሲሆን የእግር ጣቶች የማበጥና ውሃ የመቋጠር ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ እኔም የገጠመኝ ይኸው ነው፤ ምንም ማለት አይደለም›› በማለት በቻምፒዮናው የነበራትን ቆይታ ከቡዳፔስት መልስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግራለች።

ከረጅም ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ አረንጓዴውን ጎርፍ ባሳካችበት የ10ሺ ሜትር ውድድር ጉዳፍ የወርቅ ሜዳሊያውን ከዚህ በፊት በማትታወቅበት ርቀት በድንቅ ብቃት በማሳካቷ ‹‹በውድድሩ የ10ሺ ሜትር ርቀት አሸናፊ ለመሆን ነበር የገባሁት፡፡ ምክንያቱም አምና በ5ሺ ሜትር ወርቅ ሳገኝ ሕዝቤ የሰጠኝ ክብር እንዲሁም ከእኔ ብዙ ይጠብቅ ስለነበር ኃላፊነት ነበረብኝ፡፡ ስለዚህም ተስፋ ሳልቆርጥ እስከ መጨረሻው በመሮጥ ውጤታማ ልሆን ችያለሁ›› ብላለች።

ጉዳፍ ተጨማሪ ውጤት ለማስመዝገብ የጓጓችበት 5ሺ ሜትር ውድድር አስቀድሞም እጅግ ከባድ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው። የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ከወር በፊት የሰበረችውና የብቃቷ ጥግ ላይ የምትገኘው ኬንያዊት አትሌት ፌይዝ ኪፕየጎን ፉክክሩን ፈታኝ አድርጋዋለች። በሌላ በኩል በዚህ ርቀት እንዲሁም በሦስት ርቀቶች በመሮጥ አስደናቂ ብቃቷን በተደጋጋሚ እያስመሰከረች የምትገኘው ሆላንዳዊቷ ሲፋን ሃሰንም የዘንድሮውን የ5ሺ ሜትር ውድድር ብርቱ አድርገውታል። ይህም በምርጥ ብቃት ላይ የምትገኘው ጉዳፍን ተጨማሪ ስኬት እንዳታስመዘግብ አድርጓታል። ጉዳፍ ግን የውጤት ልዩነቱን የፈጠረው የኬንያዊቷ ብቃት ብቻ እንዳልሆነ ትናገራለች። ‹‹በዝግጅቴ ላይ ከዚህ በፊት ይጎድሉኛል ብዬ የማስባቸውን ክፍተቶች ሁሉ በመሙላትና ፍጥነት ላይም በመሥራት ነበር ወደ ውድድር የገባሁት፡፡ ነገር ግን ውጤት ላላመጣ የቻልኩት ባጋጠመኝ ጉዳት እንጂ በብቃት ምክንያት አይደለም፡፡ ይህንንም ተቀብዬዋለሁ›› በማለት ተናግራለች።

የዓለም ቻምፒዮና መጠናቀቁን ተከትሎ ጉዳፍ ከአመት በኋላ የሚካሄደው የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ትልቁ ትኩረቷ ሆኗል። ‹‹መጪው የፓሪስ አሊምፒክ እንደመሆኑ ቀጣይ ዝግጅቴ ለዚሁ ነው የሚሆነው። እንደሚታወቀው በኦሊምፒክ ያለኝ የነሐስ ሜዳሊያ ነው፡፡ ኦሊምፒክ ትልቅ የውድድር መድረክ እንደመሆኑ የየትኛውም አትሌት ሃሳብና አቅሙም የሚለየው በዚህ ውድድር ላይ ነው፡፡ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ለረጅም ዓመት በጥሩ አቋም ላይ የመቆየት ፍላጎት አለኝ፣ ለዚህም ያሉብኝን ክፍተቶች በመድፈን ጠንካራ ሆኜ ለመቆየት ጥረት አደርጋለሁ››፡፡ በማለት ቀጣዩ እቅዷን ተናግራለች።

ጉዳፍ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ስትወክል ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ እአአ በ2019 የዶሃ ቻምፒዮና የመጀመሪያ ተሳትፎዋ የነሐስ ሜዳሊያ ነበር ያስመዘገበችው፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ ኦሪጎን ላይ በ5ሺ ሜትር ወርቅ እንዲሁም በ1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት ነበረች፡፡ በአትሌቲክስ ሕይወቷ የሚቀራት ስኬት በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ትኩረት አድርጋ ለመዘጋጀት ተነስታለች።

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 26/2015

Recommended For You