በማን አቆጣጠር?

የዓመቱ የመጨረሻ ወር የሆነውን ነሐሴን እነሆ እያገባደድን ነው። አዲስ ዓመት ልንቀበል በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውናል። አዲስ ዓመት ሲገባ ደግሞ የለመድነውን የዓመተ ምህረት አጻጻፍ ትተን ሌላ አዲስ ቁጥር እንጽፋለን። እዚህ ላይ ታዲያ የብዙዎች ስህተት በለመደ አእምሮ የቆዩበትን ቁጥር መጻፍ ነው። መስከረም ወር ላይ ይህ ስህተት ያጋጥማል። ደግነቱ በዚህ ዘመን የእጅ ጽሑፍ የምንጠቀምበት አጋጣሚ እምብዛም ስለሆነ በቅጽበት ማረም ይቻላል።

በዓመተ ምህረት አጻጻፍ ውስጥ እስከ 10 ዓመት ድረስ ከአራቱ ዲጂቶች (ከ1999 ዓ.ም ወዲህ ማለት ነው) የመጨረሻዋን ዲጂት ብቻ ነው የምንቀይር። በአሥር ዓመት አንዴ ግን የ10 ቤት የሆነችዋን ዲጂት እንቀይራለን። ለምሳሌ ከ1990 ጀምሮ እስከ 2000 ድረስ የ10 ቤት የሆነችው 9 ቁጥር ለ10 ዓመታት ያህል ትቀጥላለች። ከ2001 እስከ 2009 ድረስ ደግሞ የ10 ቤት የሆነችው 0 ቀጥላለች። ከ2010 ጀምሮ ደግሞ የ10 ቤት 1 ቁጥር ናት። እስከ 2019 ድረስ ትቀጥላለች። የ100 ቤት እና የ1000 ቤት የሆኑት ግን ለመቀየር ክፍለ ዘመን (100 ዓመት) እና ሚሊኒየም (1000 ዓመት) ይቆያሉ። ከ2000 ዓ.ም በፊት የተወለደ የዚህ ትውልድ አካል ዕድለኛ ሆኖ ሚሊኒየም አክብሯል።

ወደ ዋናው ትዝብቴ ልግባ። እነሆ አዲስ ዓመት እየመጣ ነው። አዲስ ቁጥር ልንጽፍ ነው፤ 5 ቁጥር በ6 ልትቀየር ነው። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር 2016 ዓ.ም ልንል ነው ማለት ነው።

እዚህ ላይ ታዲያ አንድ የምንታዘበው ነገር አለ። ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን የዘመን አቆጣጠር ያለን…›› እያልን እንፎክራለን። የዘመን አቆጣጠራችንን የኮራንበትን ያህል ግን አንጠቀምበትም፤ የውጭው ናፋቂ ነን። በቀላሉ የጓደኞቻችሁን (የራሳችሁንም ቢሆን) ስልክ ተመልከቱ! ሰዓቱ የሚሞላው በፈረንጅኛው አቆጣጠር ነው። ቀኑ እና ዓመተ ምህረቱ የሚሞላው በፈረንጅኛው አቆጣጠር ነው። ስልኩ የኢትዮጵያን አቆጣጠር አይሰራም ይሆን?

በተለይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋማት ውስጥ በሚሰሩ ጓደኞቼ ደግሞ ከዚህም በላይ የታዘብኩት ነገር አለ። የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ይጠፋባቸዋል። ‹‹ዛሬ ቀን ስንት ነው?›› ተብለው ቢጠየቁ ‹‹ነሐሴ 24›› ከማለት ይልቅ ‹‹August 30›› የሚለው ቶሎ ትዝ ይላቸዋል። ምክንያቱም የሥራ እንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ ከውጭው ጋር ነው የሚቀራረቡት። ደብዳቤዎችና ሌሎች የሥራ ሰነዶች የሚጻፉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። የወር ደመወዛቸውን የሚቀበሉት በውጭው አቆጣጠር ነው። በእነዚህ ተፅዕኖዎች ምክንያት ከኢትዮጵያው አቆጣጠር ይልቅ ለውጭው ይቀርባሉ።

