በሀገራችን በፋሽን ዘርፍ ላይ ትምህርትና ሥልጠና ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ ነው። ኮሌጁ ተማሪዎችን በበርካታ ዘርፎች እያሠለጠነ ይገኛል። ከእነዚህ ዘርፎች መካከል በጋርመንት ትምህርት ክፍል የሚሰጠው የፋሽን ዘርፍ አንዱ ነው። የትምህርት ክፍሉ በፋሽን ኢንዱስትሪው ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አዳዲስ ሃሳቦችን በማከል የተለያዩ የፋሽን ሥራዎችን ይሠራል።
ትምህርት ክፍሉ ባሉት የጋርመንት፣ የቴክስታይልና የሌዘር ዘርፎች በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ አንድ ርምጃ ወደፊት ሊያስኬዱ የሚችሉ ሥራዎችን ይሠራል። ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገርም ለፋሽን ትርኢቶች ውድድሮች የሚሆኑ አልባሳትን ያዘጋጃል። በየዓመቱ በሚካሄደው ‹የቴክኒክ ሳምንት› በፋሽን ትርኢት ላይ ያዘጋጃቸውን አልባሳት ይዞ በመቅረብም ይወዳደራል። በዚህም በየዓመቱ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን አንደኛነቱን አስጠብቆ ቀጥሏል።
ኮሌጁ በፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የምትናገረው የኮሌጁ የጋርመንት ትምህርት ክፍል አሠልጣኝ ሀዊ ረፊሶ ፤በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ትገልጻለች። ሀዊ እንደምትለው፤ ኮሌጁ በፋሽን ዘርፍ በሦስቱ የትምህርት ክፍሎች የሚሰጡትን ትምህርቶች አንድ ላይ በማቀናጀት በተግባር ተርጉሞ በፋሽን ትርኢት መልኩ እንዲቀርቡ እያደረገ ነው። ኮሌጁን ለየት የሚያደርገው የሀገር ውስጥ ምርቶች መጠቀሙ እና በቀላሉ የሚገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም በጣም ውብ ደረጃቸውን የጠበቁ አልባሳትን ማምረት መቻሉ ነው።
ለፋሽን ትርኢት የሚዘጋጁት አልበሳት ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚዘጋጁ ናቸው። እነዚህ አልባሳት በአብዛኛው የሚሠሩት በተማሪዎች ሲሆን፤ ተማሪዎቹ ክህሎታቸው የሚገልጹበትና የሚያሳደጉበት ነው። ተማሪዎቹ ዲዛይኖችን በመፍጠር፣ ያሉትን ዲዛይኖች በማስተካከል የሀገራችን ምርት በሆኑ ጨርቆች የተለያዩ አልበሳትን መሥራት እንደሚቻል የሚያሳዩበት ነው። በአሠልጣኞቻቸው ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
በኮሌጁ በፋሽን ትርኢቱ መስፈርቶች መሠረት የሀገር ውስጥ ምርቶች በመጠቀም፣ ከባህላዊ ይዘት ያላፈነገጡ አልባሳት ዲዛይን ማዘጋጀት እና ባህላዊን አልባሳትን ከዘመናዊ፣ እንዲሁም ዘመናዊን አልባሳት ከባህላዊ ጋር በመቀላቀል ዲዛይን በማድረግ ማራኪ አልባሳትን ያመርታሉ።
በፋሽን ትርኢት ላይ ለመሳተፍ ቅድሚያ በተመስጦ ሃሳብ መፍጠር ያስፈልጋል። ተማሪዎች የፈጠሩት የተመስጦ ሃሳብ አልባሳትን ዲዛይን እንዲያደርጉ ይረዳል። በተመስጦ ፈጠራው አልባሳት ቆዳ ከጨርቅ ጋር በመደባለቅ የሚሰሩ ሥራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በየትምህርት ክፍሉ ያሉ ተማሪዎች ተቀናጅተው በአንድ ላይ እንዲሰሩ እንደሚደረግ ትገልጻለች።
ዘርፉ የሚፈልገው የተለያዩ ፈጠራዎች አሉ የምትለው ሀዊ፤ በወዳደቁና በማያስፈልጉ ግብዓቶች፣ ለአይን የሚስቡና ማራኪ አልባሳቶች ይሰራሉ። በፋሽን ትርኢት ላይ የሚያስፈልጉ አልባሳትን ዲዛይን ለማድረግ አስራ አምስት ቀናት ይፈጃል። ሳቢ የሆኑ ሃሳቦች ተፈጥረው፣ የሚሰሩ ዲዛይኖች ተዘጋጅተው ፤ ንድፎች ተዘርግተው ወደ አልባሳት ለመቀየር ጨርቆችን ለመግዛት ያለው ሂደት ክፍተት ይፈጠራል እንጂ በትክክል ሁሉም ሂደቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚሄዱ ከሆነ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ መጨረስ ይቻላል ስትል ታብራራለች።
