በኢትዮጵያ የኮሜዲ ጥበብ መቼ እንደተጀመረ በታሪክ ማህደር የሰፈረ ማስረጃ ባይኖርም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት የአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር ጌጡ አየለን በድምፃዊነት ቀጥሮ በኮሜዲ ዘፈኖቹ በጊዜው የጥበብ አፍቃሪያንን አስፈግጓል። ምንም እንኳን የጌጡ አየለ የጊዜው የሙዚቃ ሥራዎች ፈገግታን የሚጭሩ የነበሩ ቢሆኑም በጊዜው የነበረውን ማኅበራዊ ህይወት በቀልድ እያዋዙ መልዕክቱን ለአድማጭ ተመልካች ያደርሱ ነበር። ከተለመደው የሙዚቃ አቀራረብም የተለዩ የነበሩ በመሆናቸው የጥበብ አፍቃሪያንን ቀልብ መሳብ ችለዋል።
ድምፃዊው ከሚያቀርባቸው የዘፈን ሥራዎች በተጨማሪ በቲያትር ቤቱ መድረክ አስቀድሞ በሚያሳያቸው አስቂኝ እንቅስቃሴዎችና በሚያቀርባቸው ንግግር አዘል ቀልዶች ተመልካቾችን አዝናንቷል። ይህም ድምፃዊው ከሙዚቃ ሥራው በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የኮሜዲ ሥራ የራሱን አሻራ እንዳስቀመጠ ያሳያል።
የኢትዮጵያ የኮሜዲ ጥበብ ሥራ ሲታወስ ግን ኮሜዲን እንደአንድ የሙሉ ጊዜ ሥራ ይዞ በመምጣትና አብዮቱን በማቀጣጠል ረገድ ኮሜዲያን አለባቸው ተካና ልመነህ ታደሰን የሚስተካከል የለም። ሁለቱ ኮሜዲያን የተለያዩ የኮሜዲ ዘውግ ያላቸውን የቀልድ ሥራዎቻቸውን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በማስቀረፅ ለአድማጭ ተመልካች አቅርበዋል።
ተመልካቹም አልፎ አልፎ በተለያዩ የጥበብ መድረኮች ከሚሰማቸው ቀልዶች ወጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን ችለው በወጡ የኮሜዲ ሥራዎች የቀልድ ጥማቱን አርክቷል። በጊዜውም ኮሜዲያን አለባቸው ተካና ልመንህ ታደሰ በአዝናኝ የኮሜዲ ሥራዎቻቸው ከፍተኛ ዝናን አትርፈዋል። ከጥበብ አፍቃሪያን በኩልም ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝተዋል።
እነ ኮሜዲያን አለባቸው ተካና ልመነህ ታደሰ በኮሜዲ ሥራቸው ሕዝቡን እያዝናኑ ለረዥም ዓመታት ዘልቀዋል። እንደውም የመጀመሪያዋ ሴት ኮሜዲያን እንደሆነች የሚነገርላትን እንግዳዘር ነጋን አካተው የኮሜዲ ሥራቸውን በማቅረብ ይበልጥ በኮሜዲ ሥራ ነግሰዋል። ሁለቱ የኮሜዲ ጥበብ ሰዎች የኮሜዲ ሥራን የሙሉ የጊዜ ሥራቸው አድርገው በመቀጠላቸው የኋላ ኋላ ለተተኪ ኮሜዲያን በር መክፈታቸው አልቀረም።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሳ ነበር። ኮሜዲያን ተስፋዬ ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ባህልና ቲያትር በዘፋኝነት ተቀጥሮ ሥራውን የጀመረ ቢሆንም፤ ከዘፈኑ ጎን ለጎን ኩምክናንም ደርቦ ይሠራ ነበርና ቀልድ ወዳዱ ኅብረተሰብ በሥራዎቹ ይዝናና ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደኮሜዲ ሥራው በማዘንበሉ ታዳሚያንን ይበልጥ እያዝናና መጣ።
በጊዜው ኮሜዲያን ተስፋዬ ይዞት ብቅ ያለው የኮሜዲ ሥራ አዲስ፣ የእያንዳንዱን ሰው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የሚያንኳኳ ብሎም ድምፁን አንዴ እንደ ሕፃን ሌላ ግዜ ደግሞ እንደወጣት፣ አንዴ እንደ አሮጊት ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ሽማግሌ እየቀያየረ ማቅረብ በመቻሉ የብዙዎችን ቀልብ በአጭርጊዜ ውስጥ መሳብ ችሏል።