የመንግሥት ተቋማት ሆነውም የውጭው አቆጣጠር ተፅዕኖ ያለባቸው አሉ። እንዲያውም ከመገናኛ ብዙኃን በስተቀር አብዛኞቹ በውጭው አቆጣጠር የሚጠቀሙ ናቸው። ለምሳሌ ባንኮች ደረሰኝ ላይ ቀን የሚጽፉት በውጭው አቆጣጠር ነው። ብዙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቀንና ዓመተ ምህረት የሚጻፈው በውጭው አቆጣጠር ነው። በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ሁሉ በውጭው አቆጣጠር ነው። በእርግጥ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማስተማሪያ ቋንቋውም እንግሊዝኛ ስለሆነ ከተፅዕኖው ነፃ መሆን አይቻልም፤ ቢሆንም ግን ቢያንስ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሚወጡና በሀገር ውስጥ ቋንቋ በሚጻፉ ማስታወቂያዎች የኢትዮጵያን መጠቀም ይቻል ነበር።

የዘመን አቆጣጠርን እያደበላለቁ መጠቀም ለመረጃ ስህተትም ይዳርጋል። አንድ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ስህተት ላስታውሳችሁ። እንደሚታወቀው በእንግሊዝኛ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኝ ዓመተ ምህረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነው። በእንግሊዝኛ ስንጽፍም ይህንኑ ዓመተ ምህረት ነው መጠቀም ያለብን። ምናልባት የኢትዮጵያን ዓመተ ምህረት መጥቀሱ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ E.C የሚለው የተለመደ አገላለጽ አለ። ልብ ብላችሁ ከሆነ ግን ይሄን ሳይጠቀሙ በኢትዮጵያ ዓመተ ምህረት በእንግሊዘኛ የሚጽፉ አሉ። ይሄ ነገር ለስህተት ይዳርጋል።

ለምሳሌ ዓመተ ምህረቱ ያለፈ ከሆነ የሰባት ወይም የስምንት ዓመት ልዩነት ተሳስተናል ማለት ነው። ምናልባት ዓመተ ምህረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ወደፊት ከሆነ ግን ከጽሑፉ ዓውድ ልንረዳው እንችላለን። ለምሳሌ ‹‹በ2018 በተደረገው…›› የሚል የሆነ ሁነት ብናነብ የኢትዮጵያ 2018 ገና ወደፊት ስለሆነ በአውሮፓውያኑ ነው ማለት ነው። ‹‹በ2010 በተደረገው… ›› ቢባል ግን የአውሮፓውያኑም የኢትዮጵያም 2010 አልፏል። ምናልባትም ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሆኖ ከነዓመተ ምህረቱ ካላስታወስነው በስተቀር ለስህተት እንዳረጋለን።

በተመሳሳይ፤ በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥ አቆጣጠሩ የውጭ ከሆነ እ.ኤ.አ ብሎ መግለጽ የተለመደ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህን ሳይጠቀሙ በውጭው አቆጣጠር ይጽፋሉ። ይሄም ከላይ የገለጽኩትን አይነት ስህተት ያስከትላል። እንደምልክት የሚያገለግል ነገር ደግሞ አለ። ‹‹ዓ.ም›› የሚል ካለው አቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ነው፤ ከሌለው በአውሮፓውያኑ ነው የሚባል ነገር አለ። ይሄ አከራካሪ ስለሆነ አስተማማኝ አይሆንም! የውጭውም ‹‹ዓ.ም›› ይባላል የሚሉ አሉ። ምክንያቱም በእንግሊዘኛ B.C እና A.D የሚባል ነገር ስላለ A.D ‹‹ዓ.ም›› እንደማለት ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ፤ ለማንኛውም ይሄኛው ዘዴ የማሳሳት ዕድሉ ሰፊ ነው።