ሌላው ለፋሽን ትርኢቱ አስፈላጊ የሆኑ ተጓዳኝ ምርቶች (አክሰሰሪዎችን) ማለት እንደ ቦርሳ፣ ጫማዎች፣ የእጅ ጌጦች፣ የጆሮ ጌጦች፣ ጸጉር ላይ የሚደረጉ ጌጦች፣ የእጅ ጓንት ፣ የፊት ማስክ እና የመሳሳሉት ሁሉም አብረው የሚሄዱ ቁሳቁስ ስለሆኑ እንዲኖሩ ያስፈልጋል። ስለዚህ ለእነዚህን ሁሉም መያዝ የሚያስችል ሥራ አብሮ ይሰራል።
ሀዊ እንደምትለው፤ አልባሳቱ የሚዘጋጁት ለአንድና ለሁለት ለባሾች ብቻ ተብለው አይደለም። አነሰ ቢባል ሶስት ለባሾች (ሞዴሎች) የሚለብሷቸው አልባሳት ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በኮሌጁ እስከ አስር የሚደርሱ ለባሾች የሚለብሱት ልብስ ተዘጋጀቷል። አልባሳቱ በሁሉም የእድሜ ክልል ከሕጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂዎች ድረስ ያሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሚለብሷቸው ናቸው። ይህም ሁሉም ሰው መልበስ እንደሚችል ለማሳየት ይጠቅማል። ከዚህ በተጨማሪም ከተለመዱ አልባበሶች ውጭ ያሉ አልባሳትንም እንዲሁ ማካተት አለባቸው። ቀደምሲል የተለመደው ሱሪ ከሆነ በጉርድ ቀሚስ እና በተለያዩ ነገሮች በመቀየር መልበስ እንደሚቻል ማሳየትን ይጠይቃል። እነዚህን ሁሉ ያሟሉ ለሁሉም የሚመጥኑ አልባሳት እንደሚዘጋጁ ትናገራለች።
‹‹ብዙ ጊዜ የምንሰራቸው ሥራዎች የፋሽን ኢንዱስትሪውን ሊመጥኑ የሚችሉ አልባሳት ስለሆኑ ተመራጭ ናቸው።›› ስትል ትገልጻለች። ፋሽን በባህሪው የሚደገም ኡደት ስለሆነ በተለያየ መልኩ መላልሶ በመሥራት ብቻ ሳይሆን ዘመኑ የሚፈልገው የፋሽን አይነት ምንድነው የሚለውን እንጨምርበታለን። ዘንድሮ በፋሽን ትርኢቱ ላይ ያቀረብናቸው አልባሳት በተለየ መልኩ የተመሰጥንባቸውን ሃሳቦች፤ ያልተለመዱ ግን መልዕክት ሊያስተላልፉ የሚችሉ ነገሮችን አጎልተን አሳይተናል ትላለች። ለምሳሌ ከተመሰጥንባቸውና ከተጠቅምንባቸው ሃሳቦች አንደኛው ሰፌድ ነው። በሰፌድ የአንድነትና የክብር ምልክትን ገልጸንበታል። ሌላው ደግሞ መጪው የክረምት ጊዜ መሆኑን ለመግለጽ ዝናብን የሚያሳዩ አልባሳት በጋቢ መልኩ ሰርተን በማሳየት መልዕክት ለማስተላለፍ ተጠቅመንበታል›› በማለት ገልጻለች።
በአልባሳቱ ለሀገርና ፤ ለሰው ልጆች ይጠቅማሉ ያሏቸውን መልዕክቶች ማስተላለፋቸውን ጠቅሳ፤ ትኩረታቸው የነበረው በአልባሳቱ መልዕክትን ማስተላለፍና ሀገር በቀል በሆኑ ምርቶች ባህላዊ ይዘቶችን በጠበቀ መልኩ አልባሳትን ማዘጋጀት መሆኑንና ይህንንም ማድረጋቸውን ትገልጻለች።
‹‹ለፋሽን ትርኢቱ የተጠቀምንባቸውን አልባሳትንም ሆነ ተጓዳኝ ምርቶችን (አክሰሰሪዎችን) ትርኢቱ ካለቀ በኋላ ባሉን የማሳያ ቦታዎች ላይ እንዲታዩ እናደርጋለን›› የምትለው ሀዊ፤ አብዛኛውን ጊዜ ኮሌጁን ለመጎብኘት የሚመጡ ኢንተርፕራይዞች አልባሳቱን አይተው የሚፈልጓቸው ዲዛይኖች ካሉ በማሳየት አምረተውት (አብዝተው) ለሽያጭ እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ ትገልጻለች። ለጉብኝት የሚመጡ ተማሪዎችም እያዩ እንዲማሩበት ይደረጋል ብላለች።
‹‹ግባችን ብቁ የሆኑ ሠልጣኞችን በማፍራት የፋሽን ኢንዱስትሪውን ወደፊት እንዲራመድ ማስቻል ነው›› የምትለው ሀዊ፤ አንድ ነገር በመቅዳት አንዱን ዲዛይን ወይም ባሕል ማንጸባረቅ ላይ ብቻ ትኩረት እንደማይደረግም ትናገራለች።
ሰዎች ከሚበሉት ይልቅ ለሚለብሱት መጨነቅ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ይታያል የምትለው ሀዊ፣ ፋሽን ደግሞ ዛሬ ታይቶ ነገ የሚጠፋ ሳይሆን ሁሉ ጊዜ ቀጣይነት ያለው ፤ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የሚጋብዝ፤ አእምሮን ሁሌም ለፈጠራ ዝግጁ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ታመለክታለች። ስለዚህ በፋሽን ኢንዱስትሪው በኩል የተሻለ በመሥራትሀገርንም ራስንም መጥቀም ይቻላል ስትል ገልጻለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015