በተለይ ደግሞ ተስፋዬ የቀልድ ሥራዎቹን በተለያዩ መድረኮች ለሕዝብ በማቅረቡ የጥበብ ታዳሚያን እንደልባቸው ቀልድ እንዲኮመኩሙ አስችሏል። ከዚህ ባለፈ ተስፋዬ ሥራዎቹን በካሴት በማስቀዳት ጭምር ለአድማጭ እንዲቀርቡ አድርጓል። አድማጩም ሥራዎቹን ደጋግሞ በማድመጥ አጣጥሟቸዋል። በዚህም ሰዎች ኮሜዲን በተለየ አንግል አይተውና ‹‹እንዲህም ዓይነት ቀልድ አለ እንዴ?›› ብለው ስቀዋል።
የተስፋዬ ካሳ አስደማሚ የቀልድ ሥራዎቹ ታዳሚያንን ዘና ፈታ እያደረጉና በኮሜዲ ጥበብ አዲስ ቀለም እየጨመሩ ዛሬም ድረስ ተወዳጅነትን እንዳተረፉ ዘልቀዋል። ምንም እንኳን ጥቂት ቢሆኑም ከኮሜዲ ሥራው ጎንለጎን የዘፈናቸው ዘፈኖቹም ዘመን ተሻግረው ዛሬም ድረስ ይደመጣሉ።
የኮሜዲያን ተስፋዬ ካሳ የኮሜዲ ሥራዎች እንዳሉ በዛው ተቀራራቢ ዘመን የተከሰቱት ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌና ሀብቴ ምትኩም በራሳቸው የኩምክና ስልት ብቅ ብለዋል። ኮሜዲያኑ የራሳቸውን ለየት ያለ የቀልድ ሥራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይዘው ከመምጣታቸው ባለፈ ሥራዎቻቸውን በቪዲዮ ካሴት በማስቀረፅ ለኮሜዲ ሥራ አድናቂዎች ይበልጥ መቅረብ ችለዋል። በዚህም በአድማጭ ተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተወዳጅነት አግኝተዋል። ቀደም ሲል ጥበብ አፍቃሪው በጥበብ መድረኮች ብቻ የሚያየውን የኮሜዲ ሥራ በቴሌቪዥን መስኮት እንዲመለከትና እንዲዝናናም እድል ሰጥተዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ኮሜዲያኖቹ ሥራዎቻቸውን በተከታታይ በማቅረባቸው ቀደም ሲል የነበረውን የኮሜዲ ሥራ ድርቅ አርጥበዋል። የእነርሱን እግር የተከተሉት እነ ኮሜዲያን አስረስ በቀለ፣ ጥላሁን እልፍነህና ዳንኤል ቁንጮም በኮሜዲ ሥራዎቻቸው የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።
በተለይ ከብሔራዊ ቲያትር የፈለቀውና በተወዛዋዥና በትያትር ትወና የጥበብ ሥራውን ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው ኮሜዲያን ክበበው ገዳ በዘፈን እያዋዛ ያቀርባቸው የነበሩ የኮሜዲ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመልካቹን ቀልብ በመሳብ በኮሜዲ ዘውግ አዲስ አብዮት አቀጣጥሏል። በዚሁ የኮሜዲ ሥራ ገፍቶበት በአጫጭር ድራማዎች የተለያዩ ቀልዶችን ለአድማጭ ተመልካች በማቅረብ ብዙዎችን አስፈግጓል።
ከዛም በኋላ እነ ኮሜዲያን ደምሴና ቤቴልሄም /ዋኑሶች/ ፍልፍሉ፣ ምትኩ ፈንቴ/ሀኪም አድነው/ እና አሰፋ ተገኘ /ባሻ/ በራሳቸው የኮሜዲ ቀለም መጥተው በኢትዮጵያ የኮሜዲ ጥበብ ዑደት እንዲቀጥል የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፤ እያሳረፉም ይገኛሉ።
በጌጡ አየለና በነ ልመነህ ታደሰና አለባቸው ተካ የተጀመሩ የኮሜዲ ሥራዎች ከነሱ ዘመን ተሻግረው አሁንም ድረስ በተወዳጅነታቸውና በአዝናኝነታቸው ቀጥለዋል። ቀልድ አፍቃሪው አሁንም ድረስ በእነርሱ ሥራ ይዝናናል፤ ይደሰታል። እንዲህ እንዲህ እያለ የኢትዮጵያ ኮሜዲ ጥበብ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሷል።
የኮሜዲ ጥበብ አሁንም መልኩን ቀይሮ በአዳዲስ የአቀራረብ ስልት ለአድማጭ ተመልካች እየቀረበ ቢሆንም አዳዲስ ፈጠራዎችን ይዞ በመምጣትና የኅብረተሰቡን የልብ ትርታ በሚነካ መልኩ እየተሠራ ባለመሆኑ የህልውና አደጋ የተጋረጠበት ይመስላል። አሁን ላይ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ኅብረተሰቡን ማሳቅ አዳጋች እየሆነ መጥቷል።