በነገራችን ላይ ጉዳዩ የሀገር ውስጥ ሆኖ የውጭውን አቆጣጠር እንዲንጠቀም የሚያስገድዱን ነገሮች አሉ። ይሄውም በራሳችን አላዋቂነት የመጣ ነው። ብዙ ነገሮቻችን በውጭዎች የተጻፉ ናቸው። ስለዚያ ጉዳይ መረጃ ፈልገን ወደ በይነ መረብ (ኢንተርኔት) ስንገባ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ታሪክ እናገኛለን። በሀገር ውስጥ ቋንቋ ስንፈልገው ግን ዘረኝነትና የፖለቲካ ብሽሽቅ ነው የሚያመጣልን። ለምሳሌ የአንድ ታዋቂ ሰው ስም አስገብታችሁ ብትፈልጉ፤ ‹‹የእገሌ ስውር ሴራ፣ የእገሌ ገመና ሲጋለጥ…›› የሚሉ አሉቧልታዎችን ነው የሚያመጣልን። በእንግሊዝኛ ስትፈልጉ ደግሞ የሕይወት ታሪኩን፣ የሰራቸውን ሥራዎች፣ የትምህርት ደረጃውን… ይነግረናል። በእነዚህ ምክንያቶች እንግሊዝኛውን ለመጠቀም እንገደዳለን።

እንዲህ የውጭውን አቆጣጠር የመለማመዳችንን ያህል ግን ለምን ወደ ሀገርኛ መተርጎም አልቻልንም? ቀኑ እና ወሩ ከተጠቀሰ በውጭ አቆጣጠር የተጻፈን ጽሑፍ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ማስቀመጥ በጣም ቀላል ነው። በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ያለን የቀን ልዩነት ይታወቃል። ያለን የዓመተ ምህረት ልዩነት ይታወቃል። ለምሳሌ ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ወራት ውስጥ የሰባት ዓመት ልዩነት ነው ያለን። በእንግሊዝኛ ጽሑፍ የተገለጸው ወር ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ከሆነ ከዓመተ ምህረቱ ላይ ሰባት መቀነስ ነው። ከጥር በኋላ የፈረንጆች ዓመት ስለሚታደስ ከጥር እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ደግሞ ልዩነታችን ስምንት ስለሆነ ስምንት መቀነስ ነው። ቀኑም ልክ እንደዚሁ! ለምሳሌ አሁን በነሐሴ ወር ያለው ልዩነት ስድስት ሲሆን በመስከረም ወር ደግሞ 10 ነው።

ይሄኛው አቆጣጠር ውሰብሰብ ስለሚል ሁሉም ይጠቀመው ማለት አይቻልም፤ ቢያንስ በምርምር ላይ ያሉ ሰዎች ግን እንዴት ይሄ ይጠፋቸዋል? እሺ ይሄም ይቅር! ሀገራዊ ሁነትን በራስ አቆጣጠር ቢጻፍ ምን ችግር አለው? ምናልባት መሰልጠን እየመሰለን ነው አይደል? ሰው እንዴት የራሱ አኩሪ ታሪክ እያለው የሌላው ይናፍቀዋል?

እዚህ ላይ ግን አንድ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ማመስገን እፈልጋለሁ። የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በቅርቡ የሕይወት ታሪካቸውን ጽፈው ነበር። የእርሳቸው የሕይወት ታሪክ የኢትዮጵያና የዓለም ታሪክ ማለት ነው። እኚህ ምሁር በመጽሐፋቸው ምረቃ ላይ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ ዓለም አቀፍ ሰነዶችን አገላብጠው መጽሐፉን ሲጽፉ ሰፊ ጊዜ የወሰደባቸው ዓመተ ምህረቶችን ወደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር መመለስ ነበር። የሀገሬን ሁነት በውጭ አቆጣጠር አልጽፍም ብለው ነው ይህን ያደረጉት። ይህ የኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ሁሉ ልምድ ይሁን!

 ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015

Recommended For You