ኤፍ ቢ ሲ፡- ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርቷን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ባለ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ መድረክ ላይ አቅርባለች።
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በመካሄድ ላይ ባለው የግምገማ መድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በሪፖርታቸውም በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት የሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል መሰረታዊ እርምጃዎች መውሰዷን አስረድተዋል።
ዶክተር ጌዲዮን በሪፖርታቸው፤ መንግ ስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ለአብነት የጠቀሱ ሲሆን፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በፀረ ሽብር ህግ አማካኝነት ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች እና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በምህረት እና በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱ መደረጉን አብነት ጠቅሰው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበረውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጆች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፤ ይህም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነፃነት የሚሰጥ መሆኑን እና የሲቪክ ማህበራትም የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲን ለማስረፅ የሚሰሩትን ስራ በተሻለ መልኩ እንዲያከናወኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በህዝቡ ዘንድ የጋራ መግባባትና ብሄራዊ እርቅን ለመፍጠር ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሰራበት እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ ይህም የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ቁልፍ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።
የትምህርትን ዘርፍ እና የአዳዲስ መንገድ ግንባታን ለሁሉም አካባቢዎች የማዳረሱ ስራ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል ያሉት ዶክተር ጌዲዮን፤ ውጤታማ የሆነው የኢትዮጵያ ሴፍቲኔት መርሃ ግብ ርም ከአፍሪካ ግዙፉ የማህበራዊ ዋስትና ፕሮግራም መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የሴቶችን እኩል ተሳታፊነት ለማረጋገጥም ውጤታማ ስራዎች መስራቷን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ ከነዚህም መካከል በመንግስት ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን እና በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት መሾማቸውንም ለአብነት አንስተዋል።
በመድረኩ እየተሳተፉ ያሉ በርካታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል የሰራችውን ስራዎች አድንቀዋል። በተለይም በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ሪፎርም አማካኝነት የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱ እና ከሽብር ጋር ተያይዞ ተከሰው በእስር ላይ የነበሩ እና ተፈርዶባቸው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ከእስር እንዲወጡ መደረጉ መልካም መሆኑን አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ መድረክ የተመድ አባል ሀገራት በአራት ዓመት ከግማሽ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የአፈፃፀም ሪፖርት የሚ ያቀርቡበትና የሚገመግሙበት መድረክ ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ በ2009 እና በ2014 በተካሄዱት ሁለት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ መድረኮች ላይ መሳተፏ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011