በርግጥ አሁንም አዳዲስና ወጣት ኮሜዲያን በተለየ አቀራረብ ሥራዎቻቸውን ለአድማጭ ተመልካች እያቀረቡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይግባውና በዩቲዩብና ቲክቶክ አጫጭር የኮሜዲ ሥራዎችን ሠርተው በመልቀቅ ለተመልካች ይበልጥ መቅረብ ችለዋል። ከዚህ ባለፈ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚዘጋጁ የስታንድ አፕ ኮሜዲ ፕሮግራሞች ሥራዎቻውን ለታዳሚያን በቀጥታ ያስተላልፋሉ። ከዚህ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲወዳደር ይህ ዘመን የኮሜዲ ሥራን በተለያዩ አማራጮች ለአድማጭ ተመልካች ማድረስ ምንኛ ቀላል እንደሆነ ያሳያል።
ዋናው ጥያቄ ግን አሁን ላይ ለኮሜዲ ሥራ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታና የቴክኖሎጂ አማራጭ ተጠቅመው ኮሜዲያን ይበልጥ አዝናኝና አስቂኝ ሥራዎችን ለሕዝብ ይዘው እየቀረቡ ነው ወይ? የሚለው ነው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ቀደምት የኮሜዲ ሥራዎችን ማንሳቱ በቂ ነው። እንዲህ እንደልብ ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበትና አንድ ለእናቱ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እጅግ እዝናኝና ድንቅ የኮሜዲ ሥራዎች ይቀርቡ ነበር። ታዳሚያንም ጥርሳቸው እስኪነቃነቅ በሥራዎቹ ይስቁ፤ ይፈነድቁ ነበር።
ዛሬስ? ዛሬ ቴክኖሎጂው አለ። የኮሜዲ ሥራዎች የሚቀርቡባቸው በርካታ የሚዲያ አማራጮች አሉ። ማህበራዊ ሚዲያዎችም የኮሜዲ ሥራዎችን በተለያየ መልኩ ለአድማጭ ተመልካች ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። አሁን ላይ ማኅበረሰቡ የደረሰበት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታም ተዝቆ የማያልቅ የኮሜዲ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ያስችላል። ማህበረሰቡ የደረሰበት አሁናዊ የንቃት ደረጃም ፈጠራ የታከለበትና አዝናኝ የኮሜዲ ሥራ ለማፍለቅ ያስገድዳል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ታዲያ አሁን ላይ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በርካታ የኮሜዲ ሥራዎች ለሕዝቡ እየቀረቡ ነው ማለት አይቻልም። ጥቂቶች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የኮሜዲ ሥራዎቻቸውን ለሕዝቡ ጀባ ቢሉም ካለው የሕዝብ ቁጥር ብዛት አንፃር የእነርሱ ሥራ ኢምንት ነው። በሥራዎቻውም በአብዛኛው ትንሽ ፈገግ የሚለው ከተሜው እንጂ በገጠር አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ አይደለም። ምክንያቱም የኮሜዲ ሥራዎቻቸው ሁሉንም ያማከሉ አይደሉምና።
በዚህ ጊዜ የኅብረተሰቡን የእለት ተእለት ህይወት የሚቃኙና ማኅበራዊ ህይወቱን የሚዳስሱ የኮሜዲ ሥራዎች በብዛት አይታዩም። ከዚህ ይልቅ በብዛት ፖለቲካ ላይ ያተኮሩና ነቆራ አዘል ቀልዶች ናቸው በየቦታው የሚደመጡት፤ የሚታዩት። በርግጥ ይህ ጊዜ ሀገሪቱ በተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለፈችበትና አሁንም ያለችበት ቢሆንም ከዚሁ ጎን ለጎን በሰዎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የኮሜዲ ሥራዎች እምብዛም አይታዩም።
ፖለቲካ ኮሜዲ የሚሠራበት አንድ ዘውግ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ፖለቲካ ላይ ተንተርሰው የሚሠሩ ቀልዶች በአብዛኛው ትኩረታቸው ፖለቲካዊ መልእክቱን ማስተላለፍ እንጂ በደምብ አስቆ ተገቢውን መልእክት ማስተላለፍ አይደለም። እንደውም አንዳንዶቹ የፖለቲካ ቀልዶች ችክ ያሉ ከመሆናቸው ቀልድነታቸው ተረስቶ የፖለቲካ ስብከት ሆነው ቁጭ ይላሉ። ሁሉም ግን እንዲህ አይነት ለዛ አላቸው ማለት አይደለም። በጣት የሚቆጠሩ ቢሆንም ለታዳሚያን ሳቅ እያጫሩ ፖለቲካዊ መልእክት የሚያስተላልፉ የኮሜዲ ሥራዎች አሉ። ለአብነትም የእነ በእውቀቱ ስዩምን፣ እሸቱ መለሰንና ተስፋሁን ከበደ/ፍራሽ አዳሽ/ የስታንዳፕ ኮሜዲ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል። አሁን የመጣው ኮሜዲያን ምናለ ያረጋልም የዚሁ ዘውግ ተጠቃሽ ኮሜዲያን ነው።
ሀበሻ ‹‹ፕራንክ›› በሚል በሰይፉ ፋንታሁንና በኢምሬሽኒስት /ድምፅና የሰውነት እንቅስቃሴ አስመሳይ/ ኮሜዲያን ‹‹ጃሚ›› ምን አልባትም ከአስር ዓመታት በፊት በታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ተጀምሮ ብዙዎችን እንዳስፈገገ ይታወሳል። በፕራንክ /የመሸወድ/ ቀልድ ዘውግ ይህ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቀዳሚው እንደሆነ ይነገርለታል። እንዲህ ዓይነቱ የኮሜዲ ሥራም ዛሬ ላይ በዩቲዩብ፣ ፌስቡክና ቲክቶክ ፕራንክ ለሚሰሩ ‹‹ኮሜዲያን›› በር ከፍቷል ማለት ይቻላል።
ነገር ግን አሁን ላይ በቲክቶክና በዩቲዩብ የሚሠሩ የፕራንክ /ሽወዳ/ ኮሜዲ ሥራዎች ከማሳቅ ይልቅ የሚያስደነግጡና ምን አልባትን ከሀበሻ ወግና ባህል ትንሽ ወጣ ያሉ ናቸው። የኢትዮጵያውያን የሥነ ልቦናና ንቃተ ህሊና ደረጃን ያገናዘበም አይደለም። በእንዲህ አይነቱ የኮሜዲ ሥራ ብዙዎች ሲደነግጡ አለፍ ሲል ደግሞ ራሳቸውን ጭምር ሲስቱ ተመልክተናል።
አሁን ደግሞ በቲክቶክ ቪዲዮ አራትና አምስት በመሆን ቀጥታ ገብተው የመቀጣጣት ጨዋታ የጀመሩም አሉ። ተጨዋቾች ይህን ያህል ይከፈልሃል በዱቄትና በዘይት ፊትህን ታጠብና መሰል ትእዛዞችን እንዲፈፅሙ የሚገደዱበት ጨዋታ መሆኑ ነው። በዚህ ጨዋታ የተባለውን ትእዛዝ የሚፈፅም ገንዘብ ይከፈለዋልና የተባለውን ይፈፅማል። በዚህ መሀል ሌላው ተመልካች ይዝናናል። እንግዲህ ይህም ቀልድ መሆኑ ነው። ለዛ የሌለው ቀልድ።
ቴክኖሎጂው ብዙ ነገሮችን አምጥቷል። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ኮሜዲ ሥራዎችም በዚሁ ቴክኖሎጂ የተቃኙ ናቸው። አሁን ላይ የሚታዩ ብዙዎቹ የኮሜዲ ሥራዎችም ከውጭ ሀገር የተቀዱ እንጂ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የተከተሉ አይደሉም። በኮሜዲ ሥራዎች ውስጥም አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች አይንፀባረቁም። የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁናቴም በጥልቀት አይዳስሱም።
ይህ ሲባል ‹‹ኮሜዲ ድሮ ቀረ›› ለማለት አይደለም። አሁንም ድንቅ የኮሜዲ ሥራዎችን ለአድማጭ ተመልካች እያቀረቡ ያሉ ኮሜዲያን አሉ። ግን ብዙ አይደሉም። አሁንም አዳዲስ ሃሳቦችን ይዘው ብቅ የሚሉና ተመልካች አድማጭን የሚያስፈግጉ ኮሜዲያን አሉ። ግን አንዴ ታይተው የሚጠፉ እንጂ የሚዘልቁ አይደሉም። ቴክኖሎጂውን በሚገባ ተጠቅመው ሥራዎቻውን ማቅረብ የተካኑ ኮሜዲያን አሉ። ግን ደግሞ ሥራቸው ለዛ ያጣና አንዳንዴም ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ከዚህ ከዚህ አንፃር ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ኮሜዲ የህልውና ስጋት ገጥሞታል የምንለው!